ሁለት እምነቶችን በአንድ ጣራ ለአስርታት ያሳደሩ ጥንዶች

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኮምቦልቻዎቹ ጥንዶች ሶፍያ ሰይድ እና ወንድሙ ነጋ የተገናኙት በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጨረሻ ነው። ሁለቱም ገራገር ተማሪዎች ሳሉ።

“መንገድ ላይ ከጓደኞቼ ጋር የእግር ጉዞ እያደረገን እያለ ነው ያየኋት። እንዳየኋት ወደድኳት” ይላል ወንድሙ ሁለት አስርት ዓመታት የተሻገረውን የአብሮነት ጥንስስ ሲተርክ።

መተያየት ወደትውውቅ፥ እርሱም ወደ ፍቅር ግንኙነት ሲያድግ ጊዜ አልፈጀበትም። ለጥቆም ትዳር መጣ። ልጆች ተከታተሉ። ሶፍያ የእስልምና እምነቷን እንደያዘች፥ ወንድሙም ከክርስትና የኃይማኖት ጎዳና ፈቀቅ ሳይል።

“መጀመሪያ ስንገናኝ የኃይማኖታችን መለያየት ብዙም ችግር ሆኖ አልታየኝም” ትላለች ሶፍያ። “ልጅነትም ስለነበረ ስለዚህ ጉዳይ አጥብቄም አላሰብኩበትም።”
ከዚህም ባሻገር ግን የኃይማኖት ልዩነት በትዳር ለመጣመር ደንቃራ ላለመሆኑ በዙሪያቸው ሲያዩት የኖሩት እውነታ መተማመን ፈጥሮባቸውም ይሆናል።

ኮምቦልቻ በምትገኝበት የደቡብ ወሎ ዞን ከሁለት የተለያዩ ኃይማኖቶች የመጡ ጥንዶች መሥርተዋቸው ለረጅም ዘመናት የዘለቁ ትዳሮችን ማግኘት እንግዳ አይደለም።

ወላጅ፥ አያት፥ ቅድመ አያቶቻቸውን ሲቆጥሩ የተለያዩ ኃይማኖቶች መነሻዎች ያሏቸውም ጥቂቶች አይደሉም።

ብዙ ጊዜ ግን በጋብቻ ማግስት ባል የሚስትን እምነት ወይንም በግልባጩ ሚስት የባልን ኃይማኖት ተቀብለው አዲስ የሚመሠረተው ቤተሰብ ተመሳሳይ እምነት ሲኖረው ይስተዋላል።

ሶፍያ እና ወንድሙም በትዳራቸው የማለዳ ወራት የኋላ ኋላ አንዳቸው ወደሌላኛቸው ኃይማኖት እንደሚያመሩ ቃል ተገባብተው ነበር።

ይሁንና ከሃያ አመታት በኋላ እርሷ ከመስጂድ እርሱ ከቤተ ክርስትያን ደጆች ሳይነጣጠሉ አሉ። “አምላክ ባለው ጊዜ ይሆናል” ይህንን አስመልክቶ ሁለቱም የሚሰጡት ማብራሪያ ነው።

ከወዳጆች፥ ከጎረቤቶች እንዲሁ ከዘመዶች ግን የ’ለምን አንድ አትሆኑም?’ ጥያቄዎች ደጋግመው መምጣታቸው አልቀረም።

BBC

Share.

About Author

Leave A Reply