…እኛ እንድንፈታ ህዝብ የደም ዋጋ ከፍሎበታል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

እኛ እንድንፈታ ህዝብ የደም ዋጋ ከፍሎበታል

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ መልስ | ለሸገር ታይምስ

የኢህአዴግ አራቱ መስራች ድርጅቶች ሊቀመንበሮች የሰጡት መግለጫ ለሀገሪቱ ፖለቲካ ብዙ ነገር ይዞ የመጣ ይመስላል። መግለጫው እስረኞችን ስለመፍታትና ማዕከላዊ የተባለውን ቦታ ስለመዝጋት ተነግሮበታል። ከዚህ መግለጫ በኋላ እስረኞች ከማረሚያ ቤቶች መለቀቅ ጀምረዋል።

በአገሪቷ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ታሳሪዎች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አንዱ ነው። እስክንድር በአስኳልና ምንሊክ ጋዜጦች የሚታወቅ ጸሀፊ ሲሆን ስርዓቱን የሚተቹ በርካታ ጹሁፎችን ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወቃል።

ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በአገሪቷ ስላለው የፖለቲካ ትኩሳት፣ መለወጥ አለባቸው ብሎ ስለሚያስባቸው ነገሮች አንዲሁም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ቀውስ እንድትወጣ መፍትሄ ነው ስለሚለው ሃሳብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከ ሸገር ታይምስ መፅሄት ባልደረባ አንድነት በጋሻው ጋር ቆይታን አድርጓል።

ሸገር ታይምስ መፅሄት፡- ከእስር በኋላ ኢትዮጵያን አንዴት አገኘሀት?

እስክንድር፡- ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት እንዳለ ነው የተገነዘብኩት በተለይ በምንወጣበት ጊዜ ህዝቡ ደማቅ የሆነ አቀባበል ነው ያደረገልን። ይህ ደማቅ አቀባበል ግን ለኛ በግል የተደረገልን አቀባበል አይደለም። በግል ብቃታችን ወይም በጣም ከፍተኛ መስዋዕትነት ስለከፈልን የተደረገልን አቀባበል አይደለም፡፡ አቀባበሉ ህዝቡ የለውጥ ፍላጎት እንዳለው የገለጸበት ነው። ለውጥ እፈልጋለሁ እያለ ነው። እዚህ ጋር ሁለት ነገር አለ አንዱ ህዝቡ እኛን የከፈላችሁት መስዋዕትነት ዋጋ አለው እያለ ነው፡፡ በአንድ በኩልም ትግሉ ዝም ብሎ አይደለም ውጤት እያመጣ ነው የሚል መልዕክት እያስተላለፈልን ነው።

በሌላ ወገን ደግሞ ህዝቡ ለኢህአዴግ ነው መልዕክት እያስተላለፈ ያለው።እኛ ከከፈልነው መስዋዕትነት በበለጠ እሱ ነው ትልቁ ነገር። መልዕክቱ ምንድነው? ጊዜው የለውጥ ነው። ለወጥ እንፈልጋለን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንፈልጋለን ነው እያለ ያለው። ኢሀአዴግ መታደስ ብቻ ሳይሆን ከመታደስ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ቦትስዋና፣ እንደነማላዊ እነደነ ደቡብ አፍሪካ እንደነቤኒን የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ እንዳለው አይነት ዴሞክራሲ እፈልጋለሁ እያለ ነው ። ማተኮርም ያለብን በዚህ በሁለተኛው መልዕክት ላይ እንጂ እኛ በከፈልነው መስዋዕት ላይ አይደለም። ሁለተኛው መልዕክት ራሱ ተስፋና አደጋ አለው። ይህንን የለውጥ ጥያቄ ይህንን የለውጥ ፍላጎት በአግባቡ ልናስኬደው ካልቻልን ወደባሰ ነገር ነው የምንሄደው። ወደመጥፎ ነገር ነው የምናመራው።

ሸገር ታይምስ መፅሄት፡- ሀለተኛው ጉዳይ ማለትም ለውጥ እንፈልጋለን ያለውን ህዝብ አደራጅቶ የሚመራው ማነው?

እስክንድር ነጋ፡- በነገራችን ላይ ህዝቡ ለውጥ እፈልጋለሁ ሲል ኢህአዴግን እንደፓርቲ እንዳትኖር እፈልጋለሁ እያለ አይደለም። የኢህአዴግን አምባገነንነት ነውን አልፈልግም እያለ ያለው። በሁለቱ መካከል መሰረታዊ ልዩነት አለ። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካለ ለኢህአዴግ ቦታ ይኖረዋል። ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ቦታ አለው። ህዝቡ እያለ ያለው ኢህአዴግ ይደምሰስ አይደለም፣ህዝቡ እያለ ያለው ኢሀአዴግ አንዲኖር አልፈልግም አይደለም። ህዝቡ እያለ ያለው ኢህአዴግ የምታምንበትን ዓላማ ተው አይደለም። ህዝቡ እያለ ያለው ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩልነት የሚያስተናገድ እና ሃሳብ በነጻ የሚገለጽበት ስርዓት እፈልጋለሁ ነው።

እንደልቤ የምደራጅበት ስርዓት እፈልጋለሁ እያለ ነው። በኢህአዴግ ላይ እንደ ኢህአዴግነቱ የመጣ ተቃውሞ አይደለም። በኢህአዴግ ዓላማ ላይ አይደለም ህዝቡ ያለው ተቃውሞ በኢህአዴግ አምባገነንነት ላይ እንጂ። በአምባገነንነት ላይ የተነሳ ተቃውሞ ነው። ይህንን አበክረን መያዝ አለብን። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካን ብንወስድ እዛ ለውጥ የመጣው የአፓርታይድ ፈልሳፊ አርክቴክት ጠንሳሽ ተግባራዊ ያደረገው ናሽናል ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ቦታ ነበረው። ለውጡ የመጣው በናሽናል ፓርቲ ላይ አይደለም በአፓርታይድ ስርዓቱ ላይ ነው። ህዝቡ ያፈረሰው የአፓርታይድ ስርዓትን እንጂ ናሽናል ፓርቲውን አይደለም።

ናሽናል ፓርቲው በዴሞራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ቦታ ኖሮት ከኤኤንሲ ጋር ተፎካክሮ የተወሰነ ድምጽም አግኝቷል ። እንዲየውም ከሚጠበቀው ድምጽ በላይ ነው በወቅቱ ያገኘው። ሊያውም የፖለቲካ ተንታኞች ራሱ ከጠበቁት በላይ ድምጽ፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ነገር ነው የአትየጵያ ህዝብ እየጠየቀ ያለው። ስለዚህ የኢህአዴግ አባላት ይሄን አላግባብ መረዳት አይገባቸውም። በተለይ በተለይ በራሳቸው ፣ በእምነታቸው እና በድርጅታቸው ላይ የመጣ ማዕበል አድርገው ሊቆጥሩት አይገባም ።

ሸገር ታይምስ መፅሄት ፡- ኢህአዴግ እነዚህን ማድረግ ይቻለዋል?

እስክንድር ነጋ፡- ህዝቡ እነዚህን ነገሮች ጣል እያለው አይደለም። ለምሳሌ መሬት የመንግስት ነው የሚለውን እምነቱን ጣል እያለው አይደለም፤ ሕዝቡ ላይ በሀይል አትጫን ነው ያለው ያለው፡፡ አልደራደርባቸውም ያላቸውን ነገሮች ችግር የለውም ይህን እምነትህን ይዘህ ትቀጥላለህ ግን ህዝብ ላይ በጉልበት አትጫን እያለው ነው እዚያ ላይ ነው ልዩነቱ፡፡ ስለዚህ እሱ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸውን አላማዎች ይዞ መቀጠል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ክልሎች መደራጀት ያለባቸው በቋንቋ ነው የሚል አቋም አለው ይህን አቋሙን ይዞ መቀጠል ይችላል፡፡

አሁን የተነሳው የዴሞክራሲ እንቅስቃሴም ይህን ለውጥ እያለው አይደለም፡፡ በነጻ ምርጫ ውስጥ ተሳትፈህ የምታሸንፍ ከሆነ እነዚህን አላማዎችህን ይዘህ መቀጠል ትችላለህ፡፡ የምትሸነፍ ከሆነ ግን አቋምህን ይዘህ ህዝብን ለማሳመን ትታገልና ሌላ ምርጫ ላይ እድል ታገኛለህ፡፡ ምክንያቱም ምርጫ አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ በምርጫ ተሸንፈህ እንደገና በሌላ ምርጫ ተወዳድረህ ህዝቡን አሳምነህ ታሸንፋለህ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ እያለ ያለው፡፡ ለዚህ ነው የህዝብ ጥያቄ በኢህአዴግ ፕሮግራም ላይ ሳይሆን በኢህአዴግ አምባገነንነት ላይ ነው የምለው፡፡

ሸገር ታይምስ መፅሄት፡- ከእስር የተለቀቃችሁትን በተመለከተ ኢህአዴግ ማሻሻያ ስላደረኩ ነው የተፈቱት ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከእስር የተፈታሁት በህዝብ ጫና ነው የሚል አመለካከት አለህ፡፡ በአንተ እምነት የተለቀቃችሁት መንግስት ባደረገው ማሻሻያ ነው ወይስ በህዝብ ጫና?

እስክንድር ነጋ፡- ምንም ጥያቄ የለውም የተፈታነው በህዝብ ጫና ነው፡፡ በነገራችን ላይ በኢህአዴግ አመራርና በኢህአዴግ አባላት መካከል ብዙ ልዩነት አለ፡፡ በአምባገነናዊ ስርዓት ባለቤቶቹ ታች ያሉት አባሎቹ ሳይሆኑ ከላይ ያሉት አመራሮቹ ናቸው፡፡ የተወሰኑ አመራሮቹ የለውጥ ፍላጎት እንዳላቸው እየታየ ነው፡፡ እያየነው ካለው አንፃር የእስረኞች መፈታት እና ለውጥ እንዲሁም በኦህዴድ ውስጥ ስብሰባውን ሲጨርስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ፓርቲዎች ጋር መስራት እፈልጋለሁ ካለው ተነስተን በኢህአዴግ ውስጥ የዴሞክራሲን ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ የማይታወቀው ምን ያህል ቁጥርና ምን ያህል አቅም እንዳለው ነው፡፡ አሁን በኦህዴድ ውስጥ ይህ ተከስቷል በሌሎቹ ሶስት ድርጅቶች ውስጥ እንደዚህ አይነት ተጨባጭ የሆነ ለውጥ አላየነም፡፡

በዋናነት ግን እስረኞች የተለቀቁት መሬት ላይ ባለው የህዝብ ተቃውሞና ጫና እውነታ ነው፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ እንደተጠበቀ ሆኖ እኛ እንድንፈታ ህዝብ የደም ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ የተፈታነው በህዝብ የደም ዋጋ ነው፡፡ ኢህአዴግ ውስት ያሉትን ጥቂት አመራሮች ወደ ለውጥ እንዲመጡ ያነሳሳቸው መሬት ላይ ያለው የህዝብ ጫና እንጂ ኢህአዴግ ለለውጥ የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ገና ነው፡፡ ነገር ግን ይህን የአስተሳሰብ አብዮት እየጠበቅን ነው፡፡

ሸገር ታይምስ መፅሄት ፡- ያልተፈቱ ብዙ እስረኞች አሉ ይባላል፡፡ እዚህ ላይ ምን ትላለህ?

እስክንድር ነጋ፡- ቀሪ ትግል እንደሚቀረን እና ትግሉ እንዳላበቃ ነው የምረዳው፡፡ ያልተፈቱ ብዙ እስረኞች አሉ፡፡ እኔ ከማውቃቸው እንኳን ለምሳሌ ዮናታን ተስፋዬ አልተፈታም፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ትግሉ ገና ነው፡፡ ትግሉ ግን የፖለቲካ እስረኞችን ከማስፈታት በዘለለ አንድ ደረጃ መሻገር አለበት፡፡ እሰረኞችን የማስፈታቱ ሂደት ሙሉ በሙሉ ባያልቅም እየተገባደደ ስለሆነ ወደምንፈልገው ነገር ለመሄድ አንድ ተጨማሪ ተጨማሪ ጥያቄ ያስፈልገዋል፡፡

በእኔ ግምት ይህን ጥያቄ ህዝቡ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ከሚለው በተጨማሪ ከዚህ በፊት የፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለባቸው ብሎ እንደታገለው ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ህገ ወጥ ወይም ህጋዊ ብሎ ልዩነት ሳያደርግ እደራደራለሁ ብሎ በአደባባይ ቃል እንዲገባ ህዝቡ ጥያቄ ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ ጥያቄ ከተመለሰ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ መቋጫ የሚሰጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለድርድርና ለውይይት ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ከተቀመጠ ሰላማዊ ትግሉን ወደ አንድ ደረጃ እናደርሰዋለን ማለት ነው፡፡

ሸገርታይምስ መፅሄት፡- በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ካሸነፈ በኋላ አገሪቱ ላይ ሁለት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ የደረሱ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ የድርጅቱ ነባር ታዮችና አመራችም ከስራ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው እንደገና የተመለሱም አሉ፡፡ ሰሞን ደግሞ አቶ ኃይማሪያ ከስልጣቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ እነዚህን መንገራገጮች የተመለከቱ አገሪቱ አደጋ ላይ ናት ይላሉ፡፡ ለዚህ የህዝብ ስጋት መፍትሔው ምንድን ነው ትላለህ?

እስክንድር ነጋ፡- እኔ ደግሜና ደጋግሜ የምለው ለኢትዮጵያ የሚሻላት ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ድርድር አደርጋለሁ ብሎ ቃል መግባት ነው፡፡ ወደ መፈራረስ የሚወስደንን አሁን ያለውን ግጭት ማስቆም የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር አሁን ኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እለቃለሁ ማለታቸውን ጨምሮ ይህ መሸጋሸግ ኢህአዴግን ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለድርድር የሚወስደው ከሆነ እሰየው፡፡ ወደ መፍትሔ እየሄድን ነው ማለት ነው፡፡ ወደ ድርድር የማይወስደው ከሆነ ግን ኢትዮጵያን ወደባሰ ችግር ነው የሚወስዳት ፡፡ ይህ ደግሞ መፍትሔ ሳይሆን ችግር ነው ማለት ነው፡፡ ወዴት እየሄድን ነው የሚለውን ግን አቅጣጫውን አላውቅም፡፡ በሂደት የምናየው ነገር ነው፡፡

ሸገርታይምስ መፅሄት፡- በኢትዮጵያ የብሔር ግጭቶች እና መጠራጠሮች ይታያሉ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሊወሰድ የሚገባው መፍትሔ ምንድን ነው ትላለህ?

እስክንድር ነጋ፡- ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ኢህአዴግ በአደባባይ ወጥቶ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ ቃል እንደገባው ሁሉ አሁንም አደባባይ ወጥቶ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ልዩነትና መስፈርት ሳያስቀምጥ እደራደራለሁ ብሎ ቃል ቢገባ አሁን የምናየውና የምንሰማቸው ግጭቶች በማግስቱ ነው የሚቆሙት፡፡

ሸገርታይምስ መፅሄት ፡- ኢህአዴግ በባህሪው ለውይይትና ለግልጽ ድርድር በሩን ሊከፍት የሚችል ፓርቲ ነው?

እስክንድር ነጋ፡- ልክ ነህ የኢህአዴግ ባህሪ እንደዛ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ አስገዳጅ እውነታ እየፈጠረ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩትም በኢህአዴግ አመራር ውስጥ ግልጽ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ለመከሰቱ ማረጋገጫ የለም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ መሬት ላይ ያለው የህዝብ ጫና እያስገደደው ነው፡፡ እስረኞችን የፈታውም እኮ በህዝብ ጫና ነው፡፡ ይህ መሬት ላይ ያለው አስገዳጅ ሁኔታ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም እንዲደራደር የሚያደርግ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቢቀርና ኢህአዴግ በአቋሙ ጸንቶ አልደራደርም ብሎ የሚቀጥል ከሆነ ወደማንፈልገው ብጥብጥና ግጭት ሊወስደን ይችላል፡፡

በኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ ኢትዮጵያን ከጥፋት ሊታደጉ የሚችሉበት ብልሃት ይህ ነው መሬት ላይ ወደ ብጥብጥ የሚወስዱ አስገዳጅ ምክንያቶች ሳፈጠሩ ቀድመው መፍትሔው ይህ ነው ብለው በዛ መንገድ መሄዱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ካልኩለስ ወይም ኑክሌር ፊዚክስ አይደለም ቀላል እና አስተማማኙ መንገድ ነው፡፡

ሸገርታይምስ መፅሄት ፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ወታደራዊ መንግስት ይቋቋማል የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ እውን ወደዚያ ሊወስደን የሚችል ምክንያት ይኖራል?

እስክንድር ነጋ፡- ወታደራዊ መንግስትማ ሊቋቋም እንደማይችል የአፍሪካ ህብረት ይከለክላል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ መንግስትን (Zero Tolerance) ይለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና በኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት ይቋቋማል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትተፋ እና ማዕቀብ እንዲጣልባት ያደርጋል፡፡

ወታደራዊ መንግስት ቢቋቋም ከአውሮፓዊያን እና ምዕራባዊያን በፊት መጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የሚጣላው እዚሁ አዲስ አበባ ከሚገኘው ከአፍሪካ ህብረት ጋር ነው፡፡ በዓለም ላይ የወታደራዊ መንግስት ዘመን አልፏል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ወታደርና ፖለቲካ አብሮ የማይሄዱ ወሃ እና ዘይት መሆናቸውን በደርግ አይተነዋል፡፡ ፖለቲካ ሲበላሽ ወታደሮች ሊያስተካክሉት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ መንግስት ኢትዮጵያዊያን ላለንበት ችግር መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡

ሸገርታይምስ መፅሄት ፡- ከእስር እንደምትፈቱ ከተነገረ በኋላ እንድትፈርሙት የሚጠይቅ ሰነድ ቀረበላችሁ፡፡ እሱን መፈረም እንደማትፈልጉ ገልጻችሁ ወደ እስር ቤት መመለሳችሁ ተሰምቷል፡፡ እንድትፈርሙ የቀረበላችሁ ሰነድ ምንድን ነው ሂደቱስ እንዴት ነበር?

እስክንድር ነጋ፡- በመጀመሪያ በአማራ ቴሌቪዥን ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሰጠውን መግለጫ ጠቅሶ እነ እከሌን ጨምሮ 417 እስረኞች እንዲፈቱ የይቅርታ ቦርድ ወስኗል የሚል ዜና ሰማን፡፡ ይህን ዜማ ስሰማ እኛ ይቅርታ ስላልጠየቅን ዜናው ዱብ እዳ ቢሆንብንም ይፈታሉ የሚለውን ዜና ስንሰማ ደስታ ነበር የተሰማን፡፡ ተፈትተን እውነታን ለህዝብ መንገር እንደምንችል ስለምናውቅ የይቅርታው ጉዳይ አላሳሰበንም፡፡ በነጋታው ጠዋት በመንግስት የስራ መግቢያ ሰዓት ቢሮ ተጠራንና መንግስት ሊፈታችሁ ወስኗል እና ይህ የይቅርታ ቦርድ ፎርም ነው ይህን ፎርም ሞልታችሁ የግንቦት ሰባት አባል እንደሆናችሁ ገልጻችሁ ፈርሙ አሉን፡፡

እኛም ‹ትናንት እኮ በቴሌቪዥን ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ እንዲፈቱ ተወስኗል ተብሎ በዜና ተነግሯል፡፡ እንዴት ነው አሁን የይቅርታ ፎርም የምንሞላው›› አልን፡፡ በዚህ ብቻ ሳይሆን በመርህ ደረጃ ከተያዘንበት ጊዜ ጀምሮ ይቅርታ እንደማንጠይቅ ገልጸን ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በቅንጅት በነበረው ሁኔታም በይቅርታ መደምደም የለበትም ብለን ወስነናል፡፡ ይህ ውሳኔያችንን ደግሞ ለስድስት ዓመት ተኩል ይዘነው የቆየነው ውሳኔ ነው፡፡ ስድስት ዓመት ተኩል የቆየነውም በዚህ ውሳኔያችን ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ በሚዲያ ተናገሩትም አልተናገሩትም እኛ ይቅርታ የምንፈርምበት መንገድ አልነበረምና ‹አንፈርምም› ብለን መለስንላቸው፡፡

ፈርሙ ብሎ እምቢ ስላልነው አይፈታንም ብለን ተስፋ ቆርጠን ቁጭ ብለን ሳለ አንድ ቀን ጠዋት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ እነ እከሌ እና እከሌ ዛሬ ይለቀቃሉ ተብሎ ሲነገር ሰማን፡፡ በድጋሚ ወደ ቢሮ ተጠራንና ‹እናንተ አንፈርምም ብትሉም መንግስት ሊለቃችሁ ወስኗል፡፡

ማንኛውም እስረኛ ሲፈታ የሚሞላው ፎርም አለ፡፡ ይህ ደግሞ የማረሚያ ቤቱ አሰራር ነውና እዚህች ላይ ይህን ፎርም ሙሉ እና እንለቃችኋለን› አሉን፡፡ አሁንም አንፈርም አልናቸው፡፡ አንፈርምም የምንላቸው ትዕቢት ወይም ህጉን አለማክበር ሳይሆን ምንም ወረቀት ላይ ብንፈርም ‹ፈርመዋል አልፈረሙም› የሚል ክፍተት ያመጣል፡፡ ፈርመው ነው የወጡት ሲሉ እኛ ደግሞ ‹የፈረምነው የማረሚያ ቤቱን እንጂ የይቅርታ ቦርዱን አይደለም› እያልን እንባላለን ከዚያ ልንጨቃጨቅ ነው ማለት ነው፡፡

ለህዝባችን የገባነው ቃል አለ ያንን ቃል ማክብር ስላለብን የተሳሳተ አረዳድ (miss understanding) እንዳይፈጠር እንጂ ለህግ ተገዥ ካለመሆን ጋር የሚያያዝ ሳይሆን በዚህ ምክንያት እዚህ ወረቀት ላይም አንፈርምም ይቅርታ አድርጉልን ብለናቸው ወደ እስር ቤቱ ተመለስን፡፡

ከዚህ በኋላ ይፈቱናል ወይስ አይፈቱንም ብለን 50 በመቶ ብቻ ተስፋ ይዘን ወደ እስር ቤቱ ከገባን በኋላ ወደ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ጠርተውን ‹በሉ መውጣት ትችላላችሁ እቃችሁን ሰብስቡ› አሉ፡፡

እቃችንን ሰብስበን ወጥተን በር ላይ ተፈትሸን በር ላይ ከደረስን በኋላ የይቅርታ ቦርድ የሚሰጠው ሰርተፊኬት አለ ያንን ሰርተፊኬት አመጡና ‹ይህን የይቅርታ ቦርዱ የሚሰጠው ሰርተፊኬት ነው፡፡ ዋናውን ውሰዱና ኦርጂናሉን ስለመውሰዳችሁ ኮፒው ላይ ፈርሙ› አሉን፡፡ እኛ ግን ለሶስተኛ ጊዜ አንፈርምም አልናቸው፡፡ እንደ ሁለተኛው ፊርማ ሁሉ አሁንም የሰጠናቸው ምክንያት ተመሳሳይ ነው ብዥታ እንዲፈጠር አንፈልግም የሚል፡፡

ምክንያም ቃላችንን አክብረናል ብለን ለህዝባችን ለመናገር አያስችለንም፡፡ የታችኞቹ ፖሊሶች ይህን ስንነግራቸው ለኃላፊዎቻቸው ሲነግሯቸው ‹በቃ ይሂዱ› የሚል መልስ ሰጧቸው፡፡ እኛም የይቅርታ ቦርዱ የተሰጠንን ሰርተፊኬት ይዘን ከማረሚያ ቤቱ ተለቀን ወጥተናል፡፡

ሸገርታይምስመፅሄት፡- ከዚህ በኋላስ እሰክንድርን በምን አንጠብቀው?

እስክንድር ነጋ፡- እኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ወደ ነጻው ፕሬስ ስገባ ንጹህ ጋዜጠኛ ሆኜ መስራት ነበር አላማዬ፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ይህን እንዳደርግ አላስቻለኝም፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይመሰረት አንድ ጋዜጠኛ ንጹህ ጋዜጠኛ ሆኖ ለመስራት የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ የምታደርገው በአንድ እጅህ ጋዜጠኝነትን ትሰራለህ በአንድ እጅህ ደግሞ የጭቆናው ሰለባ ስለሆንክ በዜግነትህ ብቻ ሳይሆን በሙያህም ለመብትህ ለመታገል ትገደዳለህ፡፡ ይህ እንግዲህ ፕሬስ ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ የነበረኝ ስራ ነው፡፡

ጋዜጠኝነቱን ይዘን ለነጻ ፕሬስ፣ ለሰብአዊ መብት እና ለዴሞክራያዊ መብት መከበር ስታገል ነበር የቆየሁት ጋዜጣዬ እስከተዘጋበት ምርጫ 97 ድረስ፡፡ አሁንም ፍላጎቴ ይህንኑ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ጋዜጠኝነቱን እሰራለሁ በአንድ በኩል ደግሞ አክቲቪስትነቱንም እቀጥላለሁ ዴሞክራሲ እስከሚከበር ድረስ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply