ለ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስቸኳይ ምክር (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ውድ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ

ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን በአለዎት ፍቅር የተነሳ ስልጣን ከያዙ ሶስት ወር እንኳን ሳይሞላ እርስዎና ባልደረቦችዎ የፈፅማችሁአቸውን ታላላቅ ተግባሮች አሁን እኔ እዚህ አልዘረዝራችውም። እርስዎ፣ እቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የለኮሳችሁት ኢትዮጵያዊነት እሁን ወደ ፍቅርነት አየተለወጠ እየነደደ ነው። በፍቅር ላይ ደሞ እርስዎ መደመርን፣ እንዲሁም ይቅርታ እና ምህረት ማድረግን ጨመሩባቸው። በጣም ደስ ይላል። ዳሩ ግን የእርስዎ ፍቅር፣ መደመር፣ ይቅርታና ምህረት የማይስማሟቸው የጭለማ ሰራዊቶች መኖራቸውን በቀደም እለት ለእርስዎ አነጠጥረው በህዝብ መሀል ያለርህራሄ ባፈነዱት ቦንብ እና በአፈሰሱት ንፁህ ደም ይፋ አድርገዋል።

 

ከቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ፡ የምንኖረው አብሪት፣ ትእቢት፣ጭካኔ፣ ሴራ እና ግድያ በሞሉበት ዐለም ውስጥ ነው። ይህ የጭለማ ዐለም የፍቅርን፣ የይቅርታን እና የምህረትን ብርሃን ጠልቶ ሊያጠፋው እንደሚጥር አሙን ነው። ሆኖም ቦምቡ የተወረወረው ከላይ ለእርስዎ ቢሆንም ከውስጥ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለማጥቃት እና አሁን የተቀዳጁትን ፍቅር፣ አንድነት እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመንጠቅ የታቀደ እኩይ ሴራ ነው።

እርስዎ የአበሰሩቸው ይቅርታና ምህረት በመሰረቱ መልካም ቢሆኑም ይቅርታ እና ምህረት የሚደረጉት ስለበደሉ ተፀፅተው ይቅርታን እና ምህረትን ለሚጠይቁ ሰዎች ብቻ ነው። አጥፍቻለሁ ይቅር በሉኝ፣ ማሩኝ የሚሉ ሳይኖሩ ይቅርታ እድርጌላችኋለሁ፣ ምሬአችኋለሁ ማለት ትርጉም የለውም። በዳዮቹ ስንትና ስንት ግፍ ፈፅመው ሳይፀፀቱ በቀላሉ ምሬአችኋለሁ ሲባሉ ስላልተቀጡ ታብየው አዲስ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                               ለማድረስም ሲጥሩ እየታየ ነው። ይህ እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫው ምህረት፣ ፍቅር እና መደመር በሚሰበክበት ሰዐት የተወረወረው ቦምብ እና አሁንም በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱት ትርምስና የህዝብ ፍጅት ናቸው። እውነተኛ ምህረት ማድረግ የሚገባው በዳይ በይፋ ወጥቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጠ እንደተደረገው ወንጀለኛም ፊት ለፊት ቆሞ “አጥፍቻለሁ፣ ተፀፅቻለሁና ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ስለ ፍቅር በስመአብ ይቅር፣ እባካችሁ ማሩኝ” ሲል ብቻ ነው። ከዛ በፊት ግን ወንጀል የፈፀሙትን ገዳይዎችን እና ሌቦችን ጨምሮ፣ ለፍርድ ማቅረብ ግድ ይላል።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                        አነዚህ ግለሰቦች ከአሉበት ተስብስበው ተይዘው ወንጅላቸው በህግ ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ አዘብጥያ መውረድ አለባቸው። ከዛ በኋላ ተፀፅተናል፣ አጥፍተናል ሲሉ ጉዳያቸው ተምርምሮ ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል። ስለእዚህ ከምህረት ፍርድ መቅደም አለበት። መቼም እንደ እግዚአብሄር መሀሪ የለም። ሆኖም አግዚአብሄር እውነተኛ ፈራጅ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በግፈኛች ላይ የፈረደ ቢሆንም ትልቁን ፍርድ ለ ዐለም ፍፃሜ ጊዜ አዘግይቶታል። በዚያን ጊዜ ተደብቀውም ሆነ በጉልበታችውና በገንዘባችው ተማምነው ወንጀል የሠሩትን አጋልጦ ይፈርድባችዋል። እግዚአብሄር መሀሪ እንደመሆኑ መጠን ፈራጅም ስለሆነ እርስዎም የእሱን ፈለግ ተከትለው ፈራጅም መሆን ይገባዎታል። ምህረትና ፍርድ እይነጣጠሉምና። ስለእዚህ በየቦታው እይዞሩ የእርስዎን አስተዳደር ለማሳጣት ፀጥታ የሚያደፈርሱትን እና ጎሳን በጎሳ ላይ እያነሳሱ ባለፉት 27 ዓመታት እና አሁንም ደም የሚያፋስሱትን እብሪኞች መቅጣት ይገባዎታል። እንዲህ ዐይነቶቹ እብሪተኞች ፍቅርና ምህረትን አንደ ፍርሃትና ልምምጥ ስለሚቆጥሩት እነዚህ መልካም ቃላት ያስቋቸዋል እንጂ እልባቸው ውስጥ አይሰርፁም።

ደህንነቶን አስመልክቶ፡ ምንም በህዝብ ፍቅር ነድው ያለ እጃቢና ጠባቂ በህዝብ ውስጥ ለመደባለቅ ቢወዱም እርስዎ የጀመሩትን የለውጥ ሂድት የሚቃወሙ ግለስቦችም ሆኑ የተደራጁ ኃይሎች በህይወቶ ላይ አደጋ ለማድረስ ምን ጊዜም ወደ ኋላ አይሉም። ይህም እባባሌ በ ቦምቡ ውርወራ ተረጋግጧል። እርስዎም ክእዚህ ክስተት ተምረው ለወደፊቱ ራስዎን ይጠብቁ። በደህነነት ተግባር በብቃትበየስለጠኑ ታማኝ ሰዎችይታጠሩ። እርስዎ የሚወክሉት ራስዎን ብቻ ሳይሆን 100 ሚሊዎን ህዝብን ነው። እርስዎ አንድ ነገር ቢሆኑ የሚጎዱት እርስዎና ቤተስቦችዎ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብና እርስዎ ሊተገብሩት የያዙት ራዕይ ጭምር ናቸው። ራስዎን ጠብቁ ሲባልም እንደነ ኮረኔል መንግሥቱ እና አቶ መለስ ዜናዊ መንገዱን ሁሉ አዘግተው፣ ዜጋው ወደ እርስዎ አቅጣጫ እንዳያይ ፊትን ወድ ግድግዳ ማስዞርና ህዝብን በፍርሃት ማስራድ አይደለም። ተግቢውን እና ዜጎችን የማያሸማቅቅ ለህይወቶ የሚገባውን ጥበቃ ያገኙ ዘንድ ግድ ይላል። ለወደፊቱ ሀገር ከተረጋጋች በኋላ ጥበቃዎን ጥቂት ላላ ማድረግ ይችላሉ። አንደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ እና ከሳቸው ቀዳሚ እንደነበሩት ነገሥታት ማለት ነው።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ በጥቂት የክቡር ዘብኛ እንጋቾቻችው ታጅበው ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ህዝብ ያሉበትን ስፍራዎች ይገበኙ ነበር። አቶ መለስ ግን ይህ የበጎ አድራጎት ሥራ ከኮንትራቴ ውጪ ነው ይል ነበር። አፄ ኃይለሥላሤ ግን ክፍለሃገር ሲሄዱ ጠባቂዎቻቸውን በርቀት ወደ ኋላ አስቀርተው ወይም ወፍራሞቹ አንጋቾቻው እያለከለኩ ሽንቃጣው እሳቸው ፈጠን ብለው ሌራመዱ ተስተውለዋል። አፄ ምንይልክም ያለ ፍርህት ከህዝባቸው መህል ይገኙ ነበር። ዜጎቻቸው በእጅ ሥራ እንዲሰለጥኑ ይፈልጉ ስለነበር በተለይ በአንዳንድ ምሽቶች ህዝቡ ፈጠራውን ይዞ እመንገድ ዳር ተኮልኩሎ ሲጠብቃችው እሳቸው በቅሎ ላይ ተፈናጠው ፈጠራቸውን እያዩላችው ለፈጣሪዎቹ የሚገባቸውን ሽልማቶች ይሰጡ ነበር። አጴ ቴዎድሮስም ምንም ራሳቸው ብርቱ ጦረኛ ቢሆኑም ጋሻ ጃግሬዎች እና ታማኝ ዘበኞች ነበሯቸው። ከእዚህ በተያያዘ የእንድ ጎበዝ ጠባቂያቸው ታሪክ ይወሳል። ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሶው ወንጀል ፈፅሞ ሊገደል ሲወሰድ ንግሡን ያይና “ንጉሥ ሆይ ያስጥሉኝ፣ እኔ ጎብዝ ሰው ነኝ፣ አንድ ቀን አጠቅሞታለሁ፣” እያለ ሲጮህ አፄው ልቀቁት ብለው እስጣሉት። ከዛም “እስቲ እውነት ጎብዝ ከሆንሽ እኔን ታግለሽ ጣይኝ፣” ብለው ታገሉት። ሰውዬው አልወድቅ ብሏቸው ብዙ ከታገሉት በኋላ እሳቸው ጣሉት። ጥንካሬውንም ዐይተው፣ “እውነትም ጎበዝ ነሽ”፣ ብለው ሞቱን ሽረውለት ጠባቂያቸው አደረጉት። ታዲያ አንድ ቀን እሳችው ከፊት፣ ይህ ጠባቂ ከኋላ ሆነው ሲራመዱ የሰጉ ሰዎች ጃንሆይ እርዎ ከኋላ ይሁኑ ቢሏቸው “ወግድ እሱ ጎበዝ ነው፣ ገበዝ ሰውን ከኋላ አያጠቃም፣ ሰውን ሳያየው ከ ኋላ የሚ ያጠቃ ፈሪ ብቻ ነው፣” አሏቸው።

በጥንት ዘመንም ሆነ አሁን እውነተኛ የስልጣን ወንበር ላይ የሚቀመጠው አንድ ሶው ብቻ ነው። በአንድ ወንበር ላይ ብዙ ሰዎች አይቀመጡም። ወንበሩም ቢሆን ላንድ ሰው ብቻ ስለታነፀ። በድሮ ዘመን የኢይዮጵያ ነገሥታት ስልጣን ላይ ለመፅናት የሚጠቀሙበት አንድ ዘዴ ነበራቸው። ስልጣን ተቀናቃኛቸው ሊሆኑ የሚችሉትን ልዑላን ዘመዶቻቸውን በተራራ ውስጥ በተመሸገ ዋሻ ውስጥ ያስሯቸው ነበር። ተራ እና እድል የገጠመው ተመርጦ ከዛ ውስጥ ተጠርቶ እስኪነግሥ ድረስ። ይህ ባይደረግ ኖሮ ሁሉም እነግሣለሁ እያለ አየተላለቀ፣ ህዝብን እያጫረሰ አገር ባመሰ ነበር። በአሁኑ ሰዐት ኢትይዮጵያን መምራት የሚገባን ልዐላን እኛ ነነ እያሉ ከእዚህ ቀደም የመሪነት ዕድል ቢግጥማቸውም ስልጣናቸውን ለጥፋትና ሙስና ያዋሉት ግለሶቦች አሁንም በዙሪያዎ አሉ። ከፍ ብዬ እንደጠቅስኩት፣ እርስዎ በፍቅር ተሞልተው ይቅርታ ይደረግላችው ብለው ቢለምኑም እነሱ እርስዎን እንደ የዋህ ቆጥረዋል። እነዚህን እገር የሚያሸብሩ ግለሰቦች አገር እስኪረጋጋ ድረስ ከህዝብ እና ከራስዎ መሀል ገለል አድርገው ፀጥታ እና ሰላምን ቢያስከብሩ ለኢትዮጵያ ይበጃታል፣ ብዬ ደግሜ አበክሬ እመክሮታለሁ።

ስለመደመርም አንድ ቃል ማለት አፈልጋለሁ። እርስዎ የእመጡት መደመር እጅግ መልካም ነው። እንደመርሆ ከመቀናነስ መደመር ወይም መደማመር ይሻላል። ቢቻልም ደግም ከመደመር ይልቅ መዋሃድ ይመረጣል። ለጊዜው ስለመደመር እናውሳና አብዛኛው ህዝብ መደመርን ቢወድም መቀነስን የሚፈልጉ እና መደመርን የማይሹም አንደ አሉ ማስተዋል ይገባናል። አነዚህ ፍጡራን ከባህሪያቸው የተነሳ በምንም ታምር አይደመሩም። እነሱን በግድ ለመደመር መሞከር የጠራ ውህ ውስጠ ጋዝ ጨምሮ በግድ ለመደባለቅ መሞክር ነው። ስለእዚህ የማይደመሩትን ችላ ብሎ ውይም ቀንሶ የሚደመሩትን ብቻ መደመር ነው። ስትደመር እስቲ ተመርመር ብሎ እንደመር ከሚሉትም ውስጥ በየ ስርዐቱ እየተሽሎከለኩ ገብተው ዐይናቸውን በጨው ታጥበው ሃገርን የጎዱ አድርባይዎች አጣርቶ ገሸሽ ማድረግ አለመበለጥ ነው። በቀውጢ ቀን ከህዝብ ገፊዎች ጋራ ተደምረው ሀብትና ስልጣን ሲያካብቱ የኖሩትን ምንደኞች ለማተባቸው ከቆሙት እኩል በሉ ተደመሩን ብሎ መጋበዝ ፍትህን ማጓደል እና ፍርድን መበደል ነው። ስለ እዚህ፣ ከመደመር ይቅደም መመርመር።

 

ሌላ የምመክርዎት ጥቂት ጉዳይዎች አሉ። እነሱም ስለ እብሪተኛው አብዲ ኢሌ፣ ስለ ፖሊሶች እና ወታድሮች ተሀድሶ፣ ስለከልል መቅረት፣ ስለ ህዝቦች መፈናቀል፣ የነፍስወከፍ መሣሪያን ስለማስፈታት፣ ያልተፈቱትን ስለ ማስፈታት፣ ስለ ትግራይ ህዝቦች ሁኔታ፣ ትግራይ ውስጥ ባዶ 6፣ በተባለው ማጎሪያ ስለታሰሩት፣ በትግራይ ስለሰፈሩት 200 000 ወታደሮች፣ እንዲሁም እዛ ስለሚገኙት የጦር መሳሪያዎች፣ በተጨማሪም ተቆፍሮ ስለ ተገኘው ድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ፣ እና ከኢትዮጵያ ተሰርቀው በውጭ ሀገራት ስለተጠራቀሙት ዶላሮች ናቸው።። ስለ ድሬደዋ ከተማም የምሎት ነገር አለኝ። በመጨረሻም በመላው ዐለም ያሉትን የኢትዮጵያን ዐምባሳደሮችን ወደ ኢትዮጵያ ስለመጥራቶ ነው።

የቀድሞ የስልክና ኤሌክትሪክ ምስሶዎች ተካይና ነቃይ ነበር የሚባለው አብዲ ኢሌ በሚያስተዳድረው የሱማሌ እና ኦሮሞ ህዝቦች ላይ ብዙ ግፍ እየፈፀመ እንደ እለ፣ እንዲሁም ህዝቡ በነቂስ ውጥቶ ይነሳልን ማለቱን እርስዎ የሚያውቁት ነው። 15 000 የሚደርሱ የታጠቁ ልዩ ኃይሎች ስለአሉኝ በእነሱ ተማምኜ እገነጠላለሁ እያለ ሲዝት እርስዎ በፍጥነት ወደ ጂጂጋ ሄደው ከ አቶ ለማ ጋራ እጅ ለእጅ አያያዘው አንደ አባበሉት አይዘነጉትም። ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች ለምእተዓመታት በፍቅር ጉርብትና ሲኖሩ ሁለቱን አጣልቶ አንድ ሚሊዎን ኦሮሞዎችን ማፈናቀሉን እና አነዚህ ምስኪን ኦሮሞዎች እስካሁንም ድረስ ወደ ቀድሞው መሬትና ንብረታቸው እንዳልተመለሱ ከእርስዎ የተስወረ አይደለም። በእነዚህ ምክንያቶች ተንተርሰው ይህን እብሪተኛ ከስልጣኑ አንስተው የጅጅጋን፣ የኦጋዴንን እና የድሬደዋን ህዝብ እፎይ ያሰኙት። የሚመካበትንም ልዩ ኃይል ወደ መደበኛው የኢትዮጵያ ጦርሰራዊት ውስጥ ያካቱት። ፓርላማንውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተውም እሱና ሌሎችም እንገነጠላለን እያሉ የሚያስፈራሩበትን አንቀፅ 39ን ሰርዘው አልቦ ያድርጉት። ባልና ሚስት ካልተስማሙ ሊፋቱ ይችላሉ የሚለው የብልጠት አነጋገር በሃገር ጉዳይ ላይ አይሠራም።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                              የብሄሮችን መብት እስከመገንጠል እንቀበላለን ብሎ ወረቀት ላይ ያሰፈረው የቀድሞው ሶሽየት ኅብረት ኮሚኒስት መሪ ዮሴፍ ስታሊን አይደለም የሌላው የራሱ ክፍለሃገር ግሩዚ እንኳን እነገነጠላልሁ ብላ ብትነሳ የማነሽ ቀልደኛ ወዴት ሸርተት ሸርተት ብሎ ድባቅ መትቷቷል። አብርሃም ሊንከንም አሜሪካ እንዳትገነጠል ጦርነት አካሂዶ በሚሊዎኖች የሚቆጠሩ እሜሪካኖች አልቀው አሜሪካን ከመከፈል አድኗታል። እንዲሁም በዐለም ላይ ገናና እንድትሆን እድርጓታል። የጀርመኑ ኦቶ ፎን ቢስማርክ እና የጣልያኑ ጋሪባልዲም የተበታተኑትን ጀርመንን እና ጣልያንን አንድ አድርገው ዛሬ ታላላቅ ሃገሮች ሊሆኑ ችለዋል። ለኢትዮጵያም ቢሆን ከመገነጣጠል ይልቅ በእኩልነት ላይ የተገነባ ባህልን እና ቋንቋን የሚያክብር ለክፍላተ ሃገር ውስጣዊ ነፃንትን የሚፈቅድ ፧ሪጅናል ኦቶኖሚ የሚበጅ ስለሆነ ባስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ጠርተው ውይይት ከፍተው እና አባላቱን አሳምነው እንቀፅ 39ን እንዲፍቁ እመክሮታለሁ። ከዛ በኋላ ማንም እየተነሳ እገነጠላለሁ እያለ ቡራ ከረዩ አይልም።

ፖሊሶችና ወታደሮችም ከአዲሱ ለውጥ ጋራ አብረው እንዲራመዱ መታደስ አለባቸው። ዛሬ የአሉት በተለይ ፌዴራል የሚባሉት ፖሊሶች ሰውን ከመደብደብና ከመግደል በቀር ምንም ሙያ የላቸውም። እኔ ሳድግ ድሮ የማውቃቸው በፖሊስነት ተግባር የሰለጠኑት እውነተኛ ሰላማዊ ፖሊሶች ግን ዜጎቻቸውን አክብረው ስርዐትን ተከትለው ነበር ፀጥታን የሚያስከብሩት። መልካም ከመሆናቸው የተነሳ

ፖሊስ፣ ፖሊስ የነፃነት፣የሰላም ስንሰለት፣ተብሎ ተዘምሮላቸው ነበር። እነዚያ ምርጥ ፖሊሶች በጣም ልዩ እና አደገኛ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር የጋዝ ጭስ እንጂ ሜዳ የወጣ ማንኛውም ህዝብ ላይ ጥይት አያርከፍክፉም ነበር። ሰው በአንድ ወንጀል ከተጠረጠረም በፖሊስ ጠቢያ ከታገተ ከ 24 ሰዐቶች በኋላ ወይም ከዘገየ በ48 ሰዐቶች ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ያቀርቡ ነበር። ሰውን ከቤቱ ለመያዝም ሆነ የቤት ፍተሻ ለማድረግ ህጋዊ የመጥሪያ ደብዳቤ ይዘው ሲመጡም ታይተዋል። የአሁኖች አንደዚህ ለህግ እና ስርዐት ተገዢ እንዲሆኑ በአስቸኳይ መታደስ አለባቸው።

የጦር ወታደሮቹም ቢሆኑ ተግባርና ሚናቸውን ሰተዋል። የወታደር ግዴታው የሀገር ዳር ድንበርን መጠበቅ እና ጠላት ድንበር ሲጥስ መከላከል ነው። በክተማ ውስጥ መልከስከስ እና በባዶ እጃቸው ሆነው መብታችን ይክበር የሚሉ ሰላማዊ ዜጎችን መረፍረፍ አይደለም። የዚህ ዐይነቱ ድርጊት የወታደርን ግዴታና ተግባር የሚያዋርድ እና የሚያሳፍር ነው። ሰለዚህ አሁን በየከተማው እያውደለደሉ ሰላማዊ ዜጎችን የሚጨርሱት ነፍሰ-በላዎች የተሀድሶ ስልጠና ተሰጥቶአችው ባስቸኳይ ወደ ዳር ድንበር ተልከው በጠረፍ ጠባቂነት ተግባራችው መሰማራት ይገባቸዋል።

ክልል የተባለው ነገር በፍፁም መቅረት አለበት። ክልል የሚለው ቃል ራሱ ለአፍ ይቀፋል። በድቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን ለማግለል ነጮች ፈጥረውት የነበረውን አፓርታይድ ስርዐትንም ያሳስባል። ይህ ቋንቋን አንተርሶ የተተገበረው ክልል በውስጡ የሚኖሩትን ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ተወልደው ባደጉበት ወይም እንጀራ ፍለጋ መጥተው በሰፈሩበት ቦታዎች ላይ እንዳይኖሩ ሲያስፈናቅላቸው እና ሲያስገድላችውም ተስተውሏል። በአብዛኛው የእዚህ ሰለባ የሆኑትም ቀደም ሲል አማሮች፣ አሁን ደግሞ ኦሮሞውች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአሻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ተዘዋውረው እና ተቀምጠው ያለ ምንም ከልካይ ሰርተው እንዲኖሩ ይህ ከልል የተባለው ክፉ የዘረኝነት እገዳ ክምድረ ኢትዮጵያ ተጠርጎ ተጥሎ በክፍለሃገር አስተዳደር መተካት አለበት። ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ትግራይ፣ ሸዋ፣ ሲዳሞ፣ ኢሊባቡር፣ ሃረር፣ አርሲ፣ ወዘተ በማልት ኢይዮጵያን አንደጥንቱ በመልክአ ምድር አቀማመጥ መሰረት ከፋፍሎ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብቱ ተክብሮለት በአማረው የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ፣ በማንነቱ መድልዎ ሳይደረግብት የመኖር እና የመሥራት ነፃነቱ እንዲከበርለት ያሻል።

ክቡርነቶ እንደመር፣ እንፋቀር፣ ይቅር እንባባል ብለው ሰላምና ፀጥታን ለማፈን ሲጣጣሩ፣ ፍቅር እና ይቅርታን የሚጠሉ፣ ሌብነታቸውን እና አምባገነንነታቸውን የሚያስቀረውን እርስዎ የጀመሩትን ለውጥ የሚቃወሙ ኃይሎች ቦምቦችን እንደቆሎ በየኮሮጆው አየሞሉና አስከ አገጨጫቸው ድረስ የነፍስወከፍ መሳርያ በየቤታችው ቆልለው አገሪቷን አያደሙ እና በብዛትም ሊያደሙ አያሴሩ መሆናቸው ከ አርስዎ የተሰወረ አይደለም። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ምስኪኑን ህዝብ ሳይጨርሱና ሳያጫርሱ መሳሪያችውን ድንገት ሳያስቡት ከየቤታቸው መልቀምና ሀገር እስኪረጋጋ ድረስ እነሱን ጠራርጎ እውሀኒቤት ማቆየት በጣም ያስፈልጋል። ይህን ነገር ችላ ሳይሉ በቶሎ እርምጃ ይወሰዱ። እነሱን በሚያስሩብት ጊዜ ደግሞ እነሱ በግፍ ለዓመታት ያሠሯቸውን አሁንም በየእስር ቤቱ የሚገኙትን ያልታወቁ እና የተረሱ ዜጎች በፍጥነት ተፈተው ክቤተሰቦቻቸው ይደባለቁ ዘንድ ያስታውሷቸው።

እርሶዎ በቅርቡ ለፓርላም ገለፃ በእደረጉበት ወቅት በትግራይ ውስጥ የሚኖሩት ተራዎቹ የትግራይ ህዝብ በገዢው መደብ ስልጣን መያዝ ምንም እንዳልተጠቁሙ አስረድተው ነበር። ቃሎ እውነት ነው። በትግራይ ውስጥ የሚኖረው ስፊው ህዝብ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ላልመሆኑ ቀላሉ ማስረጃ የሚጠጣው ውሃ እንኳን የሌለው መሆኑ ነው። እርስዎ ትግራይ በሄዱ ጊዜ መድረኩ ላይ ከርስዎ ጋራ የትግራይ አስተዳዳሪዎች እያሉ ህዝቡ እነሱን ዘሎ እና እነሱ እንደማይረዱት ተረድቶ የሚጠጣ ንፁህ ውሃ እርስዎ እንዲያንቆረቁሩለት መማፀኑአስደንቆኛል። በዛን ወቅት እኔ የተግራይ አስተዳዳሪ ሆኜ መድረኩ ላይ ብኖር ኖሮ እኔ እያለሁ ህዝቤ እርስዎን ቢማጠን በራሴ ስንፍና እና ግዴለሽነት በጣም ባፈርኩ ነበር። አሁንም ድሀው የተማፀኖትን ውሃ ለተጠማው ህዝብ በቶሎ ያድርሱለት። ከ እዚህ በፊት ለህዝቡ ውሃ ጥም ማርኪያ ከውጪ መንግሥታት በብድር የገባ 700 ሚሊዎን ብር ነበር ተብሏል። ይህ ገንዘብ የት እንደ ደረሰ አጣርተው ገንዘቡ ካልተሰረቀ ለታቀደለት ዐላማ እንዲውል ይትጉበት። ሰፊውን የትግራይ ህዝብ እንደተጠቃሚ ቆጥረው ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ያለ እግባብ እንዳየጠምዷቸውና እንዳይነሳሱባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ችላ የማይባል ጉዳይ ነው። እርስዎ እንደ አሉት አይጥ በበላ ዳዋ መምታት የለበትም።

ከትግራይ ጋራ በተያያዘ እዛም በግፍ የታስሩ ጉዳታቸው ያልታወቀላችው አያሌ የትግራይ ሰዎችና ሎሎችም ከትግራይ ውጨ የተጋዙ ኢትዮጵያውያን ባዶ 6 በተባለ ዘብጥያ ውስጥ ከሰውነት ወጥተው አንደታጎሩ ይነገራል። እነዚህን ያልታደሉ ፍጡራን እባክዎን ይድረሱላቸው። እንዲሁም በትግራይ ውስጥ የሚገኙትን ምስኪን ህዝቦች እና ከትግራይ ውጪ ያሉት በቅን ልቦና ሊደመሩ የሚፈልጉት ተጋሩዎች ደህንነት እንዲጠበቅላችውና የህይወት ዋስትናቸው እንዲረጋገጥላቸው የፀጥታውን ሁኔታ ይከታተሉላቸው።

ከኤርትራ ጋራ ሰላምን፣ እርቅን እና ፍቅረ-ዝናብን ለማውረድ የሚያደርጉት ጥረት ደስ ይላል። እርቁ ከተሳካ እና አስተማማኝ ከሆነ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበሮች ላይ የአሉት፣ ለሃያ ዓመታት ጉድጓድ ውስጥ የመሸጉት ወታደሮች ከጉድጓዳቸው ውጥተው ለጊዜው ጦር ካምፕ ውስጥ ቢቆዩ ይበጃል። ከመሃል ሀገር ወደ ትግራይ የተጋዙትም የጦር መሳሪያዎችና አይሮፕላኖች ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለስ ይገባቸዋል። በተለይ አይሮፕላኖቹ ወደ ቢሾፍቱ እና ድሬደዋ ጣቢያቸው በቶሎ መመለስ አለባቸው። 200 000 ነው የሚባለው የጦር ሰራዊት ግን የእርስዎን የጠቅላይ ጦር አዛዥነትንና ለእርስዎ በቅጥታ ተጠሪነትን ተቀብሎ ላልተወሰን ጊዜ እዛው ትግራይ ውስጥ ቢቆይ ይሻላል። እግዚአብሄር አያደርገውና በሆነ ምክንያት ወደ ትግራይ ጦር መላክ ካስፈለገ ከመሃል ሃገር ከመላክ ይልቅ እዛው የአሉትን መጠቅም ስለሚቀል።

በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከውጪ ሀገራት በልግስና እና በብድር ከተላኩት ዶላሮችና ፓወንዶች ውስጥ አብላጫው ተሰርቆ ወደ ውጪ ሸሽቶ የሌባን ገንዘብ በሚያጠራቅሙ ባንኮች ውስጥ እንደ ተሸሸገ ለጋሶቹና አበዳሪዎቹ አጋልጠዋል። ይህን የተሰረቀ የኢትዮጵያን ህዝብ ገንዘብ ለማስመልስ የሚያደርጉት ጥረት ያስመሰግኖታል። ይበርቱበት። ከኤትዮጵያ ባንኮች ያለ መያዣ ወይም ያለ ቀብድ ገንዘብ ወስደው ህንፃዎች ገንብተው እዳውን ሳይከፍሉ ቤቱን አያከራዩ እና ትርፉን ውደ ዶላር መንዝረው አትርፍው የባንክ እዳቸውን ያልከፈሉትም ግለሰቦች ሂሳብ መመርመር አለበት። ተመርምሮም መወራረድ አለበት።

ከጥቂት ቀናት ብፊት እርስዎ እንደ አበሰሩን፣ ኢትዮጵያ ቤንዚን እና የተፈጥሮ ጋዝ አግኝታለች። አሰየው ነው።ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ኦጋዴን ውስጥ ቤንዚን እንደተገኘ ሲሰማ ከርሟል። ዳሩ ግን ቤንዚኑ የህልም እንጀራ ሆኖ ቀርቶ ነበር። ይህን መልካም ዜና ለኢትዮጵያ ህዝብ አብሳሪው እርስዎ በመሆንዎ በእውነት እድለኛ ነዎት። ምንም ይህ ዜና መልካም ቢሆንም፣ በእዚህ ጠንቅ በ ነዳጅ ጉድጓዶቹ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የሶማሊያ ሱማሌዎች ጋራ ጠብ እና ጦርነት እንዳይቀሰቀሱ ታላቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። አብዲ ኢሌም የሚታመን ሰው ስለ አልሆነ እና በራሱም ህዝብ ስለተጠላ ከእካባቢው ገለል ቢደረግ ይበጃል። ዳሩ ግን እርስዎ አርቀው ስላሰቡ ከሶማሊያ መሪዎችም ጋራ አብሮ የመሥራት ውይይት አካሂደዋል። ይህም ውይይቶ ፍሬ እንደሚያፈራ ተስፋ አለኝ።

ድሬደዋን አስመልክቶ፣ በንጉሡ አግዛዝ ጊዜ ዴሬደዋ በጣም የሰለጠነች እና የበለፅገች፣ ጎሳዎች በፍቅር ቀልጠው የሚዋሃዱባት የኅብረ-ብሄሮች ከተማ ነበረች። በደርግ ጊዜ ተጎዳች። በኢህአዴግ ጊዜ ፈፅማ ወደቀች። የእዚህ ዋና ምክንያቱ ባለቤት ማጣቷ ነው። ራስ-ገዝ በሚል ሽፋን 40% ኦሮሞ 40% ሱማሌ 20% ሌሎች በሚል ፈሊጥ ወደ 30% የሚጠጋው አማራ ከአስተዳደር ስልጣን ተገልሎ እንደ ባዕድ አየታየ ችሎታውን ለከተማዋ እንዳያበረክት በሚያሳፍር ሁኔታ ታግዶ የበዪ ተመልካች ተደርጓል። ኦሮሞን እና ሱማሌን እንወክላለን የሚሉት ግለሶቦችም እየተፈራረቁ ከተማዋን ይዘርፉዋታል። ከብር ጠቅላይ ሚንስትር፣ በድሬደዋ የተንሰራፉትን ሙሰኝነት እና የዘር መድልዎ ያስቆሙ ዘንድ እማፀንዎታለሁ። የድሬደዋ ተወላጅ አማሮችም በችሎታቸው በከተማቸው አስተዳደር ውስጥ እንዲሳተፉ ይርዷቸው።

በውጪ ሀገራት የሚገኙትን ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥራቶ ተግቢ ነው። እነዛ ሁሉ ዲፕላማቶች ተጠርተው ምርቱ ከግርዱ መለየት አለበት። አብዛኛዎቹ ዲፕሎማቶች የተላኩበትን እና ወፍራም ደሞዝ የሚከፈሉበትን ሥራ ትተው ብንግድ ሥራ መሠማራታቸውን ሁሉም የሚያውቀው ነው። አብዛኞቹ ኤምባሲዎች ችሎታ በሌላቸውና ከ አንድ ጎሳ በተውጣጡ ዘሮች በመታጨቃቸው መላዋን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አይመስልም። በተለይ በእረብ ሀገራት የአሉት ለዜጎቻቸው ፍፁም ደንታ የሌላቸው እና ርኅራኄ የጎደላችው ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን እህቶቻችንን እና ወንዶሞቻችንን ፔትሮ ዶላር ያቀወሳቸውና ትእቢት ያሳበጣቸው መሃይማን አረቦች ሰብአዊ መብታቸውን ገፍፈው ሲያሰቃዩአቸው እና ሲገድሏቸውም ዘወር ብለው አያዩአየ ቸውም። የአርስዎ አምባሳደሮች ዘረኛ ያልሆኑ፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በእኩልነት የሚያስተናግዱ፣ ብቁ እና ሰብአዊ ርህራሄ ያላቸው እንድሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም በእግዚአብሄር ስለማመንዎ ደስተኛ አንደሆንኩ ልገልፅልዎት እወዳለሁ። ከአፄ ኃይለሥላሤ በኋላ ባለፉት 45 ዓመታት ሥልጣን የያዙት ሁሉ መሪዎች እግዚአብሄርን ክደው ወይም የለምና ችግሩን ሁሉ በራሳችን ጉልበት እንፈታዋለን ሲሉ ተደምጠዋል። አርስዎ ግን ከተመረጡበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሄርን ሲጠሩ ተሰምተዋል። ይህ ትልቅ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሄር ናትና። ከእዚህ በተያያዘ አንድ የሚያስደንቅ ነገር ላውጋዎ። የዛሬ 4000 ዓመት ከኖረው ኢትዮጵያን በስሙ ከሚያስጠራው አባታችን ከኢትዮጵ ጀምሮ እስክ ዐፄ እስያኤል ድረስ (የዛሬ 3000 ዓመት ድረስ የኖረው እስያን በስሙ ያስጠራው) የነገሡት ወንዶች ሁሉ ሊቀካህናት ነበሩ። በሌላ እነጋገር ሁለት ስልጣናት ነበራቸው፡– ፖለቲካዊ እና መለኮታዊ። በፖለቲካው የንጉሦች ንጉሥ ነበሩ። በ መለኮታዊው ደግሞ የካህናት ካህን።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                               በእዚህ ምክንያት የበላይ ተቆጣጣሪያቸው የዐለሙ ሁሉ ፈጣሪ ራሱ አግዚአብሄር ነበረ። ከእሱም ጋራ የቀጥታ ግንኙነት ነበራቸው። ስለእዚህ እግዚአብሄርን እያከበሩና እየፈሩ ስልጣናቸውን አለ አግባብ አንዳይጠቀሙ ይጠነቀቁ ነበር። አግዚአብሄርም በንጉሦቹ እምነት እየተደሰተ ኢትዮጵያን ይባርካት ነበር። በሰለሞናዊው እና በዛግዌው ስርወመንግሥታት ውስጥ የነገሡትም ነገሥታት እንዲሁ በእግዚእብሄር እምነታቸው የፀኑ ነበሩ፤ ምንም እንኳን ካህናት ባይሆኑም። እንግዲህ እርስዎም ምንም ካህን ባይሆኑም በእግዚአብሄር ማመኖ እላይ በተጠቀሰው ምክንያት ለኢትዮጵያ ትልቅ የምስራች ነው። በሚሠሩአቸው ሥራዎች ውስጥ ሁሉ የሚያምኑበት። በአደባባይ ስሙንም የጠሩት እና የአከበሩት እግዚአብሄር ይግባበት። ገብቶበታልም። እሱም መላእክቱን በዙሪያዎ ልኮ ይጠብቅዎት። ሀገራችን ኢትዮጵያም በሰላም፣ በፍቅር እና በብልፅግና ለዘላለም ትኑር።

ውድ አንባብንያ ይህን መልእክት እባባችሁ አካፍሉት። ለሁሉም ይድረሰው።

Share.

About Author

Leave A Reply