ለጎዳና ተዳዳሪዎችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የተጀመረው ፕሮጀክት ፈተና ገጥሞታል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና ቀጥታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማደራጀት በቅርቡ ሥራ የጀመረው ፕሮጀክት ፈተና እንደገጠመው ተነገረ፡፡ ፕሮጀክቱ በመጀመርያው ዙር አምስት ሺሕ ዜጎችን ለማንሳት ዕቅድ ይዞ 3,147 የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አረጋውያንን፣ ሠርቶ ማደር የማይችሉ አካል ጉዳተኞችንና የመሳሰሉትን ስምንት ማዕከላት ውስጥ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ መካከል 324 የሚሆኑት በቋሚነት የሚረዱበት ሌላ ተቋም ሲገቡ፣ በማዕከሉ መቆየት አንፈልግም ብለው የወጡ እንዳሉ የሚናገሩት የትረስት ፈንዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አየለ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ በተጀመረ ሰሞን የነበረው መነቃቃት በአሁኑ ወቅት መቀዛቀዙን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በከፈተው የትረስት ፈንድ የባንክ ሒሳብ፣ ማኅበረሰቡ እንደ መጀመርያው ገንዘብ እያስገባ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡ የባንክ ሒሳቡ ለሕዝብ ክፍት ከሆነበት ጥር አጋማሽ እስከ የካቲት መጨረሻ ጥሩ መነቃቃት ኖሮ ጠቀም ያለ ገንዘብ መሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸው፣ በዚህ ወቅት የተሰበሰበው ገንዘብ መጠን ምን ያህል መሆኑን ግን ጠቅለል ያለ መረጃ እንዳልደረሳቸው አስረድተዋል፡፡ እጃቸው ላይ የሚገኘው ከማኅበረሰቡ የተሰበሰበ ገንዘብ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 5 እስከ 28 ቀን 2019 ያለው መሆኑን፣ ጠቅላላ ድምሩም 253,556 ብር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ድጋፍ የማሰባሰብ ኃላፊነት የተሰጠው የትረስት ፈንዱ ጽሕፈት ቤት ቶሎ ባለመደራጀቱና በማዕከላቱ የሚገኙትን የማደራጀቱ ተልዕኮ ከተጠበቀው የበለጠ ጊዜ በመፍጀቱ፣ ከማኅበረሰቡ የሚገኘውን ድጋፍ ለማጠናከር የሚከናወነውን ሥራ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከ3,000 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ ቀላል አይደለም፡፡ ጤና፣ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ማሟላት ቀላል አይደለም፡፡ ትንሽ ነገር ሲጎድልባቸው ያኮርፋሉ፣ ይበሳጫሉ፤›› ሲሉም ጽሕፈት ቤቱ የተጣለበት ድርብ ኃላፊነት ጊዜ የማይሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ በተጀመረበት ወቅት የነበረው መነቃቃት አሁን ላይ ላለመኖሩ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው፣ መጀመርያውኑ ፕሮግራሙ ለፖለቲካ ፍጆታ ታስቦ እንጂ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ባለመቀረፁ ነው በማለት አንዳንዶች ይተቻሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ፕሮግራሙ ሲጀመር የነበረው ግርግርና ማስታወቂያ ወዲያው መክሰሙ ነው፡፡ በተቃራኒውም ፕሮግራሙ ሲጀመር የነበረው የሚዲያ ሽፋን ከሌሎች ክልሎች ሳይቀር የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ከተማዋ እንዲፈልሱ አድርጓል በማለት ይተቻሉ፡፡

በመጠለያዎቹ ከሚገኙ ዜጎች ዘላቂ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ወደሚያገኙበት፣ ከተለያዩ ክልሎች የመጡትን ደግሞ መጠነኛ ድጋፍና የአዕምሮ ዝግጅት እንዲያገኙ እየተደረጉ ወደመጡበት እንዲመለሱ የማድረግ ዕቅድ ነበር የተያዘው የሚሉት አቶ ሁነኛው፣ ወደ ክልል እንዲመለሱ ማድረግ ላይ ችግር እንደተፈጠረ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሥር ከሥር ወደ መጡበት እየመለስን ሌሎች ድጋፍ የሚሹትን ከጎዳና ለማንሳት ነበር ዕቅዳችን፡፡ ከክልል የመጡትን ከ45 ቀናት እስከ ሁለት ወራት እኛ ዘንድ እንዲቆዩና ወደ መጡበት እንዲመለሱ ብለን ነው የተነሳነው፤›› ብለው፣ ክልሎች ወስደው እንዲያቋቁሟቸው የታሰበ ቢሆንም ክልሎች ብዙ ጫና እንዳለባቸውና አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ይኼንን ማድረግ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ወጣቶቹ በማገገሚያ ማዕከላቱ መቆየት ካለባቸው ጊዜ የበለጠ እንዲቆዩ መደረጋቸውን፣ ይህም 5,000 ዜጎችን ለማደራጀት መነሻ ብሎ መንግሥት የበጀተላቸው ገንዘብ በምግብና በመሳሰሉት ወጪዎች እንዲመናመን እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በቀን ለአንድ ሰው 50 ብር ወጪ ተይዟል፡፡ ወጣቶቹ በማዕከላቱ በቆዩባቸው ጊዜያት ጫማና ልብስ ከተያዘው በጀት ውጪ ተደርጎ ለሁለት ጊዜያት ተገዝቶላቸዋል፡፡ ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስም እንዲሁ መሸመቱን፣ ከዚህ በተጨማሪ የመጠለያ ማዕከላት ለማስገንባት ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች እስከ 30 ሚሊዮን ብር ከዚሁ 100 ሚሊዮን ብር በጀት ላይ መያዙን አቶ ሁነኛው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን ከተያዘው በጀት ላይ 40 ሚሊዮን ብር ለልዩ ልዩ ተግባራት ሲውል፣ በዚህ አካሄድ የቀረው ገንዘብ ብዙ የሚባል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

ጎዳና ላይ የወደቁና በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍ የማደራጀት ዕቅድ የወጣው፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በዓለም ባንክ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሥር እንደሆነ አቶ ሁነኛው አስታውሰዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ የጀመረው ሐሳብ ሳይሆን የቻለውን ለማድረግ የገባበት ነው ብለዋል፡፡ የዓለም ባንክን ፕሮግራም ለማስጀመር የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply