ለአማራ ብሔር እንታገላለን ለምትሉ ከዳር ቆማችሁ ምን እየሰራችሁ ነው?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ለአማራ ብሔር እንታገላለን ለምትሉ ይሄንን ልምከራችሁ

  1. ዶር አብይ ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት በሀገር ውስጥ ያሉት ለኦሮሞ ብሔር የሚታገሉ ድርጅቶች ከኦህዴድ መሪዎች ጋር ሲመካከሩ ነበር። በውጪ ሀገር ያሉትም አንድ በአንድ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። የራሳቸውን መሰረት በማጠናከር የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ነው።
  2. በተመሳሳይ ሁኔታ አሥመራ ያለው የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትሕዴን/ እና አውሮፓ ያለውና በዶር አረጋዊ በርሄ የሚመራው ድርጅት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸው ተነግሯል።
  3. ግንቦት ሰባትም በይፋ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ለመንቀሳቀስ በዝግጅት ላይ ነው።

ለአማራ ብሔር እንታገላለን የምትሉ ቡድኖችና ድርጅቶች ግን ከዳር ሆናችሁ አንዳንዶቻችሁ እዬዬ ላይ ናችሁ። ሌሎቻችሁ የሚሆነውን ነገር በዝምታ በመታዘብ ላይ ናችሁ። የተወሰናችሁት ደግሞ የሚደረገው ነገር ሁሉ “የወያኔ ድራማ ነው” ብላችሁ “አማራው ከዚህ ይራቅ” እያላችሁ ነው።

ሀገር ቤት ያለውና አዲስ የተመሰረተው ድርጅት /አብን/ ገና ስለሆነ ብዙም ላይጠበቅበት ይችላል። በዲያስፖራ ሆናችሁ በአማራ ብሔር ሥም የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ የሲቪክ ማህበር መስርታችሁ ያላችሁ ሰዎች ግን ምን እየጠበቃችሁ ነው?ሁሉም የራሱን ጥቅም ለማስከበር በሚረባረብበት ወቅት ከዳር ሆኖ መታዘብና መቃወም ብቻውን እንታገልለታለን ለምትሉት ሕዝብ ምን ይጠቅማል?

ራሳችሁን አዘጋጅታችሁ ማድረግ ያለባችሁን ነገር ካላደረጋችሁ የሚጠብቃችሁ የለም። መብትህን በተፈጠረው አጋጣሚና ክፍተት ሁሉ ተጠቅመህ ታስከብራለህ እንጂ ለአንተ ብሎ ቆሞ የሚጠብቅ የለም። ነገ ሁሉም ቦታውን ይዞ በሚፈጠረው ለውጥ የብሔሩንም ሆነ የሚታገልለትን ወገን ድምጽ በሚገባ እንዲሰማና እንዲወከል ሲያደርግ እናንተ ኋላ እንዳትቀሩ።

ዶር አብይ የሚያካሂደው ለውጥ ጥገናዊ ይሁን መሰረታዊ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀሙ ይበጃል። እንደ ድርጅት ከሚገባው በላይ ተጠራጣሪ፣ ታዛቢ፣ የሴራ ትንተና እስረኛና አኩራፊ መሆን አይጠቅምም። ሀሳባችሁን ለማራመድ የግድ “መደመር” በሚባለው አካሄድ ውስጥ መግባት አያስፈልጋችሁም።

ከዳር ሆኖ መታዘቡን ምን አልባት በግለሰብ ደረጃ ያስኬድ ይሆናል። እሱም ብዙ ርቀት አያስጉዝም። ሌላውን ትቶ ቢያንስ የታየውን ትንሽ ተስፋ ለማዳፈን የሚፈልጉትን መቃወምና መታገልም ይጠይቃል። የፖለቲካ ድርጅት ወይም ሲቭክ ማህበር የመሰረተ ግን ከዚህ በላይ ይጠበቅበታል።

አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካ መሠረት የተመጣጠነ የፖለቲካ ድርጅቶች አሰላለፍ የሀይል ሚዛኑን ለማስጠበቅና ለውጡን ለማፋጠን ያግዛል። 1983 ድጋሚ እንዳይከሰተ ከፈለጋችሁ ቶሎ ንቁ።

(አቤኔዘር ቢ. ይስሀቅ)

 

Share.

About Author

Leave A Reply