ልጇ የሚጠበቀውን የፈተና ውጤት ስላላመጣ ልጇን የካደችው እናት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በቻይናዋ ሉኦያንግ መንደር ቻይናዊቷ ወላጅ ልጇ የሚገባውን የፈተና ውጤት ማምጣት አልቻለም ብላ መንገድ ላይ ትታው ሄዳለች። የ12 አመቱ ታዳጊ በአገር አቀፍ ፈተና 95 ከመቶ ያመጣል ብላ የጠበቀችው እናት 81 በመቶ በማምጣቱ መንገድ ላይ ትታው መሄዷ ብዙ እያስባለ ይገኛል።

በግርግሩ የሉዎያንግ መንገድ ላይ እናቴ ትመለሳለች ብሎ ሲጠብቅ ፖሊስ ያገኘው የ12 አመት ልጅ ስለሁኔታው አካባቢው የነበሩ ሰዎችን ሲጠይቅ እናቱ ከመኪና ውስጥ እያመነጫጨቀች ካስወጣችው በኋላ መታችው እሱን ውጭ ትታም መኪናዋን አስነስታ ሄደች ብለዋል።

በሲሲቲቬ ካሜራ የነበረውን እንቅስቃሴ ካጣራ በኋላ ወደ ቤተሰቡ የደወለው ፖሊስ ልጁን ሊቀበል የመጣው አጎቱ ብቻ መሆኑን ሲያውቅ የውላጆቹን ሁኔታ ለማየት እናቱን አፈላልጎ በማግኘት ስልክ ይደውላል። ልጇን ጥላ የሄደችው እናትም ልጁን ጭራሽ እንደማትፈልገውና የፈለጉትን ቢያደርጉት ቅር እንደማይላት ለፖሊስ አስረግጣ ትናገራለች። ምናልባትም ሊያስቀጣት ሊያሳስራት ቢችል እንኳን ይህንን ሰነፍ ልጇን መልሳ መውሰድ እንደማትፈልግ ትገልጻለች።

መልሷ ያስገረመው ፖሊስም ወደ ሌሎች ዘመዶቹ ከደዋወለ በኋላ አጎቱ ሊወስደው ፈቃደኛ ሆኖ ወስዶታል።በቻይና አገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ጥሩ ማምጣት እና አለማምጣት የታዳጊዎችን የወደፊት እንቅስቃሴ ከሚወስኑ ነገሮች መሀል ዋነኛው ነው። ብዙ ወላጆችም ልጆቻቸው በታዳጊነታቸው ጥሩ የሚባል ውጤት እንዲያመጡ እጅጉን ይታትራሉ።

ሆኖም የዚህች ወላጅ ጉዳይ ግን በማህበራዊ የትስስር ገጾች ብዙ እያስተቻት ይገኛል። ምንም ልጁ አጥፍቶ ቢሆን እንኳን በትዕግስት መንከባከብና የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ መርዳት እንጂ በዚህ መልኩ ሜዳ መጣል ተገቢ እንዳልሆነ ብዙ እየተባለ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply