የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል መንግስት ለ2010 በጀት ዓመት የ14 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ተጨማሪ በጀቱን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ተጨማሪ በጀቱ የፀደቀው ለ2010 ከፀደቀው አጠቃላይ 320 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ውስጥ ለመጠባበቂያ ተይዞ የነበረው 2 በመቶ ገንዘብ ለተፈጥሮ አደጋዎች መቋቋሚያ በመዋሉ መሆኑ ተጠቅሷል።
ተጨማሪ በጀቱ በሀገሪቱ የሚደርስውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም፣ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ቀሪ ክፍያን ለመሸፈን፣ የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ቀጣይ የቅበላ አቅም ለማሳደግና የዲጂታል ቴሌቪዥን ሽግግርን ለማፈጠን የሚውል ነው።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ከፀደቀው 14 ቢሊየን ብር ውስጥ 1 ቢሊየኑ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እና 500 ሚሊየን ብር የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ለማሳደግ እንዲሁም 300 ሚሊየን ብር ለዲጂታል ቴሌቪዥን ማስፋፊያ መሳሪያ ግዥ እና ቀሪ ክፍያዎች የሚውል መሆኑም ተገልጿል።
እንዲሁም 5 ቢሊየን ብር በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እና ለማቋቋም ሲውል፤ ቀሪው 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ደግሞ በ2010 በጀት ዓመት ለተቀመጡ የፕሮግራም በጀት ግቦች ለማሳካት እና እጥረት ያጋጠማቸውን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን ፋይናንስ ለማድረግ በመጠባበቂያ የተያዘ ነው።
በጀቱ የሚሸፈነው ከታክስ እና ከካፒታል ገቢዎች በሚገኝ 14 ቢሊየን ብር ሲሆን ከታክስ ገቢ ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከምን ተከትሎ ባንኮች ባገኙት ንፋስ አመጣሽ ገቢ ላይ ከተጣለ ግብር 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከካፒታል ገቢ ደግሞ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ 9 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንደሚገኝ ከተካሄደው ምርመራ መገንዘብ መቻሉን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

Share.

About Author

Leave A Reply