ለህዝቡ መብትና ለልአላዊነቱ የማይቆም መንግስት ያለው አገር ይዞ መኖሩ፣ እንደ አንድ አገር የማሰቡ ነገር እየቀረ መሄዱ ያሳስባል። (አስራት አብረሀም)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በፌስቡክ ተአቅቦ ላይ ነበርኩ። ነገር ግን የትናንትናው የኢህአዴግ መንግስት ውሳኔ ዝም ብዬ አልፈው ዘንድ አልቻልኩም። በሰው ላይ እንጂ በአገር ላይ አኩርፎ መኖር አይቻልምና። ሁኔታው በህዝቡ ላይ ምን ስሜት ፈጠረ የሚለውን ነገር ለማወቅ በፈስቡኩ መንደር ዞር ዞር አልኩ። የተለያዩ ወገኖች የአቋም መለኪያ ናቸው የምላቸውም ለይቼ ፈተሽኩ።

ከ70 ሺህ በላይ ልጆቹን የገበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ውሳኔ ደስ ሊለው እንደማይችል ግልፅ ነው። አንዳንዶች ግን የትግራይ መሬት ቢሄድ ሚመጣ ምን ቸገረን በሚል መልኩ ደስ ያላቸው እንዳሉ ታዝቤያለሁ። እንደዚሁም የአግኣዚያን ንቅናቄ ደጋፊ የሆኑ ኤርትራውያን “ባድሜ የትም አይሄድባችሁም፣ አልወሀ ድረስ ስላለው መሬት አስቡ” የሚል አቋም አንፀባርቋል።

ፌስቡክ ላይ ያሉ የትግራይ አክቲቢስቶች ደግሞ የተለያየ ስሜቶች ነው እያንፀባረቁ ያሉት። የህወሀት ደጋፊ የሆኑት ስለሁለቱ ህዝቦች አንድነት ነው ማሰብ አለብን እያሉ ነው። የአረናና ሌሎች ነፃ የሆኑ አክቲቢስቶች ደግሞ አጥብቀው እየተቃወሙት ነው የሚገኙት።

ከዚህ ውጭ የሆኑት ደግሞ የትግራይ ህዝብ በሁለት ወገን ከሚቀረቀር የባድሜ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ እልባት ሰጥቶ በአንድ ልብ በደቡብ በኩል ያለውን የተስፋፊነት ፍላጎት መመከት ይሻላል የሚል አቋም ያላቸው ይመስላሉ።

የሆኖ ሆኖ ህወሀት በስልጣን ለመቆየት ካለው ጥማት የተነሳ አሳልፎ የማይሰጠው ነገር ያለ አይመስልም። በስልጣን ለመቆየት ሲል በአንድ ዓመት ውስጥ የትግራይ መሬት ቆርሶ ሲሰጥ ይሄ ለሁለተኛው ጊዜ ነው።

አምና ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለብአዴን ሰጥቷል፤ አሁን ደግሞ እንደዚሁ ከገባበት ቅርቃር ለመውጣት ባድሜን በዶ/ር አብይ አህመድ በኩል ሰጥቶ ከሻዕቢያ ጋር መታረቅ ፈልጓል። ከዚህ በኋላም ህወሀት በስልጣን ለመቆየት ይጠቅመኛል ብሎ ካሰበ ሌላውንም ቦታ እንደዚሁ እየቆረሰ የማይችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ሁኔታው በጠቅላላ እንደ አገር ካየነው አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።

ለህዝቡ መብትና ለልአላዊነቱ የማይቆም መንግስት ያለው አገር ይዞ መኖሩ፣ እንደ አንድ አገር የማሰቡ ነገር እየቀረ መሄዱ ያሳስባል።

Share.

About Author

Leave A Reply