ለአብኑ አደረጃጀት ኃላፊ ጋሻው መርሻ ከጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የተሰጠ ምላሽ በትህትና ብታጎነብስላቸውም አይምሩህም!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአብኑ አደረጃጀት ኃላፊ፣ ወንድሜ ጋሻው መርሻ የፃፈውን “ምክር” አነበብኩ። አብዛኛው ጥሩ ምክር ነው። ከአንድ የፖለቲካ አመራር የሚጠበቅ የሰከነ ምክር ነው። ውስጣችን መመልከቱ፣ ለጅብ ቀዳዳ አለመተው ትልቁ ቁምነገር ነው። የተጎዳነውም ለጅብ ቀዳዳ እየተውን ነው። ይህን የጋሻው መርሻ ምክር ከልብ መውሰድ ያስፈልጋል። አብዛኛው ፅሁፉ ተገቢ ምክር ሆኖ እያለ ሁለት ቦታ ላይ ግን ተገቢ ያልሆኑ አገላለፆች ተሰንቅረውበታል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጋሻው መርሻን ልሞግተው እወዳለሁ። የሙግቴ አላማ ሁለት ነው። አንደኛው የጋሻውን ፅሁፍ አጉል እየለጠጡ መጠቀሚያ ያደረጉትን በማየቴ ነው። ሁለተኛው የራሳችን መሪዎችም በአደባባይ መሞገት መልመድ ስላለብን ነው። ብዙዎች ይህን ያልተገባ ቃል አጠቃቀም እንዳይዋሱት ወንድሜን ጋሻውን በአደባባይ መሞገቱ ተገቢ ነው!

ጋሻው መርሻ ጥሩ መክሮ ያለ አግባብ ከሰነቀረው መካከል “የአማራ ፖለቲካ ማለቃቀስ ይበዛዋል” የሚለው ነው። ይህ ያለ አግባብ የተሰነቀረ አገላለፅ አላማው ከቅንነት የመነጨ ይሆናል። ለአማራ ሕዝብ ስነ ልቦና ከማሰብ ይሆናል። ነገር ግን ጋሻው ፖለቲከኛ ነው። ማን መጠቀሚያ ሊያደርገው እንደሚችል ማወቅ አለበት! በሁለተኛ ደረጃ አገላለፁ ስህተት ነው። የአማራ ፖለቲካ በዚህ መንገድ ሊገለፅ አይችልም። “ማለቃቀስ” ማለት ምንድን ነው? የአማራ ሕዝብ አዋጅ ወጥቶለት ይጥፋ አልተባለም ወይ? የትኛው ሕዝብ ነው እንደ አማራ ሕዝብ ስሙ ተጠቅሶ፣ ፖሊሲ ተነድፎለት ይጥፋ የተባለው? የአማራ ወጣቶችን ያህል በማንነቱ የተኮላሸው ማን ነው? አንድ ሁለት ተብሎ ይጠቀስ እስኪ። የአማራን ሕዝብ ያህል ርስቱን የተቀማ ማን ነው? የአማራን ሕዝብ ያህል ሆን ተብሎ እንዲደኸኝ የተደረገ አንድ ሕዝብ ጥራልኝ እስኪ ወንድማለም ጋሻው? በወልቃይት ተገድሎ የሚጎተተው፣ በጅምላ ቀብር የተቀበረው አማራ አይደለም ወይ? በራያ በታጠቀ ኃይል የሚደፈሩት የአማራ ሴቶች አይደሉም ወይ?

በመተከል በገዥዎቹ እገዛ በቀስት የሚወጉት የአማራ ሕፃናት አይደሉም ወይ? ሸዋ ላይ መንግስት አረመኔ ቡድንን መትረየስና ስናይፐር፣ ስንቅና አንቡላንስ ሰጥቶ የሚያዘምተው በአማራው ላይ አይደለም ወይ? ማንም ክልልና ልዩ ወረዳ ሲጠይቅ ከአካባቢው የሚያፀዳው ለዘመናት የኖረውን አማራ አይደለም ወይ? በጎንደር መከላከያ ተቋሙና አማራውን ሲፈርጁ የኖሩ ኃይሎች ከ80 ሺህ በላይ የአማራ ገበሬን አላፈናቀሉም? ብዙዎቹን አልገደሉም? የሱዳን መንግስት የጎንደር አማራ ገበሬን ሲያጠቃ ማን ደረሰ? የሚጋፈጡት፣ የሚታፈኑት፣ ከባድ መሳርያ የያዘን ኃይል በክላሽን ኮቭ የሚገጥሙት የእኔና የአንተ ወንድሞች አይደሉም እንዴ? የሚሞተውስ ማን ሆነ? አማራ በአማራነቱ መገደሉና መሰቃየቱ ብቻ አይደለም። እስኪ ቤንሻንጉል ውስጥ አማራውን ገድለው ምን ያደርጉታል ብለህ ጠይቅልኝ? አንባቢን ላለማሳቀቅ እኔ እዚህ ላይ አልፅፈውም። ባለፈው አመት ሁሉም የፖለቲካ እስረኛ ሲፈታ ስድስት ያህል አማራዎች ተለይተው ሳይፈቱ አሁንም ድረስ በእስር ላይ ናቸው። እኛ ግን ረስተናቸዋል። አሁን ደግሞ እንደ አዲስ እስር ተጀምሯል።

ያውም ቀርቷል በተባለው ፀረ ሽብር አዋጅ! መፅሐፍ የከተብክላቸው ፕ/ር አስራት ድርጅት የነበረው መአህድ አባላት አሁንም ትግራይ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ እየማቀቁ ነው። ታዲያ ለዚህ ሁሉ መከራ የእኛው ዘመን ትውልድ “ታግያለሁ” እያለ የጮኸው እጅግ ትንሽ ነው። ሕዝባችን ላይ ይህ ሁሉ በደል ተፈፅሞ እኛ ለማሰማት የምንሞክራት ድምፅ እጅግ ለሁሳሳ ናት። የአማራውን መከራ የማትመጥንና ለሌሎች ማሰማት ያልቻለች ድምፅ ናት! የእኔና የአንተ ትውልድ ሰነፍ ሆኖ እንጅ የአማራውን ስቃይ ዓለም ቢሰማው የምርም ያስለቅስ ነበር። የእኔና የአንተው ትውልድ ለአማራው ማልቀስ ቀርቶ ከለሁሳሳ ጩኸት ያለፈ ማሰማት አልቻለም። እንዲያውም ትልቁ የአማራ ፖለቲካ ችግር ይሄ ነው! በደሉ አልተነገረለትም፣ አልተጮኸለትም!

የዘመኑ ፖለቲካ የመረጃና የሪፖርት ፖለቲካ ነው። እስኪ ልጠይቅህ ወንድማለም! አብን የቆመለት የአማራን ርሥት የማስመለስ አላማን ለ28 እና ከዛ በላይ አመታት አንግበው በወልቃይት፣ በራያ፣ በደራ፣ በመተከል የተዋደቁትን አማራዎች፣ በዚህ ትግል የታፈኑትን፣ የተፈናቀሉትን ቁጥር፣ ማስረጃ እስኪ ወዲህ በል? እኛኮ የምንጮኸው የጥቂቶቹን ማስረጃ ብቻ ለአብነት ያህል ይዘን ነው። ጩኸታችን በጣም ለጥቂቶቹ ነው። ጩኸታችን የአጭር ጊዜ፣ እዚሁ ፌስቡክ ላይ የሚቀር እንጅ እንደ ሌሎቹ፣ በደንብ ጮኸው ለሕዝባቸው የዓለምን ሳይቀር ትኩረት ከሚስቡት አንፃርኮ እኛ እጅግ የወጣልን ሰነፎች ነን። የአማራ ሕዝብን ጮኸት መቼ ነው የጮህንለት? የአማራ ሕዝብ በዓለም ድሃ እንዲሆን መደረጉን የምንሰማውኮ ከዓለም አቀፍ ሪፖርት ነው። እኛ የከፋውን እውነት እያወቅነው፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያወጡት አህዝ የምንደመም የአማራ ሕዝብ ስቃይ እያየ አፋችን የለጎምን ሰነፎች ነንኮ። ታዲያ ለቅሶው የቱ ላይ ነው? እውን የአማራ ሕዝብ ተጩኾለታልን? በፍፁም! እንዲያውም ከገዥዎቹ ባሻገር ተቃዋሚ ነኝ ባዩም የአማራን ሕዝብ ጩኸት በማፈን የተካነ ነው። “ይህ ሁሉ ሲፈፀም ለምን ዝም አልክ?” እንዳይባል ይመስለኛል። ትናንትና “የአማራ ፖለቲካ ማለቃቀስ ይበዛዋል” ስትል ደስ ያለውም ለዚሁ ነው። “አማራ ምንም አልሆነም” ብሎ ዝም ማለት ይፈልጋል።

ሰሞኑን የሆነውን እንኳ ተመልከት። የአሥራት ጋዜጠኞች ታስረው የሚጠየቁት “ለምን ለአማራ ሕዝብ ድምፅ ሆናችሁ?” ተብለው ነው። ለምን የአጣዬውን ጉዳይ ዘገባችሁ፣ ለምን ገቢዎች ላይ የሚሰራውን ደባ አጋለጣችሁ፣ ለምን አዲስ አበባ ዙርያና ኦሮሚያ ላይ የሚፈፀመውን ዘር ተኮር ማፈናቀል አጋለጣች………ተብለው ነው። አሥራትኮ ለአማራ የጮኸው እጅግ ትንሹን ነው። ነገር ግን ለአማራ ድምፅ ማሰማት ወንጀል ሆኗል። ለዛም ነው በጥሩ ምክርህ መሃል የሰነቀርካት “ማለቃቀስ” ተገቢ አይደለችም የምህል። ለዛም ነው አንተ ለአማራ ሕዝብ ስትጮህ ሲያወግዙህ የነበሩት የገዥዎቹም ሆነ የሀሳዊ አንድነቱ ቡድን እየመዘዘ “የአማራ ፖለቲካ ለቅሶ ይበዛዋል” የምትለዋን ለማጮህ የሞከረው!

ሩቅ አንሂድ! ሰሞኑን የሆነውን እንኳ እንደገና ተመልከት። በአብዛኛው እየታሰሩ ያሉት ስለ አማራ የሚጨነቁት ናቸው። እየታሰሩ ያሉት ገዥዎቹ በየተቋማቱ የሚሰሩትን ውንብድና እና የአማራ መገፋት ያጋለጡ ናቸው፣ እየታሰሩ ያሉት የአማራ ሚዲያ መስራቾች ናቸው፣ እየታሰሩ ያሉት ለአማራ ኢኮኖሚ ይጠቅማል ያሉትን “መቶ ፕሮጀክት” ያቀዱ ወጣቶች ናቸው። እየተጠቁ ያሉት የአማራ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው። ለእነዚህ ሁሉ የሚገባውን ያህል ጮህን እንዴ? ምን አደረግን? ሰው ያለ አግባብ ያውም ማንነቱ ብቻ ተጣርቶ ሲታሰር ፍቱት ማለት ማለቃቀስ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? ሰው በማንነቱ ምክንያት ደብዛው ሲጠፋ (እነ ሊቁ እንደስራቸው አግማሴን የመሰሉት) ጠፍተውብናል ማለት ማለቃቀስ ነው ወይ? ሰው ከኖረበት ቀየው በማንነቱ ምክንያት ሲፈናቀል ጩኸት ማሰማት ማለቃቀስ ነው ይባላል? ህፃናት በቀስት ሲወጉ መቃወምስ ማለቃቀስ ነው እንዴ? እውን ለአማራው በደልና ስቃይስ ተጩኾለታል? አንድ መቶኛውን አልጮህንም! የእኔና የአንተ ትውልድ በዚህ በኩል የወጣልን ሰነፎች ነን!

ፖለቲካ ማለት የሆነውን ለሕዝብ ማሳወቅ ነው። ለ28 አመት በትግራይ ሸለቆዎች የታሰሩትን ለሕዝብ ማሳወቅ አለብን። እንዲፈቱ መወትወት አለብን። ያደረግነው ትንሽ ነው። አሁን ደግሞ ጭራሹን ረስተናቸዋል። እኛኮ ዝንጉዎች ሆነናል! የተነጠቁትን የአማራ ርስቶች ጉዳይ፣ በእነዚህ ርስቶች ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል ማሳወቅ ነበረብን። ደግሞምኮ በርካታ ማስረጃ እያለን በዝርዝር ማስረዳት አልቻልንም። እስኪ ባለፈው ወር መተከል ላይ ከተገደሉት በርካቶች መካከል የ15 ሰው ስም ወዲህ በል ወንድሜ ጋሻው? የአራት ሰው ጥርት ያለ መረጃ ስጠኝ እስኪ? መቼ ነው ስለ አማራ ሕዝብ የጮኽነው? መቼ በደሉ ተነገረለት?

የምክርህን አላማ በገደምዳሜው እረዳዋለሁ። ለአማራ ሕዝብ ስነ ልቦና ጥሩ አይደለም ለማለት ይመስላል። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። የአማራን ሕዝብ ስነ ልቦና ማቃለል ይመስላል። አብንን ጨምሮ እንደ አዲስ የአማራው ፖለቲካ ለመነቃቃት የበቃው አማራው ከደረሰበት መካከል እጅግ ትንሹ በአደባባይ ከተነገረው በኋላ ነው። አማራ “ቁርጡን ንገሩኝ” ብሎ ቆራጥ አቋም የሚይዝ ሕዝብ እንጅ እውነታው ስለተነገረው የሚሸሽ ሕዝብ አይደለም። ሌላው ግን ሞራላዊም አይደለም። መተከል ውስጥ የአማራ ህፃናት በቀስት ልባቸውን እየተወጉ የእነዚህ ስቃይ ሲነገር ስነ ልቦናው የሚጎዳ አማራ ካለ እሱ የአባቶቹ ልጅ አይደለም። አማራ የወንድሙን ሞት ሲሸፋፍኑት የማይወድ “ንገረኝና ይቁረጥልኝ” የሚል ጠንካራ ስነ ልቦና ያለው ሕዝብ ነው። ነገር ግን በእኛ ስንፈት እንዲቆርጥለት አላደረግንም። የራሱን ሆን ተብሎ የተሰራ ድሕነት እንኳ ሰምተን የምንነግረው ከዓለም አቀፍ ሪፖርት ነው። መቼ ነው ስለ አማራ የጮህነው ወንድማለም?

አባቶቻችን “በሽታውን ያልተናገረ መድሃኒት አይገኝለትም” ይላሉ። የአማራው ፖለቲካ መድሃኒት ያላገኘው አማራው ቁስሉ፣ ስቃዩ፣ በደሉ በሚገባ ስላልተነገረው ነው። አማራው እንደ አዲስ አንገቱ ቀና አድርጎ የነበረው የሆነው በትንሹ ተነግሮት ስለነበር ነው። ቆርጦለት ለመታገል ስለጀመረ ነበር። “ምንድን ነው የሆነው?” ከሚል ቁዘማ እውነታው ተነግሮት ስለቆረጠ ነበር የእናንተ ጩኸት ብአዴን የሚባለውን የአማራን ጩኸት ሲያፍን የኖረ ድርጅት ሳይቀር ያነቃው። ትንሽ በጣም ትንሽ ጩኸት ነው ብአዴንን እናንተ የምትጮሁለትን የርስት ጉዳይ ደፍሮ እንዲይዝ ያደረገው። እጅግ በጣም ትንሽ ጪኸት ተሰምቶ ነው ብአዴንም የአማራ ሕዝብ በሕግና በአዋጅ ተጠቅቷል ብሎ ይይዘዋል ተብሎ የማይታሰበውን የሕገ መንግስት “ይሻሻል” ጉዳይ አጀንዳ ያደረገው። ትንሽ ጩኸት ነች አማራው ጠላት ነው ሲባልበት ከነበረው አካባቢ ሳይቀር “አማራው የሀሰት ትርክት ተጠቂ ነው” ተብሎ እንዲታመን ያደረገው። ይህን ያመጣው የአንተና የጓደኞች ትንሽ ጩኸት ነው። እናንተ ትንሽም ቢሆን ስትጮሁ የአማራውን መከራ ላለመስማት ጆሮውን የደፈነ ሞልቷል። ይህ የእኔና የአንተ ትውልድ ነው ፖለቲካውን ያበላሸው። ራሱ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ላለመስማት ጆሮውን በመጠርቀሙ በስነ ልቦና እየተጎዳ ያለ ይኖራል። እውነታውን ያወቀው ግን ትንሽም ብትሆን ድምፅ እያሰማ ነው። ቆርጦለታል፣ አማራ ደግሞ ቁርጡን ካወቀ ቆራጥነት አይታጣውም። አሁን አማራው አንገቱን ቀና እንዲያደርግ የሆነው ጆሯቸውን ከፍተው የሕዝብ በደል ስምተው የቆረጠላቸው ስለተገኙ ነው። ግን አሁንም ይቀራል። አሁንም የሕዝቡን ስቃይ ላለመስማት ጆሮውን የደፈነ አለ። ጩኸቱ ለሁሳሳ ስለሆነ ያልደረሰው አለ። ለሁሳሳዋ ጩኸት በሌላ በዓድ ጩኸት ስለታፈነች የማይሰማው ብዙ ነው።

ከአማራው አልፎ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በትንሹ ቢያምኑም አማራው በሀሰት የተወገዘለት ዓለም አልሰማም። አሁንም አማራው ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል አልቆመም። በደንብ አልጮህብለትም! እናንተ ለሕዝብ ስትጮሁ ብዙ ውግዘት የገጠማችሁ የአማራውን መከራ ማፈን የሚበዛ በመኖሩ ነው። ወደ ውስጣችን እንይ ያልከውን ምክር ልውሰድና አንድ ጉዳይ ልጨምር። እናንተ እጅግ ትንሽ ጩኸት ስታሰሙ አጀንዳ የሆናችሁት ብቻችሁን ስለተጋለጣችሁ፣ከእናንተ ከፍ ያለ ማስረጃ ይዞ የሚሞግት በመጥፋቱ ነው። የእኔና የአንተው ትውልድ ስንትና ስንት መረጃ እያለው የሕዝቡን መከራ በሰነድ ይዞ መሞገት፣ መጮህ ባለመቻሉ ነው። ሀገር ለሀገር እየተንከራተቱ በሕዝቡ ላይ የደረሰውን በደል ሲያሰሙ የነበሩት የእነ አክሊሉ ሀብተወልድ ልጆች እጅግ ብዙ መረጃ ቢኖራቸውም እንደ አባቶቻቸው ለሕዝብ መጮህ ስላልቻሉ ነው!

በመልካም ምክርህ ውስጥ ስለአማራው ጠላት የሰነቀርካት ያልተገባች አገላለፅም ላይ ተመሳሳይ ተመሳሳይ ስህተት አለ። በእርግጥ አማራው መጀመርያ ማጥራት ያለበት ራሱን ነው። ከዚያ ሲያልፍ ግን በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫ አማራ የሚሳደደው አጥፍቶ አይደለም። በጠላትነት ስለተፈረጀ፣ ጠላቱም ብዙ ስለሆነ ነው። እስኪ ዘወር ዘወር ብለህ ለአንድ አፍታ ተመልከት። ከጉራፈርዳ እስከ ጅማ፣ ከቤንሻንጉል እስከ ራያ፣ ወልቃይት፣ ደራ፣ አዲስ አበባ………አማራውን የሚያጠቃውን ኃይል አስብ። ከዛም ከጥሩ ምክርህ ውስጥ የሰነቀርካቸውን ሁለት አገላለፆች አስባቸው! አማራው ጠላት ሞልቶታል ማለት ግን ቤቱን ማየት የለበትም ማለት አይደለም። አንድን ቤተሰብ ከውጭ ከሚመጣ አውሬ በላይ የራሱ ችግር ሊያጠፋው ይችላል። ግን በጠላት ተከብቦ ማቃለልም ያከስራል እንጅ አይጠቅምም።

ወንድማለም ጋሻው ሆይ! አማራማ አልተጮኸለትም። መጮህ ብቻ ግን ዋጋ አለው ማለት አይደለም። መጮህም ወደ መደራጀት ይገፋል። አብን ከመጮህ፣ ከአማራው ስቃይ ብዛት አይደለም የተወለደው? በእርግጥ ትንሽም ቢሆን ጩኸት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ወደ ተግባር መቀየር አለበት። ብዙ ብዙ ይቀራል!

ወዳጄ ጋሻው ሆይ! አማራማ ጠላቱ ብዙ ነው። እስኪ ምሽት ላይ ካሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል የተወሰኑትን ብቻ ከፍተህ ተመልከት። ብዙዎቹን አማራው ላይ ሲዘምቱ ታገኛቸዋለህ። ከዛም ምክርህ ውስጥ የሰነቀርካቸውን ሁለት አገላለፆች አስባቸው! ምክሩ ጥሩ ሆኖ አገላለፆች ስህተት ናቸው። እነዚህን ስህተቶች የሚጠሉህ፣ ለአማራ ስትጮህ ያብጠለጠሉህ “ትክክል ናቸው” እያሉ እየተጋሩህ ነው። እኔ ወንድምህ ደግሞ እውነታውን እነግርሃለሁ። ዛሬ ስህተቶችህን ያወደሱልህ ነገ ብትታሰር ደስ የሚላቸው፣ በውድቀትህ ላይ የሚፎክሩ፣ እኔም አንተም እንደወንድሞቻችን ወደ ጨለማ ቤት እንድንጋዝ የሚፈልጉና የሚጥሩ ናቸው። እኔ ግን የሚጠቅምህን፣ የሚጠቅመንን እነግርሃለሁ! አገላለፆቹ ስህተት ናቸው! አማራ አልተጮኸለትም! የአማራውን ያህል ጠላት የበረከተበት የለም። አማራው በአንድ ሀሙስ የሚጠፋ ሕዝብ አይደለም። ግን በየቀኑ እየሞተ ነው። መጥፋት ደግሞ የሚለካው በተቀላ አንገት ብቻ አይደለም። እንዲጠፋ በሕግ ከታወጀበት በርካታ ሀሙሶች አልፈዋል። አማራ እንዲጠፋ ከተሰራበት በርካታ ሀሙሶች ተቆጥረዋል! አማራ ሲፈናቀል፣ በቀስት ሲገደል፣ በጅምላ ሲቀበር በርካታ ሀሙሶች አልፈዋል። አማራ የዘር ማጥፋት ሲታወጅበት፣ የዘር ማጥፋት፣ ዘር ማፅዳት ሲፈፀምበት በርካታ ሀሙሶች አልፈዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply