ለመሆኑ መሠረታዊው ጥያቄ ምንድን ነው ? ጎልቶ የማይሰማውስ ለምንድን ነው?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጠገናው ጎሹ

ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት እንደመግቢያ የሚከተለውን ልበል ።

በአገራችን እውነተኛ የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ፣ ለመመሥረትና ለማጎልበት በሚደረግ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ እጅግ ፈታኝ ከሆኑብን ጉዳዮች አንዱ የምንቃወመውንና የምንደግፈውን አካል በተመለከተ የምንጠቀምበት አቀራረብ ነው።  የምንጠላውን ሃይል (አካል) የሚያስታግስልንን ወይም ለማስወገድ የሚያስችለንን ሃይል (አካል) ተቀብሎ ድጋፍ መስጠትና  ተገቢውን አድናቆት መግለፅ እጅግ በጣም ትክክል ነው ።  እጅግ በጣም ትክክል ያልሆነው ግን ስንቀበልና ስናደንቅ የምጠቀምበት የአቀራረብ (የአመለካከት) ሁኔታ  ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ስሜታዊነት የተቃኘ በመሆኑ የምክንያታዊነት ኅይላችንን (አቅማችንን) በእጅጉ የሚያኮሰምን (የሚፈታተን)  የመሆኑ ጉዳይ ነው ።   በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ አኳኋን እያየንና እየሰማን ያለነው ይህንኑ ከዘመን ጋር መዘመን ያቃተውን በስሜት የመንጎድን ወይም ምን? ለምን? እንዴት? ከየት ወደየት? መቼና እስከመቼ? ወዘተ ብሎ ከምር ሳይጠይቁ አደባባዩንና አዳራሹን በስሜታዊነት ፈረስ  ቀውጢ የማድረግን  ልማድ  ነው።

የምንጠላውን (የበደለንን) አካል  የምንታገልበት አቀራረብና ዘዴ በተቻለ መጠን  እንታገልለታለን ከምንለው  የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህሪ ፣መርህና ተልእኮ ጋር የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል ። በደለን እንደምንለው አካል የበደል መጠንና አይነት በሚኖረን አቀራረብ መሠረት ሃሳብን በሃሳብ ፣ ኢ-ፍትሃዊነት በፍትሃዊነት ፣ ህገ ወጥነትን በህጋዊነት ፣ ወንጀለኝነትን አግባብነት ባለው ህግና ደንብ ፣ ስሜታዊነትን በስክነት ፣  ብልግናን በጨዋነት ፣ የሞራል ድህነትን በሞራል ልዕልና ፣ አሳዳጅነትንና ተሳዳጅነትን በአቀራራቢነት ፣ የሃሳብ ጠማማነትን በሃሳብ ቀናነት ፣ ወዘተ የማስተናገድን (መፍትሄ የመስጠትን) የፖለቲካ ባህል ካላዳበርን በስተቀር የምንመኘው የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንኳን እውን ሊሆን በጥሩ ህልምነትም አይጠጋንም ።  ብንሞክረውም እንኳ አብሮን አይዘልቅም ።

ለሚስማማን ወይም ይስማማናል ለምንለው አካል የምድሩንና የሰማዩን ሁሉ የቅዱስነት ማዕረግ ያለምንም ሂሳዊ አስተያየት   እያጎናፀፍን ፣ በበደለን ወይም ይበድለናል በምንለው አካል ላይ ደግሞ በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ጭራቃዊ ስም ከመስጠት አልፎ በህግ (በፍትህ ሥርዓት) ሳይሆን እኔ ባለፍኩበት አታልፍም/አታልፊም  እየተባባልን ከምንፈልገው የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር የታረቀ የፖለቲካ ሰብዕና እንዴት ይኖረናል ?በጭራሽ አይኖረንም ። እንዴኖረን ከምር የምንሻ ከሆነ ወደ ኋላ የሚጉትተንን አስተሳሰብ  ከቻልን  እያስወገድን ቢያንስ ግን እየተቆጣጠርን መራመድ ይኖርብናል።  ይህን ሆኖና አድርጎ ለመገኘት ደግሞ  ከየራሳችን ህሊና ጋር  ትግል ማካሄድ ግድ ይለናል።  ለዘመናት ለዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እና ለበለፀገ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ጨርሶ ባእዳን ሆነን ከዘለቅንበት ምክንያቶች አንዱ ወደ የጋራ ትግል ስንቀላቀል ከየራሳችን ጋር በመታገል ከራሱ ጋር የታረቀና ለጋራ የነፃነትና የፍትህ ትግል ከምር የተዘጋጀ የፖለቲካ ሰብእናን እና ቁመናን ተላብሰን ስለማንቀላቀል ነው ።  ይህን ክፉ አባዜ ከምር በመታገል መሆንና ማድረግ የሚገባንን  ሆነንና አድርገን  ካልተገኘን  እውነተኛውን ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እናደርጋለን ማለታችን ቅዥት እንጅ የገሃዱ ዓለም ራእይ ከቶ ሊሆን አይችልም ።

የኢህዴግን ጠርናፊ የፖለቲካ ሰንሰለት ሰብረው በመሪነት የለውጥ እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉት ፖለቲከኞች ያሳደሩብንን አግራሞት (excitment) በሰከነ አኳኋን ማስተናገድ አልሆንልን ብሎ ከቁጥጥራችን ውጭ በሆነ ስሜት ውስጥ በምንገኝበት በዚህ  ሰሞን ይህን ሂሳዊ አስተያየት ወደ አንባቢ ሳደርስ መሪዎችን መዳፈርእየመሰላቸው ምቾት የማይሰማቸው አንባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እረዳለሁ ። የማይጠበቅ ነው የሚል የቂልነት/የድንቁርና እይታም የለኝም ።   ነገር ግን ሁሌም አንዱ የሌላውን ሰብአዊ ተፈጥሮና ግላዊ ሰብእና እስካላጎሳቆለ ድረስ ሃሳብን ወይም አስተሳሰብን በደምሳሳው ሳይሆን  በምክንያታዊነት ቢተች ፣  ቢሞግትና አስፈላጊም ከሆነ  አካፋን አካፋ እስከ ማለት ቢሄድ በጣም ትክክል ነው የሚል ፅእኑ አስተሳሰብ አለኝ ። እንዲያውም ለዘመናት አጠቃላይ ውድቀታችን አንዱ ምክንያት በዚህ ረገድ ያለብን ከባድ ጉድለት ነውና ከምር ልንወስደው ይገባል ባይ ነኝ ።

በዚሁ መርህና እምነት መሠረት ልቀጥል ። 

“We let go of the old to discover the new, as we let go of illusions to discover the real.” (“ተጨባጩን እውነት ለማግኘት የተሳሳተውን እምነት (አስተሳሰብ) እንደምናስወግድ  ሁሉ አዲሱን ለማግኘትም አሮጌውን እንናስወግዳለን።”) THE Art of Original Thinking / the Making of a Thought Leader/, Jan Phillips, 2006

እንደ እኔ ግንዛቤና አረዳድ በአገራችን ኢትዮጵያ በመታየት ላይ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ የመነሻውና የመዳረሻው አውደ ቁም ነገር ይኸው ነው ።  አዎ! አሁን ያለንበት የፖለቲካ  አውደ ቁም ነገር  ብዥታን ወይም የተሳሳተ አስተሳሰብንና እምነትን (illusion and delusion) እያስወገድን  በእውነቱ (በገሃዱ) ዓለም ምንነትና እንዴትነት ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብንና እምነትን ከምር የምንቀበልበትና የምናጎለብትበት ነው ። የምንገኝበት አውደ ቁም ነገር  ለሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ምንጭ ሆኖ የዘለቀውን (ያረጀውን) እና አሁንም  “ታይቶ የማይታወቅ” ጥገናዊ (ተሃድሷዊ) ለውጥን (reformismን ) ከራሱ ተፅዕኖ ባልወጣ (እንደ ሥርዓት በሚቀጥልበት) አኳኋን ለማስኬድ እየሞከረ ያለውን  የኢህአዴግ አገዛዝ አስወግደን አዲስና ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበረሰብ የመፍጠርና የመገንባት አውደ ቁም ነገር ።

እየተነጋገርን ያለነው የበኩላቸውን  አውንታዊ ጥረትና አስተዋፅኦ እያደረጉ  ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድንና ቡድናቸውን ስለመውደድ ወይም ስለመጥላት አይደለም ። እየተነጋገርን ያለነው አገርን አገር የሚያሰኝ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የአገርና የወገን ጉዳይ ያገባኛል በሚል የፖለቲካና የሲቭል አካል (ድርጅት) ባለድርሻነት፣ ባለቤትነት ፣ እኩል ተሳታፊነትና ወሳኝነት ፣ ሃላፊነትና ግዴታ እውን ስለማድረግ ነው ።የጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጥ ደጋፊ ቡድናቸው ጥረት መታየት ያለበት በዚሁ እጅግ ውስብስብና ፈታኝ የፖለቲካ እውነታ ውስጥ እንጅ እራሱን ወሳኝ የለውጥ አካል ( agent) በማድረግና ኑ እና ተጨመሩ (ተደመሩ) በሚል የፖለቲካ ቅኝት መሆን የለበትም ነው የመነጋገሪያችን ቁም ነገር ።

እንደ እኔ ግንዛቤና እምነት የለውጡን እንቅስቃሴ ምንነትና እንዴትነት  ከዚህ መሠረታዊ ጥያቄ ውጭ እንኳን መቀበል ለመቀበል ማሰብም ለዘመናት በተከፈለ መሪርና ግዙፍ የነፃነትና የፍትህ መስዋዕትነት መቀለድ ወይም መነገድ ነው ። የረጅም ዘመን የፖለቲካ ታሪካችን እንደሚነግረን ደግሞ ለውጥ እየመጣ ነው ወይም በር ላይ ቆሟል በተባለ ቁጥር በእውን እውነተኛውን ህዝባዊ ተልእኮ እውን ለማድረግ እንዲያስችል ተቀብለን እንዴት እናስተናግደውና እንዴት ለዋናው የጋራ ግብ እናብቃው ?  የእኔስ/የእኛስ ሚና እና አስተዋፅኦ ምንድን ነው? ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ   በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ (by hook or crook) እንዴት የግል ወይም የቡድን ፍላጎቴን አረካለሁ በሚል ልክፍት የተለከፈው በቁጥር ቀላል የሚባል ሊሆን እንደማይችል እውነት መሆኑን ነው ። እጅግ አስቀያሚ ከሆኑትና አሁንም እየተናነቁን ከሚገኙ እውነታዎች አንዱም ይኸው ነው።

አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴ የታለመለትን ግብ (ተልዕኮ) ይመታ ዘንድ ከምር ልብ እንድልንላቸው ግድ የሚሉን እጅግ መሠረታዊ ጉዳዮች (indespensible issues)  መኖራቸውን በፖለቲካ ትኩሳት ሽምጥ የሚጋልበውን የስሜታዊነት ፈረስ ልጓሙን ገትተንና ትንፋሽ ወስደን ለመረዳት ቢያንስ የሞራል ድፍረት ሊኖረን ይገባል ።  ልክ የሌለው  ስሜታዊነትንና  ልጓም አልባ የተስፈኝነት ፈረስ ግልቢያውን በቅጡ አድርገን ፈታኝ ሁኔታዎችን (ጉዳዮችን) በሰከነ አኳኋን ማየት ፣ መረዳትና ትክክለኛውን መፍትሄ ማግኘት  ካልቻልን በስተቀር  የምንመኘው የአዲስና መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና  ግንባታ ምኞት ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው ።

“አይ ! ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳልና እኛም በተሃድሶው ለውጥ (reformism) ያገኛናትን ረድኤትእየኮመኮምን ጎደል ስትል ደግሞ እንጠይቃለን (እናለቅሳለን)” የምንል ከሆነ ደግሞ እንዲሁ የገዦቻችን እጅ እያየን ስናለቅሳት እኖራለን እንጅ የትም አንደርስም ። ከዚህ የከፋና የከረፋ   እራስንና አገርን ውርደት የሚያከናንብ እኛነት ደግሞ የለም ።

ጨርሶ ሊከለስ ወይም ሊታጠፍ የማይገባውን  የለውጥ እንቅስቃሴ ተልኮ (ግብ) በክፋት ተወልዶና አድጎ በክፋት  ያረጀውን የፖለቲካ ሥርዓትን ጠጋግኖ እንደ ሥርዓት እንዲቀጥል በማስቻል  የተሳካ ማድረግ አይቻልም ። የለውጡ እንቅስቃሴ ብቸኛ መዳረሻ አዲስና እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ  የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት ነው ብሎ ለሚያምን ኢትዮጵያዊ  በቀጥታና በግልፅ የሚሞግቱ ጥያቄዎች መሪዎች በተገኙባቸው (በሚገኙባቸው) አደባባዮችና ሌሎች  መድረኮች ጎልተው አለመስተጋባት  ብቻ ሳይሆን ጨርሶ የሉም በሚያስብል ሁኔታ ላይ መገኘታችን  በእውን ሊያሳስበው ይገባል ።

በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ የተካሄዱትንና እየተካሄዱ ያሉትን የአደባባይ ትዕይንቶችንም ሆነ የአዳራሽ ውስጥ ውይይቶችን ከምር ለታዘበ  ምን ? ለምን ? የት? ወዴት? መቼ? እንዴት ? በማን/በነማን ?ለነማን? የሚሉና የአንድን ጉዳይ የይዘት ጥራትና ብቃት ለማወቅ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቂዎችና የሃሳብ ለውውጦች ከምር የተስተናገዱባቸው አልነበሩም (አይደሉም) ። ጥያቄዎችና መልሶች ወይም ወይይቶች አልነበሩም አይደለም እያልኩ ያለሁት ። እያልኩ ያለሁት ለረጀም ዘመን ለመጣንበት  የሁለንተናዊ የመከራናየውርደት አስከፊነትና አሁንም ላለንበት ተስፋ ሰጭ ግን እጅግ ፈታኝ ወቅታዊ ሁኔታ  በጭራሽ የሚመጥኑአልነበሩም(አይደሉም) ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ እንዴ ምን ነካ ? የሚያሰኙ ነበሩ (ናቸው) ። በዚህ ረገድ ደግሞ የሰሜን አሜሪካው ጥሩ (typical) ምሳሌ ነው ። በጣም ቅጥ ያጣና የሚያስተዛዝብ የድራማ አይነት ትርምሱ (over dramatization) እንደተጠበቀ ሆኖ ጉብኝቱን የተሳካ ነበር ማለት የሚቻለው ብዛትና ድምቀት ያላቸው ትይንተ ህዝቦችን በማስተናገዱ ረገድ ነው ።

እናም እውነተኛ ውበት ማለት የቅርፅና የይዘት ውህደት ነው በሚለው ከተስማማንና እነዚህ የለውጥ ፈላጊነት ትእይንቶችና ውይይቶች ከፍተኛ የይዘት ጉድለት አለባቸው ካልን ውበታቸው የተሟላ አልነበረም (አይደለም) ማለት ነው። አሁንም እያልኩ ያለሁት ኢትዮጵያውያን በህብረ ቀለም ባንዲራችንና የእኛ ብቻ በሆኑ ባህሎቻችን ደምቀንና በደስታ ስሜት ፈንድቀን  መሪዎችን ስንቀበል አናምርም ወይም ውበት አይታይብንም አይደለም ። ማለት የፈለግሁት እጅግ ግዙፍና ውስብስብ ከሆነው የአገራችን የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣትበምናደርገው ጥረት ውስጥ በይዘት ጥራትና ብቃት ላይ ማድረግ ያለብን እልህ አስጨራሽ ሥራ በቅርፅወይም ለአይን እይታና ለሌሎች ስሜቶቻችን ቅርብ በሆኑ እንቅስቃሴዎች የተሸፈኑብን ስለሆነ ውበታችን ገናየተሟላ አይደለም ነው ።

ይህ የፖለቲካ ልፍስፍስነት  ለራሳችን  መልሶ የሚነግረን አስቀያሚ መልእክት   ” አይ! መሠረታዊ ባይሆንምአይተነው የማናውቅ ጥልቅ ጥገናዊ ለውጥ (reformism) ለአሁኑ ይበቃናል ፤ ቀሪው በሂደት ይሟላል”ከሚልና በእጅጉ ከኮሰመነ (ታች ከወረደ) የአስተሳሰብና የሥነ-ልቦና ሰለባነት ለመላቀቅ ያለብን ፈተና የዋዛ አለመሆኑን ነው ።

ይህን የአስተሳሰብ ድህነታችን በድፍረትና በቶሎ ካላረምነውና ወደ ትክክለኛው መስመር ካላስገባነው የለውጡን ባቡር የዘዋሪነት መቀመጫ  ( the driver’s seat ) ለድል አጥቢያ አለሁ ባዮችና በድክመታችን ተጠቃሚ ለመሆን ጭራቸውን ለሚቆሉ ወይም የፖለቲካ ሽርሙጥና ልማድ ለሆነባቸው ፖለቲከኞች ወይም ግለሰቦች ወይም ቡድኖች  ማስረከባችን እንደማይቀር ከምር ሊያሳስበን ይገባል ።  በሌላ አባባል በለውጡ እንቅስቃሴ ተልዕኮና ግብ ላይ ያለብንን ብዥታ (illusion/delusion) አስወግደን በተጨባጩ ዓለም ላይ (real world of politics) የተመሠረተ አስተሳሰብ (አመለካከት) ለመቀበልና  ለማጎልበት  ፈቃደኛና ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንዳለብን ያለንበት ፖለቲካዊ እውነታ ግድ ይላል ።  ካልሆነ ግን የለውጡን እንቅስቃሴ ለዉጡን በተቀላቀሉ አባሎቹ አማካኝነት ከመቃብር አፋፍ በተመለሰው ኢህአዴግ የበላይ መሪነት ወይም  ዋነኛ ተዋናይነት በሚካሄድ ጥገናዊ ለውጥ (reformism) አማካኝነት የሚጣልልንን ፍርፋሪ በዝማሬና በውዳሴ ለመቀበል ዝግጁ ነን ማለት ነው ።

ለነገሩ እንኳንስ “ጠቀም ያለ” ፍርፋሪ  ተለግሶልን ገና የለውጡ ጅማሮ ከዲስኩርና ከአንዳንድ አወንታዊ እርምጃዎች ባላለፈበት ሁኔታ ውስጥ ሆነንም  የምንገኝበትን ፈታኝ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ እና መንፈሳዊ   እውነታ   እና የምንመኘውን ሥርዓት መዳረሻ  ምንነትና እንዴትነት ባላገናዘበ አኳኋን “ኢትዮጵያ ትንሳኤዋ ተፈፀመ!” በማለት የውዳሴውን ቅኔና ዝማሬ ማዥጎድጎድ ከጀመርን ሰነባብተናል። በእጅጉ የሚያሳስበው ደግሞ ልክ የሌለውን የስሜታዊነት ፈረስ ግልቢያችን እየተቆጣጠርን ወዴትና እንዴት እየነጎድን እንደሆነ እራሳችንን ለመጠየቅና ተገቢውን እርምት ለማድረግ እንኳ ከምር ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ያለመሆናችን አባዜ ነው ።

ስንመኘው የኖርነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ታሪካዊ  ትንሳኤ  እውን ይሆን ዘንድ  በሰከነና በሰለጠነ  አኳኋን ተቀብለንና  ተንከባክበን እውን እናደርገው ዘንድ ስንኝ ቋጥሮ መቀኘት ፣ ማዜም  ፣እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የተግባር ሰው ሆኖ መገኘት በእጅጉ ትክክል ነው ። ከዚህ አልፎ  ግን ” የኢትዮጵያ  ትንሳኤ ተፈፀመ ! “ብሎ አዋጅ ቢጤ መንገር  እራስን መሸንገል ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ፣ እኩልነት ፣ ሰላምና የጋራ ብልፅግና በሰፈነባት አገር ውስጥ ለመኖር ይችል ዘንድ እልህ አስጨራሺ ትግል ውስጥ የሚገኝን ትውልድ በተሳሳተ አስተሳሰብና እምነት  (illusion and delusion) ግራ ማጋባት  ነው ። “ፖለቲከኞችን ከሰማይ ቤት የተላኩ የትንሳኤው ባለቡራኬዎች  ስለሆኑ ከተቻለ ያለምንም ሂሳዊ ትችት (critique) መደገፍና መደመር  ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጊዜና ፋታ  እየሰጡ  ምክር ወይም ቅሬታ ቢጤመሰንዘር  ነው” የሚል አንድምታ ያለው  ማሳመኛ አይሉት ወይ ተማፅኖ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ አይደለም ።  በለውጡ እውነተኛ መዳረሻ  ላይ  ማተኮር  ያለባቸው ጥያቄዎች ጎልተው እንዳይወጡ  የማድረግ ተፅዕኖው ግን በእጅጉ  የጎላ ነው ።

አንድ ህብረተስሰብ በአጠቃላይ እና በተለይ ደግሞ የተማረው የህብረተሰብ ክፍል  ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለበት የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ እውን ይሆን ዘንድ ፖለቲከኞችን ከምር መሞገት ይኖርበታል ። ከምር መመለስ ያለባቸውን ጥያቄዎች በየትኛውም አደባባይ ወይም መድረክ ፊት ለፊት በማምጣት ተገቢውን መልስ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለበት ። እስከ ሚያረጋግጥም ፀንቶ መቆም አለበት ። ድንቅ ዲስኩር እየደሰኮሩና እያስደሰኮሩ  በእልልታውና በጭብጨባው ድምቀት መክነፍ እንኳን እንደኛ በሁሉም የህይወት ዘርፎቻችን ጥልቅና ውስብስብ ፈተና ባለበት አገር እጅግ በተሻለ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አገራትም ፈፅሞ የሚበጅ አይደለም ። ለዚህ ነው ለስሜታችን እጅግ ቅርብ ከሆኑ ጥያቄዎች ወጥተን ፖለቲከኞቸን ከምር እንዲያስቡና ለህመም ጊዜያዊ ማስታገሻ ከሆነ የፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጡ መሞገት የግድ ሊለን የሚገባው ።  ተስፋና ስጋት ገና በቅጡ ያለዩበት የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደትን በተፈለገው መንገድና ደረጃ እውን የማድረጉ ጉዳይ የሚወሰነው በማይናወጥ መርህ ላይ በቆመ ፣ በሰከነ፣ በተጠና ፣ በታቀደ ፣ በተቀነባበረ ፣ አላስፈላጊ ሰበብን በተፀየፈ እና የነገውን አስቀድሞ ለማየት በሚያስችል እልህ አስጨራሽ የተግባር ውሎ እንጅ ከልክና ባለፈና በመሬት ላይ ያለብንን እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በማያንፀባርቅ “የጎሮ ወሸባዬ” ትዕይንት አይደለም ። ሊሆንም አይገባም ።

በዚሁ በሰሜን አሜሪካው ጉብኝት ወቅት እንኳን የእኔ ቢጤ ፊደል ከመቁጠር ያላለፈው ይቅርና ልሂቅ (intellectual) የሚባለው የህብረተሰብ ክፍልም መሪዎችንና አሁንም እንደ ሥርዓት በሥልጣን ላይ ያለውን ድርጅታቸውን (ግንባራቸውን) በተመለከተ እጅግ ወሳኝ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ እወቀቱንና የህይወት ተሞክሮውን በሚምጥን አኳኋን አለመሞገቱ በእጅጉ አሳፋሪ ነበር ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ቤት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ጋር ያደረጉትን ውይይት በእውን ሂሳዊ (critical) በሆነ አቀራረብና አመለካከት የተከታተለ የአገሬ ሰው ለብዙ ዓመታት ለመጣንበት የግፍና የውርደት ፖለቲካ እና አሁን ላለንበት እጅግ ፈታኝ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዴት ይመጥናል? ብሎ መጠየቁ አይቀርም። መማር (ትምህርት) ማለት እውነተኛ ትርጉሙ እንኳን በራስ ድክመት ጭምር የተበላሸውን የአገርን ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሰው ሠራሽ ቀውስ  ይቅርና  ተፈጥሮ ወለድ አደገኛ ክስተቶችንም ከተቻለ ለመከላከል ካልሆነም ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል አእምሮ ወለድ መሣሪያ (an instrument agaist catastrophe) ነው ። ይህ ግን ከምሁራን (ከልሂቃን) ከሚጠበቀው በታች ሆኖ ስናገኘው ቢያንስ ለምንና እንዴት? ብለን መጠየቅ  የጥሩ ዜግነት ሰብእና ነው።  እናም በአብዛኛው የውይይትና የገለፃ ስልታቸው (አቀራረባቸው) አስተማሪ ለተማሪዎቹ እንደሚያስተምር አይነት የሆነው ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር አብይ አህመድ መድረኩን የምሁራኑን አሳፋሪ ድክመትና የእሳቸውን ብቃት(ችሎታ) ለማሳየት ጠቅሟቸዋል ቢባል እውነት ነው ። ። የዋሁ የአገሬ ሰውም ” ይኸው ነው እንዴ እየታደሰ ካለው ኢህአዴግ የተሻለ እውቀትና ራዕይ ያለው ምሁር? ኧረ የዶ/ር አብይ ኢህአዴግ ይግደለኝ” ብሎን እርፍ !

ይህ አሳፋሪ ሁኔታ በሰሜን አሜሪካው ጉብኝት 26 ይሆናሉ ከተባሉ ተቀዋሚ የፖለቲካ የድርጅቶች መሪዎች (ተወካዮች) ጋር ባደረጉት ወይይትም እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ተድግሟል ። ይህን የተከታተለ ዳያስፖራ የሚባለው የአገሬ ሰውም ለምንና እንዴት? ብሎ ሳይጠይቅ  “ከእንግዴህ ከዶ/ር አብይና እድሳት ላይ ካለው ኢህአዴግ ጋር ሞቴንም ድነቴንም ያድርገው” ብሎን እርፍ!

አንዳንዶችማ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ጥያቄዎችን አንስቶ መሪዎችን መሞገቱን ጨርሶ ረስተውት “የእባከዎ እንደመር” ተማፅኗቸውን ከምርቃት ጋር ማቅረብ ሲቃጣቸው ታዝበናል ። ከሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ተሞክሮ በኋላም በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘታችን በእጅጉ ሊያሳስበንና ከጊዜውና ከሁኔታው ጋር የሚመጣጠን ሥራ እንድንሠራ በእልህ ልንነሳሳ  ይገባል ።

ለመሆኑ፦

 • የመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄ መናሻ ምክንያቱ ምንድነው ? የኢህአዴግ የጭቆና እና የመከራ አገዛዝ አይደል እንዴ?
 • ታዲያ ከዚህ አስከፊ ሁኔታ መውጫ መንገዱ የሚቀየሰውና የሚዘረጋው በማን መሃንዲስነትና ሥራ አስኪያጅነት ነው ? ለሩብ ምዕተ ዓመት እኔ ከቀየስኩትና ከዘረጋሁት መንገድ ውጭ ለምን ሄዳችሁ በሚል የስቃይና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ የኖረ ገዥ ቡድን የለውጡን እንቅስቃሴ በበላይነት መርቶ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ እንዴት የሞራልና የፖለቲካ ብቃት ሊኖረው ይችላል ?
 • በአንፃራዊ እይታ ከኢህአዴግ አስተሳሰብና አሠራር የተለየ አቋም የያዙ ፖለቲከኞች በመልካም የፖለቲካ ቋንቋ የታጀቡ አንዳንድ ይበል የሚያሰኙ እርምጃዎችን በመወሰዳቸው ኢህአዴግ እንደሥርዓት ( ውህድና አገራዊ ስያሜ ሊይዝ እንደሚችልም እንደተጠበቀ ሆኖ) በግፍ ገዥነት የተዘፈቀ ማንነቱ በቅጡ  ሳይፈተሽ አንዳንድ አባሎቹን ከቦታቸው በማንሳቱ  ፣ ከስልጣን በማውረዱ ፣የሥራ ቦታ በመቀየሩ ፣ በዲፕሎማትነት በመሾምና በመመደቡ ፣ጦረታ በማስወጣቱ ፣ አንዳንደ የተቀዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ፖለቲከኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱና ፖለቲካዊ ባልሆኑ ተቋማት( ለምሳሌ የቦርድ አባል) እንዲሆኑ በማድረጉ ፣  አታስቡ እኔ ነኝ መሸጋገሪያውና እናንተ እየመጣችሁ ተጨመሩ ፣ ወዘተ በማለቱ   እንዴት ነው የአዲስ መሠረታዊ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን በበላይነት ለመምራት የሚያስችል የፖለቲካና የሞራል ብቃት የሚኖረው?
 • ፕሮፓጋንዳ አስፈላጊ ከሆኑ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃ ስልቶች አንዱ ቢሆንም በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን ያሳስታል። ከኢህአዴግ በወጡ የለውጥ አራማጅ በምንላቸው ፖለቲከኞች እየተመራ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በአንፃራዊ እይታ የተሻለ ራእይና አቅም አላቸው የተባሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ቀጥተኛ በሆነና ትርጉም ባለው ኦኳኋን ተሳታፊ ባልሆኑበት “ግንቡ ፈረሰና ድልድዩ ተዘረጋ” የሚል “የምሥራች አዋጅ” ከጠቀሜታው አሳሳችነቱ አይበልጥም እንዴ ?
 • የገደለና የዘረፈ ቅጣቱን ያገኝና የፍትህ ልዕልና ይረጋገጣል ። ትውልድም እየተቀባበለ የሚኖርበትን ሥርዓተ ማህበረሰብ የበለጠ ጤናማ ለማድረግ በትምህርታዊነቱ ይጠቀምበታል ። ኢህአዴግ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ሥልጣን ላይ እንደቆየ የፖለቲካ ድርጅት መግለፅ የሚያስቸግር ኢሰብአዊ ወንጀል ፈፅሟል። አገርንም አዋርዷል። “አሁን በጥልቅ እየተለወጥኩ ነውና ሃላፊነት ከመውሰድ ጋር ይቅርታ ይደረግልኝ” ባለው መሠረት “እንደማነኛውም የአገር ባለድርሻ የፖለቲካ ድርጅት የመሸጋገሪያ መንግሥት ባለድርሻ ሆነህ ሃላፊነትክን ከተወጣህ ለዘላቂ ሰላም ሲባል ይቅርታውን ተቀብለናል” ሲባል “አይ!ሽግግሩን በመሪነት ተያይዠዋለሁና እየመጣችሁ ተጨመሩ” ብሎን እርፍ ! ቢያንስ እንኳ አጀንዳው ትልቅና የጋራ ግንዛቤና ውሳኔ የሚጠይቅ ስለሆነ ከሁሉም ባለድርሻ ወገን ጋር በሚደረስበት ስምምነት መሠረት በሚካሄድ የምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል የሚል ሃሳብ ጨርሶ አለማንሳት የሚያስተላልፈው መልክት በጭራሽ ጤናማ አይደለም ። ታዲያ ኢህአዴግ በዚህ የግብዝነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንዴት ሆኖ ነው የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርንና ምሥረታን በበላይነት መርቶ እውን እንዲሆን የሚያስችለው ?
 • ለመሆኑ “የለውጡ እንቅስቃሴ ዋነኛ ግብ ኢህአዴግን በማሻሻያ ፕሮጀክትና ፕሮግራም (reformism) አጥምቆ በማስቀጠል የሚከናወን ሳይሆን በጋራ መግባባትና በንቁ ተሳትፎ በሚፈጠር የሽግግር አካል (መንግሥት) አማካኝነት መሆን አለበት” የሚለውን የዘላቂ መፍትሄ አሰጣጥ ሃሳብ በማያወላዳ ሁኔታ ውድቅ የሚያስደርግ ምክንያት አለወይ? የአገሪቱን ሁለንተናዊ የአቅም ውሱንነት እና አሁን እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ያስተጓጉላል (አደጋ ላይ ይጥላል) የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል ። መቅረቡም ተገቢ ነው ።

በሌላ ወገን ደግሞ   “ሽግግሩን በኢህዴግ የበላይ  መሪነትና ትርጉም ያለው የወሳኝነት ድርሻ በሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተደማሪነት ማካሄድ በቀላሉ ሊታይ የማይችል  ከወገናዊነት  ነፃ የመሆንና  የአስተማማኝነት ችግር ስለስለሚኖርበት  ነገ ተመልሰን ወደ ንትርክና ዱላ መማዘዝ እንድንገባ ለማድረግ በር ይከፍታል ። ስለሆነም  ለጊዜውም ቢሆን የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ በሽግግር መንግሥት አማካኝነት  ክፉውን የፖለቲካ አዙሪት ታሪክ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ  በመዝጋትና ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ መሸጋገር የተሻለ ነው የሚል መከራከሪያ መቅረቡም ተገቢ ነውና ከምር ሊወሰድ ይገበዋል። ”

እናም እነዚህንና ተያያዥ ፈታኝ ጉዳዮችን (ጥያቄዎችን) በአግባቡ የሚያስተናግድ የምክክርና የጋራ መፍትሄ አፈላላጊ  መድረክ ባልተፈጠረበት የፖለቲካ ሁኔታ “ እኛ እናሸጋግራችኋለንና እየመጣችሁ ተደመሩ (እርዱን)”ማለት ምን ማለት ነው?

እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በአግባቡና ዘላቂነት ባለው አኳኋን ለማስተናገድና የለውጥ እንቅስቃሴውን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ከግቡ ለማድረስ ትኩረት ይሻሉ የምላቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ላቅርባቸው ።

 • በአገራችን የተሞከሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች (አብዮቶች) ሁሉ በጨካኝ አምባገነን የገዥ ቡድኖች እየተነጠቁ (እየተጨፈለቁ) እስከአሁን የመከራና የውርደት ማንነት ተሸካሚ ሆነን የዘለቅነው ስለ ለውጥ እንቅስቃሴ  መነሻ ምክንት ተመሳሳይ ቋንቋ (የነፃነትና የፍትህ እጦት መሆኑን) እየተናገርን በውስጥ የአስተሳብ ጓዳችን ግን የተደበቀና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የግል ወይም የቡድን ፍላጎት እርካታን እያሰላን ወደ ድርጊት ስለገባን (ስለምንገባ) ነው ።  እንዲህ አይነቱ እኩይ አስተሳሰብ  ደግሞ የለውጥ እንቅስቃሴን ገና ከሂደቱ ጀምሮ የየራስን ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ከግቡ በሚያደርስ አኳኋን የመቆጣጠር የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ አድርጎ  ማመን የሚያስቸግር መስዋእትነት አስከፍሎናል ።

የፖለቲካ ታሪካችንና ባህላችን የለውጥ እንቅስቃሴን  ህዝብ እንደ ህዝብ  እና  ያገባናል የሚሉ  የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶች ከመነሻው እስከ መዳረሻው በሚኖረው የእያንዳንዱ የሂደት ክንዋኔ ውስጥ  በሙሉ የነፃነት ፣ የባለቤትና የሃላፊነት ስሜት የሚሳተፉበትን ሁኔታ የማመቻችት ሳይሆን ይባስ ብሎ የመጨፍለቅ ስለመሆኑ ከራሳችን በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም ።  የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ሂደት ፣ አቅጣጫና ግብ የሚመሩትና የሚቆጣጠሩት ቀድመው መንበረ ሥልጣኑን የሚቆጣጠሩ የገዥ ቡድኖች በመሆናቸው የፖለቲካ ሥርዓት ታሪካችን ዴሞክራሲያዊና ሰባአዊ መብቶች እንዲያከብር  የሚታሰብ አልነበረም ።   በተለይ ደግሞ ያለፈው የግማሽ ምዕተ ዓመት የፖለቲካ ምዕራፋችን ፍፁም የሆነ ሰቆቃና ውርደት የተመዘገበት ዋናው ምክንያት የዴሞክራሲ ሀሁ የሆነው የተሟላና ያልተገደበ የተሳትፎ መብት (complete and non- constrained participation) ሥልጣን ላይ በወጡ ፖለቲከኞች እኛ ነን የምናውቅልህ ባይነት ስለተጨፈለቀ  ነው ።

ከዚህ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት የሚጠይቀን የጋራ ጥረት (ትግል) እጅግ ፈታኝ ነው ።  በመሆኑም ይህ የአሁኑ የለውጥ ሂደት ጅማሮ ግቡን መምታት ካለበት በእውን በሰከነ ፣ እንደዘመኑ በዘመነ (በሰለጠነ)፣ በእውቀት ላይ በተመሠረተ  ፣ታጋሺነትን በተላበሰ፣ ፍትህን እንጅ ቂምን ፍለጋ ላይ ባለተጠመደ  የአስተሳሰብና የተግባር መንገድ መጓዝን   ይጠይቃል ።

ገና ብዙ እልህ አስጨራሽ ሥራ እፊታችን ተደቅኖ ባለበት  የድል ነጋሪቱን ያለቅጥ ከማስጮሁ ቀንሶ ነጋሪት ሳይጎሰምለት  ብዙ በሚናገረው ተጨባጭ ድርጊት ላይ ባተኮረ ፣  የበደለን አካል “እየተበላሉ በመቀደስ” አስቀያሚ ፉከራ ሳይሆን  በሰለጠነና ፍትህን በሚያስተምር አኳኋን በመሞገትና በመቃወም መራመድ አዋቂነት ነው ። በደልን ተፀይፎ ተበዳዩን (ህዝብን) በመሪነት የተቀላቀለውን ደግሞ ወደ ፍፁምነት (አምልኮ) የተጠጋ ሙገሳ መለገስና ልክ በሌለው ጎሮ ወሸባዬ ማጅብ ሳይሆን ከተገቢው ድጋፍና አክብሮት ጋር ገንቢ የሆነ ሂሳዊ አስተያየት  በመለገስ እንድንራመድ  ግድ ከሚለን ወቅትና ሁኔታ ላይ መሆናችን ከምር ልብ ልንለው ይገባል  ።

ለዚህ ነው  አስቀያሚ  የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ትርጉም ባለው አኳኋን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተንና ለታሪክ መዘክርነት አስቀምጠን የታሪክ ባለቤት በሆነው የህዝብ ፣ ያገባናል በሚሉ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶች (ሰብሰቦች) ነፃና የተሟላ ተሳትፎ  ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ የሚያሸጋግር  ድልድይ መዘርጋት ፍፁም አስፈላጊ  የሚሆነው።

“ግንቡን አፍርሰን ድልድዩን እንዘረጋለን” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰሜን አሜሪካ ጉዟቸው መሪ መፈክር ሲሰሙት የሚፈጥረው ስሜት ድንቅ ነው። አስቸጋሪው ፈተና ያለው ወደ ዝርዝር (the devil is the details) የአተገባበር ሥራ ስንገባ ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ረገድ የሚነሳ ጥያቄ ቀላል እንዳልሆነ (እንደማይሆን) ስለሚገነዘቡ ይመስለኛል በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኢምባሲ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት በጣም አጭር ንግግር ውስጥ “አገራችን ወደ ሽግግርና ልማት ገብታለችና እንኳን ደስ ያላችሁ!”የሚለውን  የንግግራቸው ዋና መልእክት ያደረጉት ።

የጥላቻንና የመለያየትን ግንብ ማፍረስ ቀላል ባይሆንም ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊሥርዓት የሚያሸጋግረውን ድልድይ መዘርጋት ግን የበለጠ ፈታኝ በመሆኑ ስፋትና ጥልቀት ያለው የፖለቲካ ሥራ ይጠይቃል ። “ሽግግሩ በድርጅቴና በምመራው መንግሥት ከተጀመረ ሰንብቷል ። ማነኛውምንም መሳተፍ የሚፈልግ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅት (ስብስብ) ተቀብለን እያነጋገርን ለማሳተፍ ዝግጁዎች ነንና በዚሁ መሠረት እየመጣችሁ ተደመሩ” የሚለው ጥሪ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ታሪካዊ የሆነ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት እውን ለማድረግ ለምናደርገው ቅድመ ዝግጅት ( ሽግግር) በፍፁም የሚመጥን አይደለም።

በእውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባት የሚያሳስበን ከሆነ ለሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ምንጭ ሆኖ የዘለቀው ሥርዓተ ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በቀጠለበትና የተወሰኑ ከፍተኛ አባሎቹ  በአንፃራዊ መልኩ የሚያበረታታ የአስተሳሰብና የአሠራር ልዩነት አሳይተው ወደ መሪነቱ መንበር ስለመጡና ለስሜት የሚጥሙ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ንግግሮችን ስለአስደመጡን ፊደል ያልቆጠረው የዋህ የአገሬ  ህዝብ ብቻ   ሳይሆን በእውቀትና በልምድ መጥቂያለሁ  የሚለው የህብረተሰብ ክፍልም  “ከእነዚህ  መላእክተለውጥ ፖለቲከኞች ውጭ  ሌላ ፖለቲከኛ ማየትና መስማት አልፈልግም” የሚል አንድምታ ያለው አስተሳሰብ (አመለካከት) ሰለባ የመሆኑ ነገር ከምር ሊያሳስበን ይገባል ።

በእርግጥ ገና ጀመርን እንጅ ግማሽ ላይ እንኳ ባልደረስንበት የለውጥ ሂደት  ወይም አገርን እንደአገር ለማቆየት እና ከመከራውና ከውርደቱ ለመላቀቅ (ድርብርብ ትግል) ውስጥ ባለንበት  ወቅት የጎሮ ወሸባየው ትዕይንት በእጅጉ ከቁጥጥር ውጭ የሆነብን  ባለፉት አያሌ ዓመታት ከኖርንበት  ሁለንተናዊ የሰቆቃ ህይውት ጋር በንፅፅር እያየነው እንደሆን እረዳለሁ ።   በጅምሩም ቢሆን የደስታን ስሜት ከንቁ ተሳትፎ (ድጋፍ) ጋር መግለፅ አያስፈልግም የሚል የደንቁርና እና የጨለምተኝነት እይታ (አመለካከት) የለኝም። እያልኩ ያለሁት ደስታችንና ድጋፋችን ስንገልፅ  ያለንበትን መልካም አጋጣሚና ፈታኝ ሁኔታ መድረስ ከምንፈልግበት መዳረሻ ጋር ባገናዘበና እሱንም በሚመጥን አኳኋን መሆን አለበት ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለበርካታ ዓመታት በንቃት የተሳተፉበት እና በለውጥ አራማጅነት ቢሆንም አሁንም የሚመሩት ድርጅትና መንግሥት ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማው ሲል እንደአሸን የፈለፈላችውን የጎሳና የመንደር የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አምስት/ስድስት ተጠጋግተው ካልመጡ ለሽግግራቸው አስቸጋሪ እንደሆነ ነግረውናል ። ቁጥራቸውም ሰማኒያ እንደሆነ እንደ አዲስ ነገር ሲነግሩን እኛም አብረን  እንድንገረምና እንደቀላል ነገር እውነትም ስድስት ወይ ሰባት ቢበዛ ደግሞ ከአሥራዎቹ መብለጥ የለባቸውም  የሚል የቂልነት የፖለቲካ ፍርድ እንድንሰጥ  የጠበቁም ይመስላል። “በእኔ አሸጋጋሪነት አሻግራችኋለሁና የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነትን እርሱትና ተደመሩ” ሲሉ ለምን? እንዴት? በማነማን ወሳኝነትና ተሳትፎ  ? ብለን ሳንጠይቅ መደመሩን  አሜን ብለን እንድንቀበል የሚጠብቁም ይመስላል ። እንዲህ አይነቱ አቀራረብ ብዙም የሚያራምድ አይመስለኝም ።

 • የተሳሳተ የፖለቲካ አስተሳሰብን ወይም እምነትን (political illusion/delusion) አስወግዶ ገሃዱን የፖለቲካ ዓለም (real world of politics) ፈልጎ ማግኘትና በአግባቡ መረዳትን ግድ ይላል ። በአሁኑ ወቅት የአገራችን የማያወላዳው የፖለቲካ እውነታ (political reality) ለዘመናት በምንም አይነት ዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት የተከፈለበትን የለውጥ ሂደት ለትክክለኛ ግቡ የማብቃት ወይም ባለው ሥርዓት ሥር በሚካሄድ የማስተካከያ ለውጥ (reformism) የምትገኘዋን ጥቅም ተቀብሎ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እየናፈቁ የመኖር ጥያቄ ነው ። መኖር ከተባለ ።

ልክ በሌለው የስሜታዊነት ፈረስ የመጋለባችን ችግር እንዚህን ሁለት የለውጥ አካሄዶችና ግቦች በተመለከተ ያለብን የተሳሳተ አስተሳሰብ እያደር እንደመሻሻል እየባሰብን በመሄዱ ትክክለኛውንና ዘላቂውን የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ግብ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው መኖሩንም የረሳነው ይመስላል ። ይህ ደግሞ መሪዎችን ከማሞገስ (እንደማምለክም ይቃጣናል) አልፈን የለውጡ እንቅስቃሴ ግብ  የኢህአዴግን ሥርዓት ማሻሻል ነው ወይስ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ?  የለውጡ አራማጅ መሪዎቸ በድፍረት ለውጡን እንደተቀላቀሉ ሁሉ የበሰበሰ ሥርዓታቸው ተወግዶ በሽግግር (transition) ፖለቲካ አግባብ ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ   ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ የመግባቱን ሂደት ለመቀበልና ተገቢ ድርሻቸውን ለመወጣት በአስተሳሰበም ሆነ በድርጊት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?  ከሆነስ ምን ሊያደርጉ አስበዋል ? ብለን እንዳንጠይቅና ግፊት እንዳናደርግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮብናል ።

ለዚህ ነው የጥያቄዎቻችን ሁሉ እናት (the mother of all our questions) እጅግ አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበት ህዝባዊ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ግቡ (goal) መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እንጅ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የመከራና የውርደት ቀንበር አሸክሞን የዘለቀውን ሥርዓት የማደስ ወይም የማሻሻል ለውጥን (reformismን) እንኳን መቀበል ማሰብም አይቻልም የሚል መሆን ያለበት።

 • የሩብ ምዕተ ዓመቱ የመከራና የውርደት ሥርዓት ተወግዶ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓትን  እውን  ወደ እሚያደርገው የሽግግር ሂደት ለመግባት የሚያስችለውን ሥራ ጊዜ ሳያባክኑ መጀመርና ዝግጁ ማድረግ የግድ ነው ።  የፖለቲካ ተቀዋሚ ድርጅቶችን ሁሉ ለፖለቲካ አመችነት ( political convenience) ሲባል “ጥሪ አቅርበናል” ማለት የትም አያደርስም ።  ጥሪውን ተቀብለው ቢቀርቡም የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ጉልህ አይደለም ወይም ጨርሶ ደካማ ነው  ተብለው የሚታሰቡትን ደግሞ በክብር (በVIP) ከመቀበልና በየቢሮው ተቀብሎ በወቅታዊ ክስተቶች ላይ ሃሳብን ከመስጠትና ከመቀበል  (brief and debrief )  የዘለለ ተግባራዊ እርምጃን ጊዜ ሳያባክኑና ሰበብ ሳየደረድሩ  ተግባራዊ ማድረግን የምንገኝበት  ሁኔታ ግድ ይላል ።

የተሃድሶ ወይም የማሻሻያ ፕሮግራም  (reformism) የፖለቲካ ጨዋታ በጭራሽ የትግሉ መዳረሻ (ግብ) አልነበረም ። አይደለምም ። መሆንም የለበትም ። ከነእኩይ አስተሳሰቡና ተግባሩ ያረጀው የኢህአዴግ ሥርዓትጨርሶ ሳይወገድ ወይም የሚወገድበት ሁኔታ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሳይመቻች ከልክ ያለፈ   “የለውጥ ጎሮ ወሸባዬ” ማስተጋባት  ጊዜያዊ ስሜትን ከማርካት አያልፍም ።

ከዚሁ ገዥ ቡድን  የተለየ የመፍትሄ ሃሳብና መንገድ ይዘው የተነሱ  ፖለቲከኞች  ለውጡን  በመሪነት    ስለተቀላቀሉ እና በአንፃራዊ እይታ ይበል የሚያሰኙ እርምጃዎችን  በመውሰዳቸው ብቻ  “ የገዥውን ቡድን ሥርዓት  ነቅሎ ማስወገድ ሳያስፈልግ  በለውጥ ጠበል አጥምቆ ወይም አስጠምቆ  ” ወደ አዲስና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መለወጥ ይቻላል  የሚል ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

ስለሆነም  በአገራችን እውነተኛና ዘላቂ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ካለበት ኢህአዴግ በበላይነት በሚመራውና በሚቆጣጠረው የሽግግር ጨዋታ መሆን የለበትም ። የዶ/ር አብይና የቡድናቸው ጥረት የሚመሰገን ቢሆንም ድርጅታቸውና መንግሥታቸው እንደ ሥርዓት በሥልጣን ላይ እስከአለ ድረስ እውነተኛና አዲስ ህዝባዊ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይሸራረፍ እውን ይሆናል ማለት ለአገራችን የፖልቲካ እውነታ ጨርሶ  የሚመጥን አይደለም ። እናም “የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነቱን ግድ የሚል ሁኔታ አሁን የለም” የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ ጨርሶ አሳማኝነት የለውም ።

 • የኢትዮጵያ ህዝብ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸክሞ የዘለቀበት ዋናው ምክንያት (root cause) የህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ የፖለቲካ ፍልስፍና ፣ አስከፊ የዴሞክራሲ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና የአገር ሃብት ዘረፋ መሆኑ ጨርሶ የሚያጠያይቀን አይደለም ።

በሌላ በኩል ግን ቢያንስ አንፃራዊ አመኔታና የህዝብ ድጋፍ በነበራቸው ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ስብስቦች የጋራ ተልእኮና ፕሮግራም ዙሪያ የማይበገር ህዝባዊ ኅይል ለማደራጀትና ለማሰለፍ ባለመቻሉ የደረሰውን ሰቆቃና ውርደት ሁሉ አስተማሪነት ባለው  ጥልቅ ፀፀት መቀበል የታላቅ ፖለቲካዊ ሰብእና ባህሪ ነው። አሁንም በተስፋና በስጋት የተወጠረውን ፖለሊቲካዊ እውነታ ከስጋት አላቀን ተስፋውን እውን ወደ እምናደርግበት አቅጣጫና ግብ ለመውሰድ  ከልብ የመነጨ ፀፀትንና የማይታጠፍ ቁርጠኝነትን ግድ ይለናል ።

በነዚህ ሦስት ወራት ውስጥ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ከምር ለሚከታተልና ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ናፋቂ ለሆነ  የአገሬ ሰው በተቀዋሚው ጎራ ያሉ (አለን የሚሉ) ፖለቲከኞች ከመሪሩ የፖለቲካችን ተሞክሮ ተምረው ወደ የምር የፖለቲካ ሥራ አለመግባታቸው በእጅጉ  ቢያስጨንቀው በፍፁም የሚገርም አይደለም ።

የለውጡን እንቅስቃሴ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ አገር ቤት ገባን ያሉትም የኢህአዴግን “ጠቀም ያለ” የማሻሻያ ፕሮግራም ( reformism) ገድል በየአጋጣሚው ከመመስከርና ትሩፋቱን በፀጋ ለመቀበል በጉጉት ከመጠባበቅ የዘለለ የፖለቲካ ሥራ ሲሰሩ አለማየታቸው የማያሳስበን ከሆነ የምንመኘውና ታሪካዊ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል ማለት ከቅዠት አያልፍም ።

ሰሞኑን ደግሞ  በተቀዋሚው ጎራ ነን ከሚሉ ፖለቲከኞች ጀምሮ በአንዳንድ ፊደል የቆጠሩ (የተማሩ) ወገኖች “የዶ/ር አብይ አህመድና  የለውጥ አራማጁ ቡድን በራሱ የሽግግር መንግሥትነትን ሚና እያቀላጠፈው ስለሆነ የሚያስፈልገው እያመሰገኑ መደመር እንጅ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ጊዜው ያለፈበት የፖለቲካ ፋሽን ነው” እስከ ማለት በመሄድ  ቢያንስ በአግባቡና በሥነ ሥርዓት መስተናገድ ያለበትንና የረጅም ጊዜና የትየለሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የህዝብ ጥያቄ እንዳልነበርና እንደሌለ ሲያደርጉት ማየት ከየት ወደ የት እየሄድን ነው ? ያሰኛል ።

በዚህ አይነት የተሸናፊነትና የሥርዓት ማሻሻያ (reformism) ትሩፋት ተመፅዋችነት የፖለቲካ ሰብእና ወይም ቁመና እውነተኛ ህዝባዊ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ ከአገራችን ውስብስብና ባለብዙ ዘርፍ የፖለቲካ እውነታ አንፃር እውን ይሆናል ብሎ ለመጠበቅ ጠንካራ አሳማኝ ምክንያት የለንም።

በሽግግር መንግሥት ፉንታ በአገራዊ መግባባት አማካኝነት “አገራዊ ሸንጎ ቢጤ”   ተቋቁሞ በኢህአዴግ ለሚመራው የዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ ፕሮግራም (reformism) ጥናታዊና ሌሎች ግብአቶችን ይመግብ የሚል በራሱ በዴሞክራሲ ላይ ቀልድ መሰል ትንታኔ ማስተጋባት   ከህዝባዊው የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ አይነተኛ ግብ (ተልኮ) ጋር ፈፅሞ የሚጣጣም አይደለም ።

የአንድ ህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ስኬታማነት ዕውን የሚሆነው የእራሱ የሆነ እና በግልፅና በማይናወጥ መርህ ላይ የቆመ ስትራቴጅና ግብ ሲኖረው ብቻ ነው ። የህዝባዊው ተጋድሎ ምክንያት ( cause) የነፃነት ፣የፍትህ ፣ የሰብአዊ መብት/ክብር ፣ የዜግነት መብት ፣ የሰላም እና ኑሮን አሸንፎ የመኖር እድል እጦት ነው ። የዚህ እጅግ አስከፊ ማህበረሰባዊ ቀውስ ምንጩ (root cause) ደግሞ የማህበረሰቡ አባል የሆኑ አምባገነን ቡድኖች ወይም ግለሰቦች የሚዘረጉትና የሚቆጣጠሩት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥርዓት ነው ።

እናም የህዝባዊው ተጋድሎ ግብ (goal) ይህን የአምባገነኖች የሰቆቃና የውርደት ሥርዓት አስወግዶ ለሁሉም ዜጋ የሚበጅ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመመሥረት ነፃነትን ፣ፍትህን፣ ሰብአዊ መብትን/ክብርን ፣ እኩልነትን ፣ ዘላቂ ሰላምንና ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው ። አዎ! የዚህ ህዝባዊ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ መድረሻ (ግብ) በአይነትም ሆነ በይዘት የህዝብ እውነተኛ ለውጥ (transformational change) የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ እንጅ በነበረው ሥርዓት ማዕቀፍ ሥር ለውጥ ወይም ማሻሻያ (reformism) የማካሄድ ወይም የማድረግ ጉዳይ አይደለም ። መሆንም የለበትም።

 • በእውነት ከተነጋገርን ከአንዳንድ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ደርሰው ከተመለሱ ግለሰቦች የምንሰማው የምስክርነት ቃል እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴ ባህሪ፣ ሂደት እና የታለመለትን   ግብ ከመምታት አንፃር ሲታይ ሚዛናዊነትና  ሂሳዊነት  በእጅጉ የጎደለው ነው ።  በእንዲህ አይነት የፖለቲካ ቀኝትና አካሄድ ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግረንን ድልድይ መገንባት የሚቻል አይሆንም ።  የሄዱበትን እውነተኛ ተልእኮ ለጊዜው በትክክል የሚያውቁት እራሳቸው ቢሆኑም ተመልሰው የሚነግሩን መረጃ (information ) እና የሚያሰሙን አስተያየት በሰከነ ፣ በታቀደ ፣ በተቀናጀ ፣ በተደራጀ አኳኋንና  እና በማይታጠፍ  መርህ  ላይ ቆሞ   የለውጡን እንቅስቃሴ እውነተኛ መዳረሻው  (ግብ) የተዋጣለት ለማድረግ የሚያስችል አቅም በእጅጉ  ይጎለዋል።

በአገራችን የሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት የሚታዩ አወንታዊና   ፈታኝ ሁኔታዎችን  ከብዙ ዓመታት በኋላ የተከፈተውን የለውጥ በር በመጠቀም ወደ አገር ቤት ዘልቆ ለመረዳት መሞከርና አገር ምን ይመስላል? ምንስ እያለ ይሆን ? ምንስ እየተደረገ ነው? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ተገቢውን  ግንዛቤ ለማግኘትና የበኩልን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚታየው ተነሳሽነት  የሚበረታታና የሚደገፍ ነው ።  ይህን በጎ ነገር  ማጣጣል በጣም ስህተት ነው።

በሌላ በኩል ግን ከጉዞ መልስ የምንታዘበውን የምስክርነት አቀራረብና ይዘት መጠየቅና ሂሳዊ አስተያየት መስጠት በጣም ትክክል ነው ። የእነዚህ ደርሶ ተመላሾች አቀራረብና የአስተያየት ድምዳሜ ሚዛናዊና ሂሳዊ (balanced and critical) በሆነ እይታ ያለንበትን እውነታ ይገልፃል ወይ?  የምንደርስበትን መዳረሻስ (ግብስ) በማያሻማ አኳኋን ያመላክታል ወይ? ብሎ መጠየቅና መተቸት በእጅጉ ተገቢ ነው ።  ሂሳዊነትና ሚዛናዊነት የጎደለው “የምሥራቸ አብሳሪነት” እየታየ ላለው የለውጥ ሂደት ቢጎዳ እንጅ አይጠቅምም ።

 የለውጡ እንቅስቃሴ ዋናው ተልኮ (ግብ) እውነተኛና ትውልድ ተሻጋሪ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ነው ወይስ በኢህአዴግ የበላይነት በሚመራ ጥልቅ የማሻሻያ ፕሮግራም (reformism) የሚከናወኑ የለውጥ ትሩፋቶችን መቀራመት ነው? ብሎ መጠየቅ ግን ከቶውንም ሊታለፍ የሚችል አይደለም ። ለነዚህ ደርሶ ተመላሾችም መቅረብ ያለበት ጥያቄ ይኸው ነው ።

ከነዚህ አንዳንድ ደርሶ ተመላሾች የሰማነው (የምንሰማው) የለውጥ አራማጅ መሪዎችን ወይም ፖለቲከኞችን ያለምንም ሂሳዊ እይታ በማድነቅ ብቻ የተወሰነ አይደለም ። ደምሳሳ (unqualified) ምስክርነታቸውን ለማሳመን የተጠቀሙበት ማስረጃ አይሉት የተሳሳተ እምነት (illusion/false beleif)  በተለይ ለእንዲህ አይነት “ትንቢት/ንግርት”  በስሜቱም ሆነ በባህሉ ቅርብ የሆነውን የአገሬን ህዝብ አሳሳችነቱና አቅመ ቢስ የማድረጉ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ።    ” የአሁኑ ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኔስትር እየፈፀመ ያለው ገና በሰባት ዓመት የብላቴናነት እድሜው በእናቱ አንደበት የተነገረውን ትንቢት መሆኑን ተገንዝቤ መጣሁ “ ብሎ ምሥክርነት መስጠት ላለንበት የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ  ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም ።

ልጆቿን የምትወድና እንደማነኛዋም ለልጆቿ ትልቁን ነገር ሁሉ እንደምትመኝ እናት የጠቅላይ ሚኔስትር አብይ እናትም ለሚወዱት ልጃቸው  ለገንዛ አገሩ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ንጉሠ ነገሥት እንዲሆን ቢመኙ (ቢተነብዩ)  እና ጠቅላይ ሚኒስትርም ሲያምኑበትና ሲመኙት ኖረው አሁን ከሆነው ጋር አገናኝተው ትንቢት ተፈፀመ ብለው ቢያምኑ የሚገርም አይመስለኝም ። ቢያንስ በመብትነቱ መቀበል አያስቸግርም ።

ሌሎቻችን ግን የተነገረንን ከሁኔታዎች ጋር እያገጣጠምን ለማመን ብንፈልግ እንኳ    በዚያው ደረጃና መጠን  እናስተናግደዋለን እንጅ በይፋ  ለምናሳየው የፖለቲካ ድጋፍና አድናቆት እንደማሳመኛ ከምር ማቅረብ ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ የገሃዱ ዓለም ፖለቲካችን  አይጠቅምም ። ምክንያቱም በተለይ እንደኛ ለዚህ አይነት “እምነት/ንግርት” ስሜቱ ቅርብ ለሆነ ህብረተሰብ አሳሳች መልእክት አለውና ነው ።

የራሱ ጨካኝ ባለሥልጣኖች (ገዥዎች)  ያሸከሙትን የመከራና የውርደት ቀንበር ፈጣሪ ከእንስሳት ሁሉ ለይቶ በሰጠው ልዩ ችሎታ(ተሰጥኦ) መሠረት በሃሳብ ተግባብቶ፣ ተደራጅቶና በጋራ ተሰልፎ መስበር ሲያቅተው “የፈጣሪ ፈቃድ ባይሆን ነው” ፤ እንደአሁኑ የድርሻውን በመወጣቱ ፈጣሪ ረድቶት ያስመዘገበውን የለውጥ ጅምር ከገዥው ግንባር አስተሳሰብና አሠራር ተለይተው በመሪነት የተቀላቀሉትን ደግሞ “ከእግዚአብሔር የተላኩልኝ”  ለሚል ህብረተሰብ “አዎ ! እኔም በመስማት ብቻ ሳይሆን መሪዎችን በአካል የማግኘት ዕድል አግኝቼ እንደተረዳሁት እውነት ነው” የሚለው የምሥክርነት ቃል የሚያስተላልፈው መልእክት መሪዎችን በሰማያዊ ትንቢት (heavenly prophecy) ተገኙ የሚል አይነት ነው ። ይህ ደግሞ “ድከሙ እረዳችኋለሁ”ያለውን መልካም ምክር ብንደክምም ባንደክምም ትንቢቱ የተነገረለት መሪ መምጣቱ አይቀርም በሚል እራስን አቅመ ቢስና ባዶ ተስፋ ናፋቂ ያደርጋል ። ይህ  አይነት አስተሳሰብ (እምነት) በተራው መሪዎችን በአግባቡና ከምር ለመሞገት በሚደረገው የፖለቲካ መስተጋብር ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።

እንዲህ ላጠቃለው ፦

የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ግብ የኢህአዴግን የመከራና የውርደት ሥርዓት አስወግዶ የሁሉንም የፖለቲካ ኅይል (ድርጅት) አመለካከትና አቋም በትእግሥትና በጥበብ በሚያስተናግድ አኳኋንና ብሔራዊ (አገራዊ)  መግባባትን እውን በሚያደርግ  የመሸጋገሪያ ሥርዓት ወደ ዘላቂውና ታሪካዊው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና የማያቋርጥ ግንባታ መሸጋገር  ነው። ይህን መልካም እድል ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ትክክለኛ አቅጣጫና ግብ ለመወሰድ ከምንም በፊት በአገር ጉዳይ ሃላፊነትና ግዴታ አለብን የሚሉ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶች በነፃነትና በእኩልነት የሚሳተፉበት ጉባኤን (ኮንፈረንስን) የግድ ይላል። በእውነት ስለእውነት እየተነጋገርን ከሆነ  “እመኑኝ እኔ አሸጋግራችኋለሁ” የሚለውን ከቅንነት የመጣ ነው ብሎ መቀበል የሚቻል ቢሆንም ወደ መሬት ሲወርድ ግን ብዙም የሚያራምድ አይደለም ። እንኳን በእንደኛ አይነቱ የዘርና የቋንቋ ማንነት ፖለቲካ አራማጅ ገዥዎችና ፖለቲከኞች ባወሳሰቡት የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ይቅርና በመንፈሳዊው ዓለምም ለአንደበት የሚቀለውን ያህል ቀላል አይደለም ።

እናም የሚበጀው በተስፋና በሥጋት መካከል ያለውን የለውጥ ጅማሮ “እኔና ድርጅቴ ከሥጋት ወደ አስተማማኝየተስፋ ዓለም እያሸጋገርነው ነውና እየተደመራችሁ አግዙን” በሚል ፖለቲካ ጨዋታ በፍፁም እውን ማድረግ አይቻልም ። ቢሞከርም እንኳ ታጥቦ ጭቃነትን አያስቀርም ።

በመሆኑም ዘላቂውንና አስተማማኙን መንገድ ሁሉም ባለድርሻና ያገባናል የሚሉ አካላት ተከራክረውና መክረው በሚበጀው ላይ በመስማማት  ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግረውን ድልድይ ሊዘረጉት ይገባል ። ይኸ በደፈናው የእንደመር (የእንጨመር)  ቋንቋ አሁን ላለንበት እጅግ ግዙፍና ውስብስብ ለሆነ አገራዊ ጉዳይ (አጀንዳ) ይቅርና ከሽግግር በኋላ እንመሠርተዋለንና እንገነበዋለን ለምንለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ብዙም የሚያስኬድ አይደለም ።

 

Share.

About Author

Leave A Reply