‹‹ለሰውዬው ደህንነት ሲባል መንጌን ከማስገባታችሁ በፊት እኔን ማስወጣት ይቅደም›› (አሳዬ ደርቤ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የእኛ ሰው የሞተንና የሄደን ሰው መናፈቅ ልማዱ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ከሞተና ከአጠገቡ ከራቀ ደግ ስራውን እንጂ መጥፎ ተግባሩን አያስታውስም፡፡

ታዲያ ይሄን አመላችሁን ባውቅም ‹‹መንግስቱ ሐይለ-ማሪያምን ትናፍቃላችሁ.. ብዬ ግን አስቤው አላውቅም፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ስርዓት ብትንገሸገሹም ስንት የሚናፈቁ መሪዎች በተፈራረቀባት አገር ላይ ‹‹መንጌን ማዬት ትመኛላችሁ›› የሚል ግምቱ አልነበረኝም፡፡

በአቶ መለስ አስተምህሮት መሰረት የአገር ትርጓሜው ‹‹ሰው›› ነው፡፡ ከሚያደርጉት ተነስተን ‹ሰውነትን› ስንተረጉመው ደግሞ…. ‹‹በአካሉ ከእንስሳቶች የሚለይ፣ በብሄሩ ማንነቱ የሚለያይ፣ በአስተሳሰቡ ከጥበትና ከትምክህት ሃይሎች አጀንዳ የጸዳና የድርጅት አባል የሆነ›› የሚል ትርጓሜ እናገኛለን፡፡

ለመንግስቱ ሃይለማሪያም ደግሞ አገር ማለት ‹‹መሬት›› ነበረ፡፡ በስልጣን ዘመኑም ሲያስከብር የነበረው ወንበሩንና ድንበሩን እንጂ ህዝቡን አልነበረም፡፡ ሻዕቢያ ጋር ሲፋለምም ከኤርትራ ህዝብ መነጠል በላይ የመሬቱ መገንጠል ዋነኛ አጀንዳው ነበረ፡፡ (ህዝቡማ እንደ ፈርኦን ጦር ቀይ-ባህር ውስጥ ቢሰጥም እፎይታው ነው!)

ይሄም ሆኖ ግን ከስልጣኑ በተጨማሪ ለአገሩ ያለው ፍቅር ‹በመልክዓ-ምድሩ ላይ የተወሰነ› ቢሆንም… የአገራችንን አንድነት አስከብሮ መሰደዱ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ያስከበረውን መሬት ለዜጎቹ መቀበሪያ እንጂ መኖሪያ አላደረገውም፡፡

ይልቅስ ባስከበረው መሬት ላይ፡- ከጄኔራሎቹ እስከ ህዝቡ….. ከመኢሶን እስከ ኢሰፓ…… ከንጉሱ እስከ ቤተሰቦቻቸው…. ከወጣት እስከ አዛውንት… ሁሉንም ቀበረበት፡፡ (በዚህ ስራውም ከደርግ በላይ የተጠናከሩ እድሮች በየሰፈሩ እንዲቋቋሙ ማድረግ ቻለ፡፡)

.

ካነበብኩት ተነስቼ ስናገር መንግስቱ ሃይለ-ማሪያም ለእኔ ጨካኝ እንጂ ጀግና አይደለም፡፡ በተለይ በስልጣኑ ከመጡበት ወ/ሮ ውባንችንም የሚምር አይመስለኝም፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ሐረር ላይ ልጆቹና ሚስቱ ሲታገቱ በመደራደር ፈንታ ‹‹ቀቅላችሁ ብሏቸው›› ብሎ መመለሱን ማውሳት ይቻላል፡፡

እናም በዚህ ጭካኔው የህይወት ዋጋ ከጥይት ዋጋ በታች እስኪሆንበት ድረስ በአራቱም አቅጣጫ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ሲጨፈጭፍ ኖረ፡፡ በመጨረሻም ይህ በጭካኔ የተሞላ ድርጊቱ በህዝብ እንዲጠላ ስላደረገው ‹ምስራቅ አፍሪካን ያሽመደምዳል› የተባለው ‹ጦር› ሻዕቢያንና ወያኔን መቋቋም አቅቶት በራሱ ወታደርና በራሱ ጠመንጃ ለመሸነፍ በቃ፡፡ ብዙዎች ‹ራሱን ያጠፋል› ብለው ሲጠብቁትም ለእልፍ አዕላፍ ህዝብ የጋተውን የሞት ጽዋ ከሌላ ሰው እጅ’ም ሳይቀምሰው… በጭካኔው ሞራሉ የተሰበረና ለአምባገነኖች ጭቆና የሚመች ባዶ ዜጋ ከሙሉ አገር ጋር ለወያኔ አስረክቦ አመለጠ፡፡

ወያኔም ከእጇ የገባውን የተዳከመ ዜጋ እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለባለፉት 25 ዓመታት እግሯን ዘርግታ ‹‹ራበን›› ስንላት እርስ በርሳችን እያባላች ለመኖር ቻለች፡፡

እናም መንጌ ፈጽሞ ጀግና አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹ጨካኝነት› የጀግንነት ሳይሆን የፍርሐት ጽንስ ነው፡፡ ጀግና ምህረትን ሲያደርግ ፈሪ ሞትን ይግታል፡፡ መንጌ በቀልን የሚፈራ በመሆኑ ገድሎ አፈር ካልጫነብህ በቀር አቁስሎ አይተውህም፡፡ ሌላውን ተውትና ጄኔራል አማንን ለመግደል የሄደበትን ርቀት ስትገነዘቡ…. በበሰበሰ ስርዓት ውስጥ የራሱን ስም ከዳሽን ተራራ አፋፍ ላይ ለመስቀል ያስወገዳቸውን ምሁራን ስታስታውሱ… ‹በአገር ስም› የደበቀውን የወንበር ፍቅር ላለመነጠቅ ያጠፋቸውን ጓዶቹን ቆጥራችሁ አልጨርሳቸው ስትሉ…. ነጋሶ እንዳለው የመለስ የጡት አባት ‹መንጌ› መሆኑን ትረዳላችሁ፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ መንግስቱን ልንሰፍረው የምንችለው ሲመራው በነበረው ድርጅት እንጂ ሲክበው በኖረው ማንነት መሆን ባይገባውም…. በግላዊነቱም ሆነ በድርጅቱ ቁና ብንሰፍረው እብቅ እንጂ ወርቅ አናገኝበትም፡፡ ለአገሩ ከሰራው በጎ ስራ ይልቅ ለወንበሩ መከበር የፈጸመው መጥፎ ድርጊት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ (በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉትን መጽሐፍት እንዘርዝር ብንል የእኔ ግድግዳ ይቅርና የጃፋር መጽሐፍት መደብርም ሊበቃቸው አልቻለምና ማለፉ የተሻለ ነው፡፡)

(በነገራችን ላይ በሃገራችን ታሪክ ብዙ መጽሐፍ የተጻፈበት መሪ ‹መንግስቱ› ሲሆን ምንም ያልተጻፈለት መሪ ደግሞ ‹አባቱ› ነው፡፡ (ሐይለማሪያም ማለቴ ነው፡፡ Lol) እናም ይሄንን የታሪክ ክፍተት ለመሙላት ‹‹ያልተዘመረለት.. በሚል ርዕስ 400 ገጽ ያለው መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ስሆን ከሽፋኑ ውጭ ያሉት ገጾች ሌጣቸውን የተተው ናቸው፡፡)

ይሄን ብዬ ወደዋናው ሃሳቤ ስመለስ መንጌ በትውልዱ ላይ የፈጸመውን የሽብር ስራ ‹ለኢሰፓ› በመስጠት፤ ወታደሩ በዚያድ ባሬ ‹ወራሪ ጦር› ላይ የፈጸመውን ጀግንነት ደግሞ ለመንጌ ብቻ ነጥሎ በማስረከብ ለማጣፋት መጣጣሩ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ‹ግፈኛ› መሆኑን ‹ሙሰኛ› ባለመሆኑም ማጣፋትም ደስ አይልም፡፡ ይልቅስ በሚወደስበት ማዋደስ፤ በሚወቀስበት መውቀስ መልካም ነው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን መንጌን ለማወደስ አንድም በዘመኑ አለመፈጠር ሁለትም የተጻፈውን አለማንበብ የግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም የመንጌን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ እያነበቡ መንግስቱን ማድነቅ ማለት…. የቫንዳምን ፊልም እየተመለከቱ ከባላንጣው መወገን ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

.

የማያልቀውን ሃሳብ እንዲያልቅ፣ የማይጠቀለለውን ሃሳብ ጠቅለል ሳደርገው… መንግስቱ ከወያኔ ጋር ተጣልቶ የተሰደደ ‹ተቃዋሚ› ሳይሆን በህዝብ ተጠልቶ የተሰደደ መሪ ነው፡፡ የእጁን ሳያገኝ አምልጦ የሄደውም ስልጣኑን ከነጠቁት ሰዎች ሳይሆን ልጆቻቸው ከተገዱሉባቸው ቤተሰቦችም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህም ምህረትን ለማያውቀው ሰው ‹ምህረት ይደረግለት› ቢባል እንኳን ውሳኔው በዶክተር አቢይ ተረቅቆና በፌስ-ቡክ ሰራዊት ጸድቆ ተግባራዊ የሚሆን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ሌንጮ ለታን ለማስገባት ሲወስን ‹‹መቼም በዜናው ውስጥ እንጂ በግድያው ውስጥ አልተሳተፈም›› ብለው በማሰብ ሊሆን ይችላል፡፡

የመንግስቱ ጉዳይ ግን በነፍሰ-በላ እጁ ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸውን ባጡ ቤተሰቦች (ዜጎች) የሚወሰን ነው፡፡ ‹‹ይግባ›› ብላችሁ መወሰናችሁ ቀርቶ ማሰባችሁ በራሱ በወቅቱ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ነጻነት ሲታገሉ…. በአምባገነኑ መሪ ጨካኝ እጆች የተገደሉ ዜጎች የከፈሉትን መስዋዕትነት አፈር አልብሶ ሰውዬው እንዲራመድበት መፍቀድ ነው፡፡ (ይሄን ስል ግን በቀይ-ሽብር ስለተሰውት እንጂ በጦር-ግንባር ስለተገደሉት እያወራሁ አይደለም፡፡)

.

ለነገሩ መንግስቱም ቢሆን የዶክተሩን ሃሳብ ከልጆቹ አንደበት ሲሰማ… በሳቅ ውስጥ ሆኖ ‹‹ወደ የትኛው አገር?›› በማለት ያለምጣል እንጂ ብሔር የተጻፈበት መታወቂያ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አይደፍርም፡፡ ቢመጣም መሬቱን እንጂ ነጻነቱን እንደማያገኘው ይገነዘባል፡፡

ስለሆነም ‹‹ወደ አገርህ ትመለስ ዘንድ ተፈቅዶልሃል›› የሚለው ደብዳቤ ሲደርሰው ወይዘሮ ውባንችን ‹‹እነዚህ ሰዎች ተመለስ የሚሉኝ ህዝቡን ይዘው ወደ የት ሊሄዱ ነው?›› ብሎ በመጠየቅ ፈንታ ‹እንሂድ› ይላል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም መንግስቱ መግደልን እንጂ መሞትን ከማንም በላይ ይፈራል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply