አርቲስት ሚካኤል በላይነህ~ “መንግስት ህዝቡን በዱላ እና በጥይት አስተዳድረዋለሁ ብሎ እያሰበ ከሆነ የስህተቶች ሁሉ ስህተት ሆኖ እንደሚጠቃለል ጥርጥር የለውም።”

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ በምኖርበት ለገጣፎ ቤቴ መግባት አቅቶኝ ሌላ ቦታ ጥገኝነት ይዤ ተቀምጬ ዋልኩ። እንደበሽተኛ የወዳጅ ዘመድ ስልክ እየተቀበልኩ እስካሁን ሰላምኝ፣ ደህና ነኝ ቤቴ መግባት አልቻልኩም እንጂ እያልኩ ስመልስ ቀኑ መሸ መሽቶም ስልኩ አልቆመም።

ብሶት ነው የወለደኝ ያለው መንግሥት እራሱ መልሶ ከባድ የብሶት አምራች ከሆነ ከረመ።
ለመንግሥት የህዝብን ልብ ትርታ ማድመጥ ወይንም ጥያቄዎቹን መመለስ ዋናው ተግባሩ መሆን ነበረበት። ነገር ግን በሀገራችን ሰው እራሱን ችሎ ማሰብ የማይችል ይመስል ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ከጀርባው እከሌ አለ፣ ከጎኑ የእንትና ቡድን ነው ያነሳሳው እየተባለ ትክክለኛውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከጉዳዩ እየሸሹ ቤታችን ወጥተን መግባት የማንችልበት ግዜ ላይ እድርሶናል።

እስከ ዛሬ ስንቱ ቦታ ሲታመም ሰላም በለገጣፎ ያለ ይመስል ነበር ፣ ግን ትላንት ከምሩ ሲናጥ አርፍዷል፣ ውሏል። እንደሚገባኝ ይህ ማለት እንቅስቃሴው ጉዞውን በአንድ እርምጃ ወደ ዋናው ከተማ አስጠግቷል ማለት ነው። የአዲስ አበባ ፌደራል ፓሊስ እና ትራፊክ ፖሊስ የነደደውን የጎማ ጭስ ከማየት ባሻገር አሽትተውታል።

ነገስ… የት ይሆን??
በመሃል ከተማ ወይስ በቤተ መንግሥት???

ባለሥልጣናት!!! እየተጨነቃችሁ አታስጨንቁን። ከዚህ በኋላ መፍትሄው አንድ መንገድ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ለሚል ወገን በሙሉ በሩን ክፍት አድርጎ ለአዲስ ዘመን እራስን ማዘጋጀት።

አንድ የድሮ ቀልድ ልንገራችሁ።
ጥያቄ: ጓድ መንግስቱ ለእርሶ ሰፊው ሕዝብ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ: ለእኔ ሰፊው ሕዝብ ማለት ቢገድሉት ቢገድሉት የማያልቅ ማለት ነው። ብለዋል አሉ።

መንግስቱ ኃ/ማርያም ገድሎ ያልጨረሰውን ሕዝብ የዛሬው መንግስት በዱላ እና በጥይት አስተዳድረዋለሁ ብሎ እያሰበ ከሆነ የስህተቶች ሁሉ ስህተት ሆኖ እንደሚጠቃለል ጥርጥር የለውም።

ሰላም ለሁሉም ወገን ይበጃል።

እግዚአብሔር ሆይ የኢትዮጵያ ሀገራችንን ሰላም አብዛልን።  (ሚካኤል በላይነህ) ~ ቃሊቲ ፕሬስ

 

Share.

About Author

Leave A Reply