ለአፄ ዮሐንስ አራተኛ የመታሰቢያ ሐውልት ሊሠራ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለነበሩት አፄ ዮሐንስ አራተኛ የመታሰቢያ ሐውልትና ሙዚየም በትግራይ ክልል ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ማህበር አስታወቀ፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መክብብ በላይ ሰሞኑን እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ለኢትዮጵያ አንድነት የታገሉና በድል የታጀበ ታሪክ ያላቸው ቢሆኑም ታሪካቸው ጎልቶ አልወጣም፡፡ በስማቸውም መታሰቢያ ሐውልት አልቆመላቸውም፡፡ ማህበሩ ሀገራቸውን ያገለገሉ ባለታሪኮች እንዲታወሱና ሥራቸውም ለትውልድ እንዲተላለፍ የመታሰቢያ ሐውልቱ እንዲሠራ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ መክብብ እንደገለፁት በጥቂት ሰዎች ተነሳሽነት ማህበር ተመስርቶ እንቅስቃሴው ቢጀመርም ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ አባላት ያሉበት ማህበር ተመስርቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ የመታሰቢያ ሐውልታቸው እንዲቆም በታሰበበት የንግሥተ ሳባ ትውልድ ቦታ ተምቤን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በአካባቢውም 56ያህል ገዳማት መኖራቸውን የገለፁት አቶ መክብብ፤ ታሪክ ላላቸው ሰዎች ሐውልት ቢሠራና ሁለገብ ሙዚየም ቢገነባ ታሪክን ለትውልድና ለሌሎችም ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ለቱሪዝም መስህብ ሆኖ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ማህበሩ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ከተምቤን አስተዳደር 350ሺ ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡንና ዓላማውን የሚደግፉ ሰዎችን የማሰባሰብ ሥራ መሥራቱን፣ እቅዱን ለማሳካትም ከግማሽ ሚሊዮን ብር ያላነሰ እንደሚያስፈልና ግንቦት 12/2010ዓ.ም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለማካሄድ መታቀዱን አቶ መክብብ ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ ዘመን

Share.

About Author

Leave A Reply