ለተፈናቃዮች የዕርዳታ ገንዘብ ሲያከፋፍሉ የነበሩ የሴቭ ዘ ችልድረንና የኦሮሚያ ባንክ ሠራተኞች በእስር ከአንድ ወር በላይ እንዳለፋቸው ተሰማ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ለተፈናቃዮች የዕርዳታ ገንዘብ ሲያከፋፍሉ የነበሩ አራት የሴቭ ዘ ችልድረንና ሁለት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሠራተኞች፣ በሥራ ላይ እያሉ ታስረው ሳይለቀቁ ከአንድ ወር በላይ እንዳሳለፉ ተሰማ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ከየካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቀበሌ አካባቢ የዕርዳታ ገንዘብ ሲያከፋፍሉ በነበሩበት ወቅት፣ መያዛቸውንና እስካሁንም በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

የሴቭ ዘ ችልድረን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሕይወት እምሻው ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አራት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ይህ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ድርጅታችን በፌዴራልና በክልል ደረጃ ካሉ የመንግሥት አካላት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ በትብብር እየሠራ ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር ስላሉት ሠራተኞቻችንም ተገቢውን የሕግና ሌሎችም ድጋፎች በመስጠት ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሠራተኞቹ ስለታሰሩበት ምክንያትና ጥፋታቸው ምን እንደሆነ ለድርጅቱ ተገልጾለት እንደሆነ ተጠይቀውም፣ እስካሁን ድረስ በጥርጣሬ ከመያዛቸውና በእስር ላይ ከመሆናቸው በቀር ስለጥፋታቸው የተገለጸ ጉዳይ እንደሌለና ክስም እንዳልተመሠረተባቸው ገልጸዋል፡፡

ከምንጮች በተገኘው መረጃ መሠረት ሴቭ ዘ ችልድረን የዕርዳታውን ገንዘብ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በኩል የገንዘብ ዕርዳታ ለተፈናቃዮች እንዲደርሳቸው በገባው ስምምነት መሠረት፣ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን አፍዴር ወረዳና በአፋር ክልል አዋሽ ዞን ዋሽ በርታ አካባቢ ለሚገኙ የሁለቱም ክልል ተፈናቃዮች የዕርዳታ ገንዘብ ከባንክ ሠራተኞች ጋር በመሆን እንዲያከፋፍሉ የተመደቡ ነበሩ፡፡ ይሁንና በአፋር ክልል ዋሽ በርታ አካባቢ አለመግባባት በመፈጠሩ በዚሁ ግርግር ወቅት መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡

አብዱራህማን ሼክ መሐመድ፣ ሞሐመድ ሙሐመድ ኑር፣ ሱሌይማን ዓሊ እንዲሁም ማህዲ አወል የተባሉ አራቱ የሴቭ ዘ ችልድረን ሠራተኞችና ሁለት ስማቸው ያልተጠቀሱ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሠራተኞች፣ በ11 ወታደሮች ታጅበው የዕርዳታ ገንዘብ ሲያከፋፍሉ ውለው ማምሻውን ለእስር ስለመዳረጋቸው ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ስለጉዳዩ ከሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ከአፋር ክልልም ሆነ ከኦሮሚያ ክልል በስልክ መረጃ ለማግኘት ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ ብሔራዊ የሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ስለጉዳዩ ተጠይቆ መረጃው እንደሌለው፣ ሆኖም የድርጅቱ ሠራተኞች መታገት ወይም መታሰር እንደማይመለከተው አስታውቋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ የሠራተኞቹ መታገት በፌዴራልና በሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ደረጃ እንደሚታወቅ፣ መረጃዎች እንዲደርሳቸው ቢደረግም ከአንድ ወር በላይ ያለ ምንም ክስ መታገታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሚሊዮን በላይ የግጭት ተፈናቃዮች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ፣ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ለጋሾች ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ የበልግ ዝናብ በሚጥልባቸው እንደ ጌዴኦና ጉጂ ባሉ አካባቢዎች የተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል፣ ከወዲሁ ከፍተኛ ሥጋት መደቀኑን የሚያሳስቡ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply