ትንቢተ ሀብታሙ አለባቸው፤ እውነት ወይስ ሐሰት?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(በፍቃዱ ሀይሉ)

ደራሲ እና መምህር ሀብታሙ አለባቸው “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪክ በተነተነበት መጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ‘የአገሪቱ መፃኢ ዕጣ ፈንታ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ምን ሊሆን ይችላል?’ የሚለውን ጥያቄ ያነሳል። ትንቢቱ ግን እሱ ካሰበው ቀድሞ እየመጣ ይመስላል። ሀብታሙ ነገሩን በኳስ ጫወታ በመመሰል ነው ቢሆኖችን ያስቀመጠው። “ኳሷ የምትገኘው በኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ነው” ብሎ ይጀምራል።

ቢሆን አንድ፦ ኢሕአዴግ በጫወታ ብልጫ ግብ ያስቆጥራል። ቢሆን ሁለት፦ በኢሕአዴግ የአጨዋወት ድክመት ጎል ይቆጠርበታል። ቢሆን ሦስት፦ ኳሳ የትኛውም ጎል ውስጥ ሳትቆጠር ሜዳ ላይ ትጉላላለች። ቢሆን አራት፦ ኳሷ ከጫወታ ውጪ ሆና ጫወታው ለተወሰነ ግዜ ይቋረጣል።

እንደደራሲው ከሆነ በጣም ተናፋቂው የመጀመሪያው ቢሆን ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተቃርኖ የሚታረቀውም ሆነ ልማቱ የሚሳለጠው ኢሕአዴግ በጫወታ ብልጫ ተቃዋሚዎቹ ላይ ግብ ካስቆጠረ ነው ብሎ ያምናል። ደራሲው ያልፈለገው እና የመጀመሪያው ቢሆን “ቀጥተኛ ተቃራኒ” ብሎ ያለው ደግሞ ሁለተኛውን ቢሆን ነው።

እኔ ግን እንደሀብታሙ ባልጠላውም አሁን እየሆነ ያለው ሁለተኛው የቢሆን ግምቱ ይመስለኛል። ሀብታሙ በዚህ ግዜ “ባለ ድግሪ የቀን ሠራተኞች፣ ባለ ድግሪ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደአሸን ይፈላሉ” ይላል። ቀጥሎም “ሚሊዮን ባለዲግሪ ወጣቶች ዲፕሎማውን ባደላቸው መንግሥት ላይ ይዘመምታሉ” ይላል። ይህም ሆኗል። ነገሩን ሲያጠናክረው የሚከተለውን እያለ ነው፦ “የሕዝብ ግፊት ጋር ተዳምሮ የሥራ አጡ ሠራዊት ቁጥር ይንራል። መንግሥት ችግሩን መፍታት እየተሳነው ሲሔድ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ድርጅታዊ ቀውስ ይከተላል። አባል ድርጅቶች ትስስራቸው ላልቶ የመጨረሻ ዋስትና ፍለጋ ወደየክልላቸውና እንወክለዋለን ወደሚሉት ሕዝብ ያፈገፍጋሉ”።

መጽሐፉ የታተመው አምና፣ ሰኔ 2009 ነው። ይህች ንግግሩ ዘንድሮ ላይ ትንቢታዊ ትመስላለች።

ደራሲው ይህ አሁን እየሆነ የሚመስለው ነገር ከሆነ መዓት ይመጣል ብሎ ነው የተነበየው። “በሀብት ክፍፍል ምክንያት ደም አፋሳሽ ግጭት ይቆሰቆሳል። የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ ገብቶ ሁኔታውን ለመለወጥ ሲሞክር በውስጡ ብሔር ተኮር ቅራኔ ተፈጥሮ የእርስበርስ ግጭት ይነግሳል። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከ1900ዎቹ በፊት ወደነበረችበት ያልተማከለ ሁኔታ ትመለሳለች።”

የደራሲው ‘ፖለቲካዊ ግምት እውን ይሆን ይሆን?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በርግጥ ደራሲው ለትሕነግ/ኢሕአዴግ ስርዓት ወገንተኛ ስለሆነ ነገሮች በኢሕአዴግ አሸናፊነት ካልተጠናቀቁ በአዎንታዊነት ይቆጫሉ ብሎ እንደማያምን ጽሑፉ ያሳብቃል። ሦስተኛውን የቢሆን ግምቱም ቢሆን በሕዝብ ቁጣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢለቅ እና ተቃዋሚዎች ሥልጣን ተቆጣጥረው አዲስ ስርዓት መንግሥት ሊያዋቅሩ ቢሞክሩ ስለማይሳካላቸው ፖለቲካዊ ቁሞቀርነት (“political deadlock”) ሊከሰት ይችላል ብሎ ገምቷል። በአራተኛው ቢሆን እንደተነበየው ደግሞ የአሁኑ የኢሕአዴግ ጉዞ ቀስ እያለ ማዝገሙን ይቀጥላል። “ከእነችግሮቹ አመራሩን ለሦስተኛው ትውልድ ያስተላልፋል” ብሎ ተንብዩዋል።

ሀብታሙ እንዳለው ኢሕአዴግ በራሱ ግብ ተቆጥሮበታል እንበል። አባል ድርጅቶቹም እርስበርስ ዓይንና ናጫ ሆነዋል። እሱ እንደፈራው በዚህ ምክንያት የሀብት ክፍፍል ግጭት ይነሳ ይሆን? መከላከያው ጣልቃ ገብቶ ግጭቱን የብሔር ቅራኔ መልክ ይሰጠው ይሆን? በዚህ ሳቢያ አገሪቷ ትበታተን ይሆን?

ሊሆን ከሚችለው ነገር ባልተናነሰ ሊሆን ስለሚችለው ነገር መነጋገር አለመቻላችን ያሳስበኛል። በመነጋገር ሊሆን የሚችለውን ማስተካከል ይቻላል።

አሁን የድርጅት ውስጥ ቀውሱ እውን ሆኗል። ኦሕዴድ የትሕነግን የኢሕአዴግ ውስጥ የበላይነት ለመንጠቅ እየሮጠ ነው። በዚህ መሐል የሚፈጠረው ግጭት ውጤቱ ምን ይሆናል? ከነባሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ በኋላ እና ከአዲሱ ሹመት በፊት ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጣለ? ለምን አገሪቱ በፀጥታ ኃይሉ እንድትመራ ተፈለገ? የኦሮምያ ክልል የኢኮኖሚ አብዮት እና የፀረ ኮንትሮባንድ ዘመቻዎች አንድምታቸው ምንድን ነው?

Share.

About Author

Leave A Reply