ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግ የፖለቲካ አመለካከት ጎደሎነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአንፃራዊ አነጋገር ከሩብ ምዕተ ዓመቱ የህወሃት/ኢህአዴግ ፈፅሞ የተለየ የፖለቲካ ቋንቋ እየሰማንና እንዲሁም አንድአንድ ተግባራዊ እርምጃዎችን እየታዘብን ባለንበት በአሁኑ ወቅት የየፌስ ቡኩ ጫፍ የረገጡ የድጋፍና የተቃውሞው አስተያየቶችን ፣ ጨርሶ ስሜት እማይሰጡ ብሽሽቆችንና እና  የስድብ እሽኮለሌዎችንም እየታዘብን ነው ።

በሌላ በኩል ግን በየአቅጣጫውና በየማህበረሰብ ክፍሉ የሚደረጉና በአንፃራዊ አነጋገር ሃላፊነትንና አስተዋይነትን የሚያንፀባርቁ ሂሳዊ የሃሳብ ልውውጦችና አስተያየቶች የሚያበረታቱና ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውንም እያስተዋልን ነው ። እንዲህ አይነቶቹ   የሃሳብና የአመለካከት መስተጋብሮች የተሻለ መልክ (አቀራረብ) እና ይዘት እየያዙ ወደ ምንፈልገው የምር ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ለመሸጋገር እንዲያስችሉን ለማድረግ ያለብን ፈተና (challenge) ግን ቀላል አለመሆኑን ከምር ልብ ማለት ያስፈልጋል ። ።

 

የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ደረጃው ይለያይ እንጅ በየትኛውም የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ጫፍ የረገጡ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ይኖራሉ ። ከቁጥጥር ውጭና ከህግ በላይ ሆነው በማህበረሰብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ እንጅ ጨርሶ ማጥፋት አይቻልም ። በተለይም በእንደኛ አይነቱ የሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን የማጣጣም እድል ኖሮት በማያውቅ ብቻ ሳይሆን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ በጎሳና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የጥላቻ ፣ የመለያየትና የመጠፋፋት አጀንዳና ፖሊሲ ሲተገበርበት በኖረ   ማህበረሰብ ውስጥ ጫፍ የሚረግጡትን ጨምሮ ብዙ አይነት  አመለካከቶችና አስተሳሰቦች  ቢኖሩ ከቶ የሚገርም አይደለም ።

እንዲህ አይነት አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ከምር በመደማመጥ ፣ በመረዳት ፣ በጉዳዩ (issue) ላይ ብቻ በማተኮር ፣ ከደምሳሳ ፖለቲካዊ ፍረጃ በመቆጠብ ፣ የሂሳችን ግብ ግለሰብን ወይም ቡድንን በመጥላትና በመውደድ ላይ እንዳይሆን በማድረግ፣ ስሜታዊነትን በምክንያታዊነት በማረቅ ፣ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታና ፖለቲከኞችን እኔ በአየሁበት እይታ ካላያችሁልኝ ከሚል አባዜ በመውጣት ፣ ወዘተ የማስተናገዱ ፈቃደኝነትና ችሎታ አሁንም በእጅጉ እየተፈታተነን ያለ ክፉ የፖለቲካ ደዌ ነውና ብርቱ ትኩረት ይጠይቃል።

ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ፦

  • የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከጥቅም መጓደል ሥጋት ፣ ከጭፍን የተቃሞ መንፈስ እና ከመረዳት አቅም እጦት የሚነሱ አመለካከቶች የማይጠበቁ አይደሉም።
  • በተቃራኒው ደግሞ ከግል ወይም ከቡደነ ጥቅም ጉጉት ፣ ከጭፍንና ስሜታዊነት ድጋፍ ፣ እና ሂሳዊ (critical) ለመሆን ካለመፈልግ ወይም ካለመቻል የሚነሱ አመለካከቶች ወይም ትችቶች የመኖራቸው ጉዳይም የማይጠበቅ አይደለም ።
  • የሁለቱንም አመለካከቶች ወደመሃል አምጥቶ በአንፃራዊ መልኩ ሚዛናዊ ነው የሚለውን አመለካከት የሚያራምድ ወገን የመኖሩ ጉዳይ ደግሞ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን እንዲጎለብት የተለየ ትኩረት ሊሰጠውና መበረታታት የሚገባው ነው ።  ትልቁ ችግር የሚመነጨው ይህን ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብር በአግባቡ በማስተናገድ አፍራሹን እየቀነሱ ገንቢውን ለማጎልበት ካለመፈለግ ወይም ካለመቻል ነው።

 

ለሁሉም  አይነት አመለካከቶች ወይም አስተሳሰቦች መንሸራሽሪያውን አውድ  ክፍት አድርገን በአግባቡና በገንቢነት ለማስተናገድ ፈቃደኘነቱ ፣ በራስመተማመኑና ጥበቡ ከጎደለን የምንመኘው የሥርዓት ለውጥ እንደምንም ቢሳካ እንኳ ስኬቱን ፖለቲከኞች በመጡና በሄዱ ቁጥር የማይናወጥ ሥርዓትአድርጎ ለመቀጠል በእጅጉ እንቸገራለን ። በእኔ ግንዛቤ ለምንፈልገው ለውጥ ሥጋት ናቸው ከምንላቸው ወገኖች (ከህወሃትና የትሮይ ፈረሶቹ – TPLF and its Trojan Horses) ባልተናነሰ የሚጎዳን በዚህ ረገድ ያለብን ብርቱ ድህነት ነው ባይ ነኝ ። ምክንያቱም ሥጋት ናቸው የምንላቸው ወገኖች  ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የግፍ ቀንበራቸውን ጭነውብን የቆዩትና አሁንም እንደሥርዓት የቀጠሉት የነሱ የሴራ ፖለቲካ እንዳለ ሆኖ በእኛው በራሳችን እጅግ አሳፋሪ ድክመት (ውድቀት) አለመሆኑን የሚያሳምን ምክንያት ጨርሶ የለንም ። ለዚህ ነው አሁንም ለሁሉምና ለማነኛውም መሰናክል (ጥፋት)  ሃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ከእራሳችን እያሸሸን ህወሃትና ህወሃት ብቻ ነው የሚለው የፖለቲካ አስተሳሰባችን ጎደሎ (ሽባ) ነው ማለት ትክክል የሚሆነው ።

ለረጅም ጊዜ በተለይ ደግሞ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተካሄደውን  የህዝብን የነፃነትና የፍትህ ትግል ተከትሎ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነቱንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ሰባ ዘጠኝ ቀናት ተቆጠሩ ። በነዚህ ቀናት ውስጥ በሥልጣን   እርክክብ እለትና   ከእርክክብ በኋላ በአዲስ አበባና  በተለያዩ ክልሎች የተደረጉ ንግግሮች በአጠቃላይና በንግግርነታቸው ሲታዩ በእጅጉ አበረታች ናቸው ። ተገቢው አድናቆትም ይገባቸዋል ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዓመታት የተጫነበት የመከራና የውርደት ቀንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተሰበረ ፈፅሞ ወደ ኋላ እንደማይመለስ  ተገንዝበው ከፖለቲካው ቋንቋ አጠቃቀም  ጀምሮ አንዳንድ አበረታችና የለውጥ ሂደት አመላካች እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈቃደኝነትና አንፃራዊ ድፍረት ካሳዩ ጥቂት  የኢህአዴግ አባላት (ባለሥልጣናት) ግንባር ቀደም ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ ይበል ያሰኛል ። ይህን ሃቅ ማጣጣል በራሱ ወይ ከድንቁርና ፖለቲካ የሚመጣ ነው ወይም ደግሞ እኔ ያላደረግሁት(የሌለሁበት)ሁሉ አይጥመኝም የሚል ስሜት የለሽ የፖለቲካ ሰበእና ነው ።

ንግግሮቹ   በንግግርነታቸው የህወሃት/ኢህአዴግ   መሪዎችና ተከታዮቻቸው (ተናጋሪውን/ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ) ለሩብ ምዕተ ዓመት ባልተገራ የባለጌ አንደበታቸው ሲተፉብን በነበረው ርካሽና በጉእጅ መርኛ በሆነ የፖለቲካ ቋንቋ ከተፀፀተ አእምሮና አንደበት የመነጩ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የንግግሮቹን እውነትነት በተግባራዊ ሂደት ለማረጋገጥ እንዲቻል እድል የመስጠቱ (the benefit of the doubt) አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ።

አዎ! ንግግሮቹ በንግግርነታቸው ሲታዩ ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቅንበትንና መልካም ሥነ ምግባር ሳይሆን ብልግና ፣ ትህትና ሳይሆን እብሪት ፣ አዋቂነት ሳይሆን ደደብነት ፣ አብሮነት ሳይሆን መለያየት ፣ ይቅር ባይነት ሳይሆን ቂመኝነት ፣ አክብሮት ሳይሆን ውርደት ፣ ርህራሄ ሳይሆን ጭካኔ ፣ እውነት ሳይሆን ሃሰት ፣ መታመን ሳይሆን ክህደት ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን መንደርተኝነትና ጎሰኝነት ሲሰበክበት የነበረውን የፖለቲካ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ አኳኋን ቀይረውታል ።የቋንቋ (የቃላት) ለውጥ ወደ ተግባራዊ ለውጥ መሸጋገር ካልቻለ  ግን ነገራችን ሁሉ “አልሸሹም ዘወር አሉ” ብቻ ሳይሆን ከዚያም የከፋ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ልብ አለማለት ግን አደገኛ የፖለቲካ ድንቁርና ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግሮቻቸው (ዲስኩሮቻቸው) የህወሃት/ኢህአዴግ የግፍ አገዛዝ በቃኝ ብሎ በተነሳ ህዝባዊ እምቢተኝነት እና እንደለመድኩት እያፈንኩና እየገደልኩም ቢሆን እገዛለሁ በሚል የክፉ ፖለቲካ ልክፍት በተለከፈው ድርጅታቸው (ህወሃት/ኢህአዴግ) መካከል የነበረውን እጅግ የከረረ   ውጥረት ለማርገብ (lessening the tension) መቻላቸውም እውነት ነው ። ይህ ውጥረት የማርገብ (አደገኛ የእሳት ነበልባልን የማጥፋት) ፖለቲካ ወደ እውነተኛ መረጋጋት (real sense of stability) የሚሸጋገርበት ሁኔታ በተገቢው የጊዜ ሰሌዳ እና ታስቦ ፣ ተጠንቶና ታቅዶ በሚሠራ ሁለገብ ሥራ እስካልተመራ ድረስ መልሶ ሊቀጣጠል የሚችለውን የተዳፈነ እሳት ለማጥፋጥ ይቅርና ለመከላከልም ይቸግራል ።

ሃቁን እንነጋገር ካልን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ውጥረት ማርገብን እንጅ መረጋጋትን (stability) አላመጡም ። ምክንያቱም ስለ መረጋጋት (stability) ስንነጋገር ከገባንበት እጅግ አስጨናቂ ሁኔታ ጊዜያዊ እፎይታ ከማግኘት አልፎ የሚሄድ የአእምሮ  ፣  የአካልና የኑሮ ደህንነትን እና የነገ ብሩህ ተስፋን  ትርጉም የተሸከመ ግዙፍና ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ  ስለመሆኑ ነው የምንነጋገረው ።  እናም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አበረታች ንግግሮች በወቅቱ የነበረውን የከረረ ውጥረት አረገቡ እንጅ መረጋጋትን ( stability ) ገና አላመጡም። አሁንኑ ይምጣ እያልኩ አይደለም ። እያልኩ ያለሁት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥረት ለማሞገስና ለማበረታታት ፅንሰ ሃሳቦችን ( ቃላትን) ከመሬት ላይ ካለው ወይም እየሆነ ካለው እውነታ በላይ አምጥቀን ወይም አጋነን መጠቀም እራሳችን ማታልል ነውና ልብ ማለት አይከፋም ነው ።

በመሠረቱ እውነተኛ መረጋጋት በበሰበሰና በህዝብ ጨርሶ በተጠላ የፖለቲካ ሥርዓት ሥር ተሁኖ  ስሜትን የሚማርኩሩና ተስፈኝነትን የሚሰብኩ ንግግሮችን  አብዝቶ በማስተጋባት  የሚቻል ጉዳይ አይደለም ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሥር ነቀል ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ዝግጁ ናቸው ወይ ? ለሚለው በየራሳችን ስሜትና ግምት ካልሆነ በስተቀር እስካሁን ግልፅና የማያሻማ ምላሺ የለም ። እንደሚኖር ተስፋ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መጠየቅና ተገቢውን ግፊት ማድረግ ግድ የሚለንም ለዚህ ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምን ሲባል ይተቻሉ ወይም ለምን ግፊት ይደረግባቸዋል?” የሚለው አስተሳሰብ በእጅጉ ስንካላ (lousy /clumsy) ነው ማለት ትክክል የሚሆነውም ለዚህ ነው ። ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ የማድረጉ የፖለቲካ አስተሳሰብ በራሱ ጊዜያዊ ወይም የአጭር ጊዜ የስሜት እርካታ ይሰጥ እንደሆነ እንጅ የምንመኘውን ለውጥ እውን ለማድረግ አያስችለንም።

እርግጥ ነው ፤ ክፉ አስተሳሰቦችና ልሳናት ሊያስከትሉ (ሊወልዱ) የሚችሉት ክፉ ንግግሮችን (ቃላትን) ነው። ክፉ ንግግሮች ደግሞ ሊያስከትሉ (ሊወልዱ) የሚችሉት ክፉ ድርጊትን ነው ።  ይህን አጠቃላይ እውነታና ሊያስከትል  የሚችለውን   እጅግ አስከፊ ውጤት  ደግሞ ለሩብ ምዕተ ዓመት በውስጡ ካለፍንበት ከእኛው ከራሳችን በላይ የሚያውቅና የሚያስረዳ ከቶ ሊኖር አይችልም ። ከዚህ አንፃር ይመስለኛል ብዙዎቻችን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ያለምንም ሂሳዊ አቀራረብ (with no critical approach) እና የማገናዘቢያ ጊዜ እንኳ ሳንወስድ አጃኢብ (እፁብ ድንቅ) ከማለት አልፈን እግዚአብሔር ከገዥው ቡድን (ህወሃት/ኢህአዴግ) ውስጥ መልእክተኛውን አስነሳልን የሚል አይነት አንድምታ ያለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የዳዳን (የሞከርነው) ።

እንዲህ አይነቱ ከልክ ያለፈ ስሜታዊነት የተጫነው አቀራረብና ድምዳሜ ለሩብ ምዕተ ዓመት ክፉዎቹና ደንቆሮ ገዥዎቻችን መልካም ንግግርን (ቃላትን) እንኳ እንዳይሰማ አድርገው ሲገዙት ከነበረው የዋህ የአገሬ  ሰው የሚጠበቅ አይደለም የሚል የግብዝነት (የደንቁርና) አስተሳሰብ የለኝም ።  አዎ! በጎ መስማት ብርቅዬ ሆኖበት ዘወትር ሲተኛና ከመኝታው ሲነሳ ፈጣሪው ቸር ያሰማው ዘንድ “ቸር አሰማኝ”እያለ ሲማፀን ለኖረ የዋህ የአገሬ ህዝብ የዶ/ር አብይ አህመድ ንግግሮች(ዲስኩሮች/ቃላት) ከሰማይ የወረዱ መስሎ ቢሰማው ጨርሶ የሚገርም አይደለም ።

ለብዙ ዓመታት የተዘፈቅንበት የመከራና የውርደት ሥርዓት  ስፋትና  ጥልቀት የሚነገረንን  የበጎ እና የተስፋ ቃል ሁሉ  ለምን ? እንዴት? እስከመቼ ? ወዴት? ለማን ? በማን ? ከዚያስ? ወዘተ የሚሉ ሂሳዊ ጥያቄዎችን ከምር ሳንጠይቅ ከልክ ባለፈ አድናቆት እንድናምንና እንድንቀበል አድርጎናል ። ይህ አይነቱ በምክንያዊነትና አስተዋይነት (power of reasoning and rationality) ላይ ሳይሆን ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ስሜታዊነት (uncontrollable emotion) ላይ የሚነሳ የፖለቲካ ግንዛቤና አስተሳሰብ ለፖለቲከኞችም ሆነ ለምንመኝው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባት ጨርሶ አይጠቅምም ። እንዲያውም እያሳሳቀ ወደ መጣንበት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ወደ ባሰ አዘቅት ነው ይዞን የሚወርደው ።

ባለሥልጣኖቻችን (ፖለቲከኞቻችን) ለሚያሳዩት በጎ ምግባርና ለሚያስመዘግቡት የሥራ ውጤት እውቅና መስጠትና ማበረታት ያለብንን ያህል የሚጠበቅባቸውን ሆነውና አድርገው መገኘት ሲያቅታቸው ደግሞ በሃላፊነትና በተጠያቂነት እንደሚጠየቁ በቀጥታና በማያወላዳ አኳኋን ማሳወቅ (ማስጠንቀቅ) የግድ ነው።  በአሁኑ ወቅት የሚታየው በዘርና በቋንቋ ላይ የመሠረተ ግጭት ፣ መገዳደል ፣ ንብረት መውደምና መፈናቀል ከሥርዓቱ ጋር የተያያዘ ነውና ዘላቂ መፍትየው ከሥርዓቱ መወገድና አዲስ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት መመሥረት ጋር የተሳሰረ ነው የሚለው እጅግ ግዙፍና ጥልቅ  እውነት ነው ።

አንድንድ ወገኖች ይህ ችግር ሊቀጥል እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም  ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሃላፊነትና በተጠያቂነት መጠየቅ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ታዝቤያለሁ ።

የሃላፊነቱንና የተጠያቂነቱን ሁኔታ (contextን) ባገናዘበ አኳኋን ማቅረብ ወይም መግለፅ ተገቢ ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥርዓቱን ለማስተካከል ከፍተኛ ትግል ላይ ስለሆኑና ችግሩም ከዚህ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ተጠያቂ መደረጋቸው አግባብ አይደለም የሚለው ግን ከሞራልም ፣ ከፖለቲካም እና ከአገር መሪነትም አኳያ እንዴት እንደሚያስኬድ ጨርሶ የሚገባ ወይም ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም ።

ይህ ነው እንግዴህ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የስሜት ፈረስ ስንጋልብ የሚያጋጥመን ችግር ። ይህን ባልንበት ተመልሰን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚያጋጥማቸው እንቅፋት ወይም ድክመት ሃላፊውና ተጠያቂው ህወሃትና ህወሃት  ብቻ  ነው ስንል ከራሳችን ህሊና ጋር ተጋጭተነው እናርፋለን ።    እውነተኛና መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በእውን የምንናፍቅ ከሆነ ይኸ ሁሉንምና ማነኛውንም አይነት ድክመትና ውድቀት በህወሃትና በህወሃት ላይ ብቻ የማሳበቡ የፖለቲካ አስተሳሰብ (አመለካከት) እጅግ ጎደሎ ነውና በቅጡ እንድናስተናገደው የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ግድ ይለናል ።

በአሁኑ ወቅት ከሚስተዋሉት አይነተኛ ድክመቶች አንዱ ይህኑ የፖለቲካ አካሄድ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያለማስተናገድ ችግር ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም የለውጥ ሐዋርያ የሚባለውን ቡድናቸውን መተቸት (ማስጠንቀቅ) የለውጡን እድል እንደማደናቀፍ የመቁጠር የፖለቲካ እንጭጭነትን (political infantile) ተገንዝቦ በወቅቱ ለማረም አለመፈለግ (አለመቻል) እየታጠቡ ጭቃ መሆን ነው ።

ችግሩ ከዚህም ያልፋል ። የጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጥ ሐዋርያ ቡድናቸው ስኬት ወይም ውድቀት በህወሃትና እና በህወሃት አወንታዊ ወይም አሉታዊ ሚና ብቻ እንደሚወሰን የማመንና የትም ቦታና ጊዜ ችግር ወይም ፈተና ባጋጠመ ቁጥር ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ የማድረግና የውግዘት ናዳ የማውረድ የፖለቲካ አባዜ አሳስቦን ተገቢውን እርምት በጊዜ መውሰድ ይኖርብናል ።  የዚህ አይነት ለሁሉምና ለየትኛውም ድክመታችን (ውድቀታችን)  ጣትን ወደ ሌላው የመጠቆምና የመውገዝ ፖለቲካ የለውጥ ሐዋርያ የምንላቸው ፖለቲከኞችን ያባልጋል እንጅ ጨርሶ አያጀግንም ። ” የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ (አደናቀፈኝ)”  እንደተባለው ሁሉ ፖለቲከኞቻችንም እንሠረዋለን ብለው ቃል የገቡትና መሠራት የነበረበት ሳይሰራ (ሳይተገበር) በቀረ ቁጥር “እኛስ ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር ።  የጥፋት መልክተኛው ህወሃት ግን ሊያሠራን  አለቻለም” ሲሉን ” እናንተ እንደ ባለሥልጣንነታችሁ እና  እኛም ደግሞ እንደግለሰብ ፣ እንደ ቡድንና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ ምን እንሠራ ነበር ? እናንተም ሆነ እኛ ለድክመታችን (ለውድቀታችን) እንደየድርሻችን ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ጨርሶ ልንሸሽ አየገባም ፣ አንችልምም “ማለት እስካልቻልን ድረስ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ የሚታሰብ አይደለም።   ይኸ ለራስ ቅጥ ያጣ ድክመት (ውድቀት) ማስተባበያ ሰበብ (execuse) የመፈለጉና ጣት ወደ ሌላው የመቀሰሩ የፖለቲካ ባህልና አስተሳሰብ ጨርሶ ሊወገድ ባይችልም በቅጡ እንዲሆን ማድረግ የግድ ነው። የምንመኘው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከዚህ አይነት ስንኩል (clumsy/lousy) የፖለቲካ ሰብዕና ጋር ጨርሶ አብሮ የሚሄድ ጉዳይ አይደለምና ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን እረክክብ ንግግራቸው ኢትዮጵያ የሚለውን የስም ቃል ስንት ጊዜ እንደ ደጋገሙት ቆጥረን የተሰማንን አድናቆት የመግለፃችን ተገቢነት እንዳለ ሆኖ ይህን ያህል ዝቅጠት ውስጥ ለቆየንበት የሩብ ምዕተ ዓመት የፖለቲካ ሥርዓት ዋናው ተጠያቂ ህወሃት ቢሆንም እኔስ ?  እኛስ ?  ብሎ ራስን አለመፈተሽ ግን ጎደሎ የፖለቲካ ሰብእና ነው ።

አዎ! የፖለቲካ አስተሳሰባችን ደካማነት የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በእጅጉ የተጋነነ የባለሥልጣናት የአደርገዋለሁና የተስፋ ቃል ወደ መሬት ወርዶ የሚጨበጥ ፍሬ መሆን ሲሳነው የራሳችን ውስጠ ህሊና ከምር መፈተሽና ማስተካከል ትተን ሰበብ (execuse) ፍለጋ ወደ ውጭ (ወደ ሌላ አካል) የመዝመት አባዜያችን ነው ። በአሁኑ ወቅት የምንታዘበውና የምናስተውለው ሃቅም የዚሁ አባዜ አካል ነው ። ለእያንዳንዷና ለሁሉም ድክመታችን (ውድቀታችን) ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ እያደረጉ ከራስ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የመሸሸ አባዜ ።

እናም  ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ከእንዲህ አይነቱ ጎደሎ (ልፍስፍስ) የፖለቲካ አሰተሳሰብ (አመለካከት) ሰለባነት ገና ራሱን ነፃ ባላወጣበት አገር    የመማር እድል ጨርሶ ያላገኘውና የዋሁ የአገሬ ህዝብ  ለጠቅላይ ሚኒስትሩ  ያለውን አድናቆት “የፈጣሪ ሥራ ነው” እስከማለት ቢለጥጠው (ቢያጋንነው) ምን ይገርማል ? የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ሙከራ (ጥረት) በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት አጥጋቢ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ “እነዚህ ህወሃቶች አያሠሩትም እንጅ  ‘የምወደው ልጄ እርሱ ነው’ ብሎ ከሰማይ ቃል ሲመጣ ( ሲወርድ) በግልፅ ሰምቻለሁ”  ቢልም  የሚገርም ነገር አይደለም።

ታዲያ የህወሃትን እኩይ አጀንዳና ተግባር  ማውገዝና መታገል እንዳለ ሆኖ ትርጉም ባለው መንገድ ወደ ተሻለ እርምጃና ብሎም  ወደ መሠረታዊ ለውጥ እንዳንሸጋገር ያደረጉንን የራሳችን ድክመቶችና ውድቀቶች በሰለጠነና ተገቢ በሆነ መንገድ ለመረዳትና ትክክለኛውን አቅጣጫ ለማስያዝ መረባረብ ሲገባን ሁሉንም ነገር በህወሃትና እና በህወሃት ላይ ብቻ እየዘፈዘፍን እንዴት አበረታች ነው የምንለውን ፖለቲካዊ አጋጣሚ ከግቡ ማድረስ ይቻለናል ?

ስሚታዊነት በእጅጉ የተጫነውን  የፖለቲካ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን በገሃዱ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታና በምናያቸው አወንታዊ ክስተቶች ምንነትና ወዴትነት ላይ በተመሠረተ ግንዛቤ ፣ አረዳድ፣ ትንታኔና የመፍትሄ ሃሳብ አቀራረብ በማስተናገድ ትክክለኛውን አቅጣጫ ማስያዝ ካልቻልን  ነገ በአስከፊነት ገፅታው ወደ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንደማንመለስ ማረጋገጫ የለንም ።

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ከጉልህ የፖለቲካችን ፈተናዎች አንዱ በአንፃራዊ  አመለካከት አቅሙ (ችሎታው) ያለው  የተማረው የህብረተሰብ ክፍል  በክስተቶች አሉታዊነት ከመቆዘም እና በአወንታዊነታቸው ደግም ቅጥ ያጣ ሙገሳ ከመደርደር ያለፈ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው ሚና ለመጫዎት መቸገሩ ነው ። ለሩብ ምዕተ ዓመት ህወሃትን ከማብጠልጠል ወይም ከዳር ቆሞ ከመመልከት አልፎ ድርጊታዊ ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማድረግና የራሱን የውጤት አሻራ ማስመዝገብ ተስኖት የኖረው አብዛኛው ፊደል የቆጠረ (የተማረው) የአገሬ  የህብረተሰብ ክፍል አሁንም ከዚሁ በክስተቶች ከመነዳት  ልፍስፍስ ( lousy and clumsy ) የፖልቲካ  አስተሳሰብ  ለመውጣት እንደተቸገረ መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም ። በትምህርት ደረጃ ፣ በእድሜና በተሞክሮ አንቱ የሚባሉ (ሊባሉ የሚችሉ) ሲጨመሩበት ደግሞ የበለጠ አስቀያሚ ይሆናል ።

አሁንም ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው ወገኔ (አብዛኛው)  ለጠቅላይ ሚኒስትሩ  ስኬት ወይም ውድቀት ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ የማድረግ የፖለቲካ አባዜ ውስጥ ይባዝናል ። ምሥጋናንና አድናቆቱትን ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን በሚያስገነዝብ ገንቢ ሂሳዊ አቀራረብ ሳይሆን የውዳሴ ዶ/ር አብይ አህመድ ስንክሳር ማዥጎድጎዱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም  ሆነ ለምንመኘው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ብዙም ፋይዳ የለውም ።  እኔ እንደግለሰብ ፣ እኛ እንደ ዜጋ ፣ እኛ እንደ  ቡድንና እና ባጠቃላይ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚፈልግ ማህበረሰብ ምን አደረግሁ (አደረግን)? እና ምንስ ማድረግ አለብኝ (አለብን)? ብሎ ራስን መጠየቅን እየሸሹ የድክመት (የውድቀት) ሁሉ ምክንያት ህወሃትና ህወሃት ብቻ ከሚል የፖለቲካ  አስተሳሰብ  አባዜ ሳንወጣ ወደ አዲስና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር የሚቻል አይሆንም ። እንደምንም ብለን  መሻገር  ብንችል እንኳን በዚህ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ልንገነባውና ልናጎለብተው ስለማይቻለን መልሰን እንደማናበላሸው ማስተማመኛ የለንም።  ለዚህ ነው ፈደል የቆጠረው (የተማረው) የህብረተሰብ ክፍል ትልቅና ፈታኝ ሥራ (ድርሻ) አለበትና እሱን በሚመጥን ደረጃ ሚና ይኑረው ማለት ትክክል የሚሆነው ።

 

የሰው ልጅ በማህበራዊና ፖለቲካዊ እንስሳነት መኖር ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ እውን ከሆነውና ከዚሁ የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር ተሞክሮ የተቀዳው “ድርጊት ከቃላት በላይ ይናገራል (action speaks louder than words; action speaks volumes)” የሚለው ሃይለ ቃል ብቸኛው  የፖለቲካችን እርምጃ መለኪያ ነው ። መለኪያነቱ   ደግሞ ፖለቲከኞች (ባለሥልጣናት) እየመጠኑ (እየሸራረፉ) በሚሰጡን የጥገና (የተሃድሶ) ተውኔት ከቶ ሊሆን አይገባውም ። እንዲሆንም  ፈፅሞ መፍቀድም የለብንም ። ጥያቄው ህወሃትን ወይም አንድ ወይ ሁለት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን የማስወገድ ወይም በሥልጣን የማቆየት ጉዳይም አይደለም ። ኢህአዴግ ተዋህዶና ኢትዮጵያዊ ስያሜ ተላብሶ እንደ አዲስ  የቤተ መንግሥት ባለጫጉላ እንዲሰየምም በፍፁም አይደለም ።

የማያወላዳው የህዝብ ጥያቄ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የመከራና የውርደት መፈልፈያና ማከፋፈያ የሆነውና ከጥፋት ተልኮው ከምር ለመማርና ለመመለስ ፈፅሞ የሞራልና የፖለቲካ ብቃት የሌለው የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዓት እንደሥርዓት የሚቀጥልበት ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደን መንገድ በሁሉም አቀፍ ተሳትፎ ይከፈት ነው 

ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከትናንት በፊት ለይስሙላ በሚሰየመው ፓርላማ (አስቀያሚ የፖለቲካ አሻንጉሊት)  ፊት ቀርበው “ህገ መንግሥትን ፋይዳ አሳጥተን ሰውን ያሰቃየንና ያጉላላን እኛው ስለሆን ስለሽብርተኝነት ስንንጋገር እኛም ከደሙ ንፁህ አይደለንም” እስከ ማለት ከሄዱ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ  ተቀዋሚ  የፖለቲካ ድርጅቶች/ቡድኖች ያለምንም የህወሃት/ኢህአዴግ (የድርጅታቸው)እና የመንግታቸው ቅድመ ሁኔታ በጠረጴዛ ዙሪያ ተገናኝተው የሚነጋገሩበትን ሁኔታ የሚያሳይ   የጊዜ ሰሌዳና የቅድመ ድርድር ሃሳብ (proposal) ይፋ ማድረግ ወይም ቢያንስ ይፋ እንደሚያደርጉ መግለፅ ለምን እንዳልፈቀዱ ወይም እንዳልቻሉ ሊጠየቁና መልስ ሊሰጡ የሚገባቸው እራሳቸው ናቸው ። አዎ!ጥፉትን ማመን ከሚደነቅ የፖለቲካ ሰብዕና የሚመጣ ደፋርነት ነው ። ይህን ያህል በግልፅና በአደባባይ የተናዘዝነውን እጅግ መሪር እውነታ እንድንፈፅም ያደረገንን ሥርዓተ አስተሳሰብና ድርጊት ዳግም እንዳይመለስ ከነሸንኮፉ ቀብሮ በቅርፁም ሆነ በይዘቱ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሚሆንበትን መንገድ ጊዜ ሳያባክኑ ማመቻቸት ደግሞ የደፋርነት (የጅግነት) ሁሉ ቁንጮ ነው ።   የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ንግግር ከዚህ እይታ (context) አኳያ ማየቱ በንግግሩ የመገረማችን ስሜት ተግባራዊ መሆን ባለበት ምክንያታዊነት ይበልጥ የተሟላ ያደርገዋል።

አዎ ! በንግግር (በዲስኩር) ደረጃ እንደ ክርስቶስ “እመኑኝ” የሚለው በገሃዱ የፖለቲካ ዓለም (ጨዋታ) ሊሠራ የሚችል ነገር አይደለምና አሁንም ይህ የሁሉም ጥያቄዎች ማዕከል (እናት) የሆነው በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወደ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ የመዝለቁ ራዕይ እውን ይሆን ዘንድ የመሪነት አርበኝነትን የግድ ይላል። ከዚህ ቁልፍ ጥያቄ ባነሰ የሚደረግ የተሃድሶ ልግሥና ብዙም ሳይቆይ ተኖ የሚጠፋ ጊዜያዊ ሆይ ሆይታ ካልሆነ በስተቀር የሚያስገኘው ከበሬታ ጨርሶ የለም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ለማድረግ  የሚያስችል የሞራልና የፖለቲካ ድፍረቱና ጥበቡ እስከሌላቸው ድረስ ጥረታቸው ሁሉ ከምንጊዜው የተሻለ በሚሉት የድርጅታቸውና የመንግሥታቸው የጭንቅ ማስታገሻ ለውጥ (ተሃድሶ) ዙሪያ ከመሽከረከር ጨርሶ አያልፉም። እናም ለዚህ ነው ለሁሉምና ለማነኛውም ድክመት (ውድቀት) በህወሃትና በህወሃት ላይ ብቻ ማሳበቡ ትልቅ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጎደሎነት አለው ማለት ትክክል የሚሆነው።

በአሁኑ ወቅት  እየሰማነውና እየታዘብነው ያለው በአንድ በኩል የለውጥ ሃይል (ምን አይነት ለውጥ ? የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ) የሚባለውን ቡድን ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ነፃ የሆነ ያህል ሙገሳውን የምናዥጎድጎዱለት እና በሌላ በኩል ደግሞ የሁሉም ድክመት (ውድቀት) ምክንያት ህወሃትና ህወሃት ብቻ እንደሆነ አድርገን ውግዘቱን የምናወርድበት የፖለቲካ ጎድሎነት የሚመነጨው ይህኑ መሠረታዊ ጥያቄ (ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ)   በፍፁም የማይናወጥ የስኬታችን ወይም የውድቀታችን ማመሳከሪያ (refernce) ማድረጉን አውቀን ወይም ሳናውቅ ወደ ጎን ከመግፋታችን ነው።

በእጅጉ ማስተዋልንና አቅዶ መራመድን የሚጠይቀው ፈተና (challenge) የሚጀምረው ገደብ የለሽ የተስፋ ቃሎቻችንን (ንግግሮቻችንን) ለምን? እንዴት ?መቼ ?  ከየት ? ወዴት?   እስከየት? ለማን ? ከማን ጋር?  ወዘተ  ብለን ከምር ራሳችን ደጋግመን ከመጠየቅ ነው ። ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድና ለመመለስ ስንችል ነው  እጅግ አማላይ ከሆነው የቃላት ድርድራችን ይልቅ ጉልህ ትርጉም ያላቸው ድርጊቶቻችን ብዙ ሳንናገር ስለእኛ ስኬታማነት እንዲመሰክሩ ማድረግ የምንችለው ። ይህን ሆኖና አድርጎ መገኘት ማጣፊያው ሲያጥረን “ህወሃቶች በአካልም ባይችሉ በመንፈስ ሁሉን ነገር በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ጥረታችን እንደፈለግነው ሊሳካ አልቻለም” የሚለው እጅግ የተዘወተረ ሰበብ ፍለጋ እራሳችን አሽመድምዶ ሳይጥለን ከቅርቡ ተጋፍጠን በቅጡ ልናደርገው የገባል ።

ለመሆኑ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ገዥዎች ይተፉት የነበረውን የክፋትና የጥፋት ቋንቋ (ንግግር) እና ያስከተለውን ግዙፍና ጥልቅ አገራዊ ውርደትና ጉዳት አስቁሞ በበጎና ገንቢ ሥርዓተ ማህበረሰብ ለመተካት ያለመቻላችን  ውድቀት ተጠያቂነት የህወሃትና እና የህወሃት ብቻ ነበር (ነው) እንዴ ?  የህወሃት አፈጣጠርና ዓላማ ግልፅና ግልፅ አልነበረም (አይደለም) እንዴ? የህወሃትን ሃላፊነትና ተጠያቂነት ገና ዛሬ ነው እንዴ ግልፅ የሆነልን ?  ህወሃት አሁንም ቢቻል በተወሰነ ደረጃ ተፅዕኖውን ላለማጣት ካልሆነም ህልውናውን ለማስቀጠል የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግ ምን ይገርማልና ነው የዜና ትንታኔያችን ፣  ውይይታችን ፣ ትርክታችን ፣ ፕሮፓጋንዳችን ፣ ውግዘታችን ፣ ወዘተ ሁሉ የራሳችን ሃላፊነትና ተጠያቂነነት እስከምንረሳ ድረስ በህወሃት እና በህወሃት ላይ ብቻ የሆነው ?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምንፈልገውን ነገር የማድረጋቸውን ዜና ስንሰማ  “ህወሃትን ተጋፈጡት (እውነትም የለውጥ ሃይል መሪ )” በማለት በስሜትእየዋኘን እና  በሌላ በኩል ደግሞ  በህወሃት አስገዳጅነት ብቻ ሳይሆን በሚመሩት ግንባር (ኢህአዴግ) አሠራር መሠረት ያልጠበቅነውን (ያልፈለግነውን)ሲያደርጉ  “የህወሃት ሴራ ነው እንጅ እርሳቸው አያደርጉትም” የሚል እጅግ ቅጥ አምባሩ  የጠፋው (disoriented)  የፖለቲካ አስተሳሰብ የሙጥኝብለን እንዴት ነው የምንመኘው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን የሚሆነው?

የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ታሪካዊ” ንግግር ተግባራዊ እንዳይሆን የማድረጉን  ሃላፊነትና ተጠያቂነት በህወሃትና ህወሃት ላይ ብቻ የመዘፍዘፍ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድስ የት ያደርሳናል ?

በሚከተሉት ነጥቦቼን (ምሳሌዎችን) በመጠቀም የበልጥ ግልፅ ልሁን ፦

  • ህወሃትጠፍጥፎ ከሠራቸውና  በኢህአዴግ ስም ለትሮይ ፈረስነት (the Trojan horse) ካዘጋጃቸው   ከሥርስቱ   አባል አገለጋይ   የብሔረሰብ ፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበላይነት የሚመሩት ኦህዴድ (የአሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት)     ሃላፊነትና ተጠያቂነት የለበትም እንዴ? እውን ኢትዮጵያ አቀፍ ወደ  ሆነና የብሔረሰቦችን መብት ወደ ሚያከብር  መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እንደሚናፍቅ የለውጥ ሃይል በሙሉ ፍላጎቱና ሃይሉ እየተንቀሳቀሰ ነው እንዴ  ? ወይንስ  በቄሮ አጋዥነት የህወሃትን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ እወክለዋለሁ ከሚለው የኦሮሚያ ክልል ጫንቃ ላይ በማስነሳት የክልሉ አራጊና ፈጣሪ መሆንና  ይህ “ትሩፋት” ለሌሎችም የክልል ገዥዎችና ካድሬዎች እንዲተርፍ ለማስቻል ነው  ?  ጎበዝ ! እንደዚህ በግልፅነትና  በቅንነት ተወያይተን ለመተማመን (ለመግባባት) የፖለቲካውና የሞራሉ ድፍረት የግድ ከሚለን ወቅት ላይ መሆናችን ለመረዳት ለብዙ ክርክር የሚጋብዘን አይመስለኝም ።  የሁሉም ችግራችን ምንጭና  ባለቤት ህወሃትና ህወሃት ብቻ ነው የሚለው እጅግ ደምሳሳ የፖለቲካ አስተሳሰብ  ግን በራሱ  የትም አያደርሰንም ።
  • የለውጥሃይሉ አካል እያልን የምናሞካሸው ብአዴኑ (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በዚህ ከባድ መስዋትነት በጠየቀው ህዝባዊ  እምቢተኝነት ትግል  ውስጥ ከኦህዴድ (የለማ ቡድ/የለውጥ ሃይል )ብለን ከምንጠራው ጋር ተደርቦ እኔም አለሁበት ከሚል የፖለቲካ ሽር ጉድ ያለፈ በትክክለኛ ትርጓሜው የለውጥ ሃይል አካል የሚያሰኝ የፖለቲካ ሥራ ሠርቷል ማለት ራስን መዋሸት አይሆንም እንዴ?  አማሮች አማራ በመሆናቸው ብቻ በርቀት ካሉ ክልሎች ብቻ ሳይሆን እዚያው ዋና ቢሮው  ከሚገኝበት ከተማ ብዙም ከማይርቀው ከቤንሻንጉል – ጉሙዝ  (የቀድሞው አንዱ የጎጃም አውራጃ -መተከል  ) መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውን ሲያጡ ምንድን ነው ያደረገው? የንቅናቄ ተብየው ባለሥልጣናት ለነፃነትና ለፍትህ የጮሁ አያሌ ንፁሃን ዜጎች (የክልሉ ኢትዮጵያውያን) ለጠላት ሊውል በሚገባው ጥይት ህይወታቸው ሲቀጠፍ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ለቅሶ ከመድረስና አለቀሱተብሎ ዜና ከማስነገር ያለፈ ምን አደረጉ ? የሚኖርበት ክልል በተፈጥሮ ፀጋና በሰው ሃይል የታደለ ሆኖ እያለ ለ27 ዓመት ሙሉ የምድር ሲኦል ህይወት እንዲገፋ የፈረዱበትና አሁንም በስመ ተሃድሶ የሚሳለቁበት እነማን ናቸው? ብአዴኖች የሚባሉ የሞራልና የፖለቲካ በድኖች አይደሉም  እንዴ? ታዲያ በምን አይነት ማሳመኛ ነው  እንዲህ አይነት አሳፋሪ  ፖለቲከኞችን በሃላፊነትና በተጠያቂነት ሳንጠይቅ ነጋ ጠባ ህወሃት ላይ ብቻየምንረባረበው? እንዴት ሰው ከገንዛ ራሱ ቀየና በር ላይ የበሰበሰንና የከረፋን የፖለቲካ አካል ማፅዳት ሲያቅተው በህወሃት ላይ ብቻ ሲያሳብብ ይኖራል ?

ህዝብን ያህል  ክቡር የሰው ልጆች ስብስብ  “ለሃጩን ማራገፍ ነው” ብሎ የተሳደበው የፖለቲካና  የሞራል ውዳቂው (አቶ አለምነህ) እኮ የሥራ አይነትና መደብ ተቀየረለት እንጅ ተጠየቅ ያለው የለም  ጎበዝ!

በህወሃት/ኢህአዴግ መሥፈርት ድሮም ቢሆን አማራን ሊወክል የማይገባውና እንደሟቹ አለቃው የፖለቲካና የሞራል ሰብዕናው እጅግ የዘቀጠው አቶ በረከት ስምኦን ዛሬም አማራው በህወሃት/ኢህአዴግ  የተሃድሶ ማዕቀፍ ሥር ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ በላቀ ቀን እየወጣለት ነው እያለን እኮ ነው ጎበዝ !

የሩብ ምዕተ ዓመቱን የባለጌና እኩይ ፖለቲከኞች ባህሪና ተግባር ወደፊት በተመራማሪና ፀሐፊ ባለሙያች ተሠርቶ በታሪካዊ አስተማሪነቱ ትውልድ የሚማርበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ።

ታዲያ እንዲህ አይነቶችን የትሮይ ፈረሶች በሃላፊነትና በተጠያቂነት አጥብቀን ሳንጠይቅ የህወሃትንና የህወሃትን እኩይ ሴራ ብቻ በማብጠልጠል ፖለቲካ መጠመዳችን  ምን ይባላል ? የትስ ያደርሰናል ?

ከዚህ ሁሉ ዝቅጠትና ውርደት ያለራሳችን እልህ አስጨራሽ ትግል ነፃ ያወጣን ይመስል እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ተመልካች እዳር ቆመን  ጠቅላይሚኒስትር አብይና ቡድኑ ህወሃትን አሸነፈ እያልን ሆታውን እናቅልጠው? ወይስ ህወሃት ሊያሸንፍ ይችላል እያለንና ፀጉራችን እየነጨን እንቆዝም ? ፈተናችን የዋዛ አይደለም !

  • በዚህየለውጥ በር ተከፈተ እያልን የምሥራች አዋጅ ለመንገር በሚቃጣን ወቅት ሌላው የትሮይ ፈረስ ደኢህዴን ( የደቡብ ኢተዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) እንደ ኦህዴዶቹ ባይሆንም እንኳ ከተለከፍኩበት የክፉ አገዛዝ ቫይረስ ተሸካሚነት ነፃ ልውጣ ብሎ ከምር ማንገራገር ያልቻለ ፖለቲካዊ እንስሳ ሆኖ ቀጥሏል ። ሰሞኑን ደግሞ መቀመጫው ያደረጋትን ሃዋሳንና ሌሎች ከተሞችን ጨምሮ አደገኛ ትርምስ ውስጥ ሲከታቸው ታዝበናል ።

እኛም በፖለቲካ አስተሳሰባችን ሸፋፋነት ምክንያት ሃላፊነትንና ተጠያቂነት ጠቅልለን ለህወሃትና ለህወሃት ሴረኝነት ብቻ እያሸከምን ቀጥለናል ። እነዚህ የትሮይ ፈረሶች ተገደው ሳይሆን ወደውና በጥቅም ሰክረው የተካኑበትን የጥፋት መልክት ለመካላከል እንደዜጋ ምን አደረግን?እንደ ድርጅትስ የት ላይ ምን ፈየድን? እንደ ገዥ ፓርቲ (ኢህአዴግ) እና እንደ ኢህአዴግ መንግሥትስ ምን ያህል ጥረት ተደረገ? ድርጊቱ እንደተፈፀመስ ምላሽ የሰጠንበት ፍጥነትና ደረጃ ምን ያህል አመርቂ ነበር ? ከድርጊቱ በኋላስ የሠራነው ሥራ ከጊዜና በእውን ውጥረትን ከማርገብ ተልእኮ አንፃር እንዴት እንለከዋለን ? ብለን ራሳችን ሳንጠይቅ አሁንም የህወሃትን የሴራ ፖለቲካ ፍለጋ ነው የነጎድነው ። ህወሃት ለምን ይጠየቃል ሳይሆን የራሳችን ተጠያቂነት እየሸሸን ሌላውን መወንጀልና ማውገዝ ራሳችን  ያባልገናል እንጅ የትም አያደርሰንም እያልኩ እንደሆነ ግልፅ ይሁንልኝ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጥ ሃይል የምንለውም እንዲህ አይነቱን ሰበብ (execuse) እንደ አንድ የራስን ድክመት መሸፈኛና ለጊዜውም ቢሆን ያገኙትን የህዝብ አድናቆት እንደ መከላከያ የመቁጠሩ ሁኔታ ሲውል ሲያድር ክፉ ልማድ እንዳይሆ ንባቸው መጠንቀቁ አይከፋም ።

  • ህወሃት/ኢህአዴግበቀጥታ  ቁጥጥሩ ሥር ያልሆኑትን ክልሎች በተፅዕኖው ሥር ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱን የበለጠ የነፃ ፓርቲዎች መድብለ-ፓርቲ ለማስመሰል ሌሎች  ሳትላይትስ/አጋር የሚላቸው አምስት ተጨማሪ የትሮይ ፈረሶች አሉት ።  በስም ለመጠቀስ ፦ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፣ የኢትዮጵያ – ሶማሊ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራቲክ ፓርቲ ናቸው ። እነዚህ ልጣፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሩብ ምዕተ ዓመት በተላላኪነት (በአስፈፃሚነት) በአገርና በህዝብ ላይ የፈፀሙት ወንጀል አልበቃ ብሎ ፈጣሪያቸውና የብልግና ሥልጣን ዋስትናቸው (ህወሃት/ኢህአዴግ ) እየተንገዳገደ ባለበት በአሁኑ ወቅትም  ያንኑ የለመዱትን በግግርና በህዝብ መከራ የመነገዱን  ፖለቲካ ቀጥለውበታል ። ታዲያ ከአሁን በኋላ በህወሃትና በህወሃት ብቻ እያሳበቡ ከሃላፊነትና ተጠያቂነት ከቶውንም ሊሸሹ እንደማይችሉ በግልፅና በቀጥታ ሊነገራቸው ይገባል ።
  • ወደ ተቀዋሚ የፖለቲካ ጎራ ስንመጣም ችግሩ የተሻለ የሚባል አይደለም ።ለመሆኑ 27 ዓመት ሙሉ በዋና ዋና አገራዊ (የጋራ) ጥቅሞችና ዓላማዎች ዙሪያ ተሰባስቦ የህወሃት/ኢህአዴግን አፈና በአንፃራዊነት እንኳ ለመቋቋም በሚቻልበት አኳኋን እውን ለማድረግ እንዴት ሳይቻለን ዘለቅን? ይኸው እስከ አሁንም ከመጠናንበት የፖለቲካ አስተሳሰብ ደዌ ለመላቀቅ ገና ከምር የፖለቲካ ሥራ ውስጥ አልገባንም ።  በየመንደራችንና በየብሔረሰባችን ከፈጠርናቸው የፖለቲካ ፍጡሮቻችን ውጭ አስፍቶ ለማየት ፣  የግል ፍላጎትንና ጥቅምን ለአገርና ለህዝብ ስነል ሲሆን ለመተው ካልሆነም ቢያንስ ለመቆጣጠር ፣ ስለአንድ አይነት አጀንዳና ተልኮ እያወራን አንድ ባንሆን እንኳ ለመተባበር ፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ደግሞ አዳዲስ ድርጅት ከመቀፍቀፍ ይልቅ ካሉት መካከል በአንፃራዊነት ይስማማኛል የምንለውን መርጠን ለመቀላቀል እና  ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የህወሃት/ኢህአዴግን የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት አስወግዶ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል ቁመና እና ይዘት ማግኘት አለመቻላችን በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል ።

 

ሌላ ተጨባጭ ምሳሌ ልጠቀም  ። በአማራነት መደራጀት እንደ መርህና እንደ መብት የሚያጠያይቅ አይደለም ።   ነገር ግን  በኢትዮጵዊነት ስም መደራጀቱ እንኳ ቢቀር ለአማራ ስንት ድርጅት ነው የምንቀፈቅፍለት ( የምናራባለት) ?  በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ከአጠቃላይ ማለትም ከፖለቲካ ፣ ከኢኮኖሚ ፣ ከማህበራዊ ፣ ከሞራል ፣ ከሥነ ምግባር ፣ ከመንፈሳዊ(ሃይማኖታዊ) እምነት ቀውስ ለመውጣት ጭንቅ ለሆነበት አገር በየብሔረሰቡ ፋይዳው ከስምና የአንዳንድ አፍቃሪ-ሥልጣን ወይም እወቁኝ ባይ ግብዝ ፖለቲከኞችን ፍላጎት ከማርካት ያላለፈ የፖለቲካ ድርጅት መቀፍቀፍ በምንም አይነት የነፃነትና የፍትህ አገር የሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ ባህሪና ተግባር ሊሆን አይችልም ።

በተለይ አሁን ከፊታችን ተደቅኖ “መባከን የለብኝም” ከሚለን መልካም አጋጣሚ አንፃር ሲታይ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ሥራ የጤንነት ሳይሆን  የፖለቲካ ብርቱ ህመም ነው ።በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ድርጅቶች  የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የእባካችሁ እንነጋገር ጥሪ ተግባራዊ ቢሆንም እንኳ የየራሳችን የንግሥና ህልምና ዘውድ የሙጥኝ ብለን የበሰበሰውንና የከረፋውን  ሥርዓት አስወግዶ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት የሚቻል አይሆንም ።  ለዚህ ነው ለሁሉምና ለማነኛውም ድክመት (ውድቀት) ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ የማድረግ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጎድሎ ( ሽባ) ነው ማለት ትክክል የሚሆነው።

 

በአገራችን ገና ማብቂያ ላልተበጀለት መከራና ውርደት ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ሃላፊና ተጠያቂ የማድረግ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሰብዕና ወደየት ይወስደናል ? የትስ ያደርሰናል ? በእውነት እንነጋገር ካልን የህወሃት የትሮይ ፈረሶች (the Trojan horses) ሃላፊነትና ተጠያቂነት ከህወሃት ሃላፊነትና ተጠያቂነት ተነጥሎ ከቶ ሊታይ ይችላል እንዴ?

አጋር የሚላቸው ፍጡሮቹና አገልጋዮችስ እኩይ ባህሪያቸውንና ተግባራቸውን ሁሉ በፈጣሪያቸውና በበላይ ጠባቂያቸው እያሳበቡ የመቀጠላቸው ድንቁርና እና እብደት በቃችሁ መባል የለባቸውም እንዴ ?

በተቃውሞው ጎራ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶስ  እንታገለዋለን የሚሉትን ክፉ ሥርዓት   በጠረጴዛ ዙሪያ  በሚደረግ  የሰለጠነና በክህሉት በተካነ ድርድር  ወደ ሥር ነቀል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እንዲያመራ በማሳመን (በማስገደድ)  የተከፈተውን መልካም አጋጣሚ   መልሶ እንዳይጠረቅመው ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ለመዘጋጀት በሚያስቸል አኳኋን ዝግጁ ናቸው እንዴ ?

ሌሎቻችንስ እንደ ግለሰብ ዜጋ ፣ በተለያዩ የሲቭል ማሀበራት እንደተሳሰረ ማህበረሰብና በአጠቃላይ ነፃነነትና ፍትህ ፈላጊ (ናፋቂ) ህዝብ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የለብንም ወይ ?

እናም በነዚህና በሌሎች እጅግ በርካታና ውስብስብ ጥያቄዎች ከማንም በላይና በፊት እራሳችንን ተጠየቅ ሳንል ህወሃትንና ህወሃትን ብቻ ለሁሉምና ለማነኛውም ድክመት (ውድቀት) ተጠያቂ የምናደርግበት የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ጎደሎ (ሽባ) በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው  ሊታረም ይገባል። የምንነጋገረው በህወሃት/ኢህአዴግ “የተሃድሶ ትሩፋት” ለመንበሽበሽ ሳይሆን ለእውነተኛና መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ ከሆነ ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አበረታች ጅምር ወደ ታሰበው መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ምሥረታ ይወስደን ዘንድ እየተመኘሁ አበቃሁ!!!

(ጠገናው ጎሹ)

Share.

About Author

Leave A Reply