ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የድንጋይ መሣሪያ ተገኘ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የድንጋይ መሣሪያ በአፋር ክልል መገኘቱን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሀ ትናንት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ እስካሁን የተገኙት የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መሣሪያዎች ከሁለት ነጥብ 55 እስከ ሁለት ነጥብ 58 ዕድሜ የነበራቸው ናቸው። አሁን የተገኘው ግን ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ ነው፡ ፡ ከዚህ በፊት ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የድንጋይ መሣሪያ በኬንያ የተገኘ ቢሆንም የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው እንደነበር ማረጋገጫ አልነበረም።

ጥንታዊ የድንጋይ መሣሪያ ለማግኘት በሚደረገው ጥናት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በመሳተፋቸው የእውቀት ሽግግር ሲደረግ ቆይታል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር አመጣጥን በተመለከተ በአይነትም በብዛትም በርካታ ቅሪተ አካል የተገኙባት በመሆኗ፣ እንዲሁም ከዚህ በፊትም ሌላ የድንጋይ መሣሪያ በመገኘቱ ሀገሪቱ ለሳይንስ የምታበረክተውን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

እነዚህ ግኝቶች ለዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ካለቸው ጠቀሜታ ባለፈ አካባቢውን ለኢትዮጵያውያንና ለቀሪው ዓለም እንደ መስህብ በመጠቀም የገቢ ምንጭ ማግኛ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የጥናቱ አስተባባሪ የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዴቪድ ብራውን በበኩላቸው በቅርቡ የተገኙት ጥናታዊ የድንጋይ መሣሪያዎች የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የቺምባዚና የዝንጀሮ ዝርያዎችም ይጠቀሙ እንደነበር ያሳያል ብለዋል። በዚህም የትኛው በሰው የትኛው በእንስሳቱ አገልግሎት ላይ ይውል እንደነበር ለመለየት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት አሁን በተገኙት የድንጋይ መሣሪያዎች ላይ በተደረገ ጥናት መሣሪያዎቹ በአሠራር ጥበባቸው፤ በቅርፅ፤ ቴክኖሎጂና መጠናቸው ሹልና ትናንሽ መሆናቸው የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው እንደነበር ያመላክታሉ ሲሉ አብራርተዋል። በአካባቢው በርካታ ቅርሶች መኖራቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ ያሉት ዶክተር ዴቪድ፣ አሁን የተገኙትን ለምን ይጠቀሙባቸው እንደነበርና ሌሎችም ጥናቶች በቀጣይ የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሰው ልጅ ስልታዊ በሆነ መልኩ የድንጋይ መሣሪያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሠርቶ መጠቀም የጀመረው የዛሬ 2 ነጥብ 28 እና 2 ነጥብ 55 ሚሊዮን ዓመት ገደማ ነበር። አሁን ይፋ የተደረገውና በአሜሪካውያንና በኢትዮጵያውያን አርኪዮሎጂስቶች በአፋር ክልል ሌዲ ገራሩ ልዩ ስሙ በኮል ዶራ በተባለ አካባቢ በተካሄደ አሰሳና ቁፋሮ የተገኘው የድንጋይ መሣሪያ ግን የሰው ልጅ የድንጋይ መሣሪያን መጠቀም የጀመረው ከ50 ሺ እስከ 100 ሺ ዓመት አስቀድሞ ነበር።

አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011

Share.

About Author

Leave A Reply