ምትክ ቤትና ካሳ ሳይሰጣቸው ቤታቸው እየፈረሰ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ምትክ ቤት እና ካሳ ሳይሰጣቸው ቤታቸው እየፈረሰ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ስር የሚገኘው የቀጠና 3 እና 4 አካባቢ፥ የተጠጋጉ የግል ቤቶች ከቀበሌ ቤቶች ጋር ጣራና ግድግዳ የተጋሩበት ያረጁ እና የተጎሳቆሉ ቤቶች በብዛት የሚገኙበት አካባቢ ነው።

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮም አካባቢው ለመልሶ ማልማት ይፈርሳል በሚል ምክንያት በነዋሪው እና በወረዳ አስተዳደሩ መካከል አለመግባባት ሲያስተናግድ ቆይቷል።

ከ200 በላይ ነዋሪዎችም ምንም አይነት የቤት ምትክም ሆነ መሬት ሳይሰጣቸው ቤታቸው እየፈረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ለስብሰባ በተጠሩበት አጋጣሚም በጎን አፍራሽ ግብረ ሀይል ተልኮ ቤታቸው መፍረሱንም ይናገራሉ።

የትኛውም የመልሶ ማልማት ሲከናወን ቀድሞ በስፍራው ለነበሩ ዜጎች ማረፊያ ማዘጋጀት የመንግስት ሃላፊነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሚመለከተው አካል ህግና መመሪያውን ተከትሎ ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ ጠቅሰው፥ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

ከአራዳ ክፍለ ከተማ የተገኘው መረጃ ቦታው ለመልሶ ማልማት እንዲፈርስ የተወሰነው በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሲሆን፥ ከ2 ነጥብ 28 ሄከታር በላይ መሬት ላይ የሰፈሩ 272 ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 212ቱ የቀበሌ፣ 4 የኪራይ ቤቶች አስተዳደርና 56 የግል መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፤ እስካሁን ለ80 ሰዎች ኮንዶሚኒየም ቤት ምትክ ተሰጥቷቸዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ጽህፈት ቤት የነዋሪዎቹ ቤት በተባለው መልኩ አለመፍረሱን ጠቅሶ፥ ኮንዶሚኒየም ቤት ምትክ የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት ብቻ ማፍረሱን ገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉ ብርሀን፥ የነዋሪዎቹ ቅሬታና ጥያቄ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ የማፍረሱ ስራ ለጊዜው ተቋርጧል ብለዋል።

ከንግድ ቤቶች ጋር በተያያዘ ግን ወረዳው ላይ የንግድ ቤቶች የሚስተናገዱበት አግባብ እንደሌለም ምላሽ ሰጥተዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፥ በመልሶ ማልማት መመሪያ መሰረት ማንኛውም ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል ተነሽ ምትክ ቤትና ካሳ ሳይሰጠው ከቦታው እንዲነሳ አይፈቅድም ይላል።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ምትክ ቤትና ካሳ ከተሰጠ በኋላ፥ በቀበሌ ቤት የሚኖሩት በአንድ ወር በግል ቤት ነዋሪዎች ደግሞ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ቤቱን እንዲለቁ በመመሪያው መቀመጡንም አስረድተዋል።

ለግል ቤቶች ምትክ ቤትና ካሳ ለመስጠትም ኮሚቴ ተቋቁሞ ካሳ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማቅረብ የሚችሉት በዚህ ሂደት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጥበት በተደጋጋሚ የጠየቅነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ጽህፈት ቤት ጉዳዩን ስለማላውቀው በሚል ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

ይፈርሳሉ ተብለው ውሳኔ በተላለፈባቸው አካባቢዎች ባደረግነው ቅኝት ግን፥ የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን መጸዳጃ ቤትና ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን በአዲስ መልክ በመቅበር ላይ ነው።

 

Share.

About Author

Leave A Reply