Thursday, January 17

ለውጥን አለመቀበል እራሱ ያለመለወጥ ምልክት ነው፡፡ (በድሉ ዋቅጅራ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ በእኛ እድሜ እንኳን ታሪክ እንዳልነበረ ሆኖ ሲለወጥ እማኝ ሆነናል፡፡ ታላቋ ሶቭየት ህብረት በገነባት ፓርቲ ተበታትናለች፡፡ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የባህር በር የነበራት ሀገራችን፣ ለወደብ ድርጎ ለየጎረቤቶቿ ተንበርካኪ ሆናለች፡፡ . . . ለውጥ ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው፡፡ ከ530-470 አ.አ. የኖረው ፈላስፋ ሄራክሊተሰ (Heraclitus)፣ የተፈጥሮን ሁለንተናዊ ለውጥ በዥረት መስሎ ባስረዳበት አገላለጹ ይታወቃል፤ ‹‹We both step and do not step in the same river. We are and are not.››
.
. . . . አንድን ዥረት በሴከንድ ልዩነት እንኳን ሁለቴ ብንሻገረው፣ የተሻገርነው የተለያየ ወንዝ ነው፡፡ ዥረቱ የሚወርድበት መልካ፣ የተሻገርንበት ድልድይ፣ ወይም የተረማመድንበት አለት ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፤ የተሻገርነው ውሀ ግን የተለያየ ነው፡፡ ተለውጧል፡፡ ለውጥ የዩኒቨርስ አዎንታዊ ህግ ነው፡፡ በተቃራኒው አለመለወጥ በዩኒቨርስ ውስጥ፣ አሉታዊ የውድቀት መንገድ ነው፡፡ . . . ከዚህ አንጻር ለውጥን አለመቀበል እራሱ ያለመለወጥ ምልክት ነው፡፡
.
ሮናልድ ሬጋን እና ጆርጅ ቡሽ የአንድ ሀገር ተካታታይ መሪዎች ነበሩ፡፡ ጆርጅ ቡሽ ታላቋን ሶቭየት ህብረት በተመለከተ ከቀዳሚያቸው ከሮናልድ ሬጋን የተለየ አቋም በመከተላቸው፣ ሚ. ጎርቫቾቭን በማግባባት ታላቋ ሶቭየት ህብረት እንድትፈርስ ሆነ፡፡ ይህም በበኩሉ ለበርሊን ግንብ መፍረስ ምክንያት ሆነ፡፡ የአሜሪካ መንግስት (ሪፐብሊካን ወይም ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች) እና የሶቭየት ኮምኒስት ፓርቲ የወንዙ ውሀ የሚወርድበት መልካ – ሜዳና ተረተር እንጂ፣ የወንዙን ውሀ አይደሉም፡፡ በዚያን ወቅት የየወንዙ ውሀዎች ቡሽና ጎርቫቾቭ ነበሩ፡፡ ዛሬም ውሀው የሚወርድበት መልካ አልተለወጠም፤ ውሀዎቹ ግን ትራምፕና ፑቲን ናቸው፡፡ በዚያው ሀገር፣ በዚያው ፓርቲ፣ በዚያው ቤተመንግስት – በዚያው ዥረት ነገ ሌላ ውሀ ይፈስበታል፡፡ ለውጡ የግድ የመሪዎችን ለውጥ የሚፈልግ ላይሆን ይችላል፡፡ መሪው ሳይለወጥ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ፖለቲካዊ ለውጥ ሊገኝ ይችላል፡፡
.
. . . ባልተለወጡ ፓርቲዎች ውስጥ የመሪዎች መለወጥ ለውጥ ያመጣል፤ መሪዎች ሳይለወጡ ፖርቲ ቢለወጥ ግን ለውጥ አይመጣም፡፡
.
እስካሁን እንደተመለከትኩት የዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ለውጡ የምርም ይሁን የቀልድ ብዙ የሚያስጨንቅ አይመስለኝም፡፡ የጠ/ሚው ለውጥ በየሀገሩ ዜጎቻችንን እንደበግ እየነዱ የሚያስሩ መንግስታት፣ አክብረውን ከየእስር ቤቱ እስከፈቱዋቸው ድረስ፣ ታች . . . መንጋው ድረስ ወርደው ሰውነታቸውን እስካሳዩ ድረስ፣ በብሄር ተከፋፍላ ጥፋት አፋፍ ያለች ሀገራችንን እስካረጋጉ ድረስ፣ ኢህአዴግ በ27 አመት ያደረሰውን ጥፋት አረክሳለሁ ብለው በአደባባይ ቃላቸውን እስከ ሰጡ ድረስ. . . ለውጡ አዎንታዊ የተፈጥሮ ህግ ነውና ልንደግፋቸው ይገባል፡፡ ሰውየው በአዎንታዊው የለውጥ መሰላል ወደላይ እየተረማመዱ ነው፤ ከዚህ የለውጥ መሰላል እንዳይንሸራተቱ መደገፍ አለብን፡፡ ምክንያቱን ከመሰላሉ ያዳለጣቸው፣ የተንሸራተቱ ጊዜ ከነበሩበት መሬት እንኳን ለመቆም እድል የሚያገኙ አይመስለኝም፤ ‹‹ድንገት ቢያድጣቸው – ቢንሸራተቱ›› ተብሎ ትልቅ አዘቅት ከስራቸው እየተዘጋጀ ይመስለኛል፡፡ . . . ደግሞስ ለውጡ እውነት ሆኖ እንዲጎለብት፣ መደገፍ እንጂ፣ ብዙ ወገኖቻችን የህይወት መስዋእትነት የከፈሉበትን ለውጥ፣ ለእሳቸው አስታቅፈን፣ ‹‹የእውነት ነው፤ ውሸት ነው›› ድብብቆሽ ስለምን እንጫወታለን?

Share.

About Author

Leave A Reply