ልጓም አልቦው የኬኛ ፖለቲካ ወዴት ያደርሰናል? ክፍል ሁለት (በመስከረም አበራ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝቦች ስቃይ፣የለገጣፎ ተፈናቃዮች፣በሱሉልታ መፈናቀል የተደገሰላቸው በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮች፣በአርሲ እና ባሌ በስጋት የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ስጋት እና እንግልት አንዱ የኬኛ ፖለቲካ መዘዝ ነው፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ብዙ ያልተነገረለት ግፍ የተከሰተው በቡርጅ እና በኮይራ ህዝቦች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የደቡብ ህዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚጎራበቱ በአገረማርያ(ቡሌ ሆራ) እና አጎራባች የኦሮሚያ መሬቶችም ይኖራሉ፡፡በተለይ በጤፍ አምራችነታቸው በአጠቃላይ በጠንካራ አራሽነታቸው ይታወቃሉ፡፡

በዚህ ምክንያት “መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ” እየተባሉ መንገላታት ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል፡፡ ከአንድ አመት በላይ መንገድ ተዘግቶባቸው ለቅንጦት ቀርቶ ቢታመሙ፣ወላድ ምጥ ቢይዛት ሆስፒታል የሚደርሱበት መንገድ የላቸውም፡፡በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ቡርጅ እና ኮይራዎች “ባለመሬት ነኝ” ባዮቹ ካድሬዎች የፈለጉትን ቢያደርጓቸው አቤት የሚሉበት አካል የለም፡፡አንድ ከአካባቢው የመጣ ኦሮሞ እንደሆነ ግን በድርጊቱ በጣም እንደሚያዝን የነገረኝ ልጅ ይህን ግፍ አጫውቶኛል፡፡አራት ጌዲኦዎች ታርደው ተጥለው በአይኑ እንዳየ እየዘገነነው ነግሮኛል፡፡የሃገር ባለቤት ነን ያሉ የኦሮሞ ጎረምሶች በቀን በብርሃን የቡርጅዎች ቤት ጣራ ላይ ወጥተው ቆርቆሮ ነቅለው ሲወስዱ ባለቤቶቹ ቡርጅዎች ቆመው ከማየት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው፤ይህንንም ሲያደርጉ እንዳየ እያዘነ ነግሮኛል፡፡”ይሄ ቡርጅ፣ኮይራ፣ጌዲኦ ላይ ለምን ተደረገ?”ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ በቡርጅ ፣ኮይራ እና ጌዲኦ ተወስኖ ይቀራል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው፡፡ዝም ከተባለ ነገ አዲስ አበባ ይመጣል፤እየመጣም ነው፡፡

ይህ የህዝቦች መፈናቀል፣የባለ ጊዜ ነኝ ባዮች ስርዓት አልበኝነት በራሱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ ለሌሎች ክልሎች ጎረምሶችም አርአያነትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ በተጨባጭ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ፣በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የታየ ነው፡፡ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ስርዓት አልበኛ ምንም ሲደረግ ያላየ የሌላ ክልል ጎረምሳም ዘሩን የበላይ ለማድረግ “ሌሎች” በሚላቸው ላይ ተመሳሳዩን እያደረገ ሲሄድ ሃገራችንን መልሰን ላናገኛት እንችላለን፡፡ ነገሩን ከሃገር መፍረስ በመለስ እንየው ከተባለም ሃገሪቱን ለከፋ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋትል፡፡ሲንፏቅ የኖረው ኢኮኖሚያችን ጨርሶ እንዲሞት ያደርጋል፡፡የኢኮኖሚ ችግር ደግሞ ዘረኝነት የለኮሰውን የፖለቲካ እሳት ይብስ ያነደዋል፤ስርዓት አልበኝነቱን ያጎነዋል፡፡ይህ ሁሉ ተደማምሮ በሃገር ተስፋ መቁረጡን ያባብሳል፡፡ስደት መፍትሄ ይሆናል፤ የባህር ራት መሆኑ ከነበረው ብሶ ይቀጥላል፡፡ኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነም እንደ ውሻ በየቦታው ወድቆ ከመቅረት፣በየባዕድ ሃገር በረሃ ከማለቅ ውርደት ጋር ተጋምዶ ይቀጥላል፡፡

በኬኛ ፖለቲካ ምክንያት በህዝብ እና በመንግስት መሃል ወርዶ የነበረው እርቅ ይከስማል፤ጠብ እና ክርክር ከአንድ አመት እረፍት በኋላ ወደቦታው ይመለሳል፤እየተመለሰም ነው፡፡በዚህ ሳቢያ ከዲያስፖራው ይመጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ይመናመናል፤እንደ ቀድሞው በዘመቻ የሚታገድበት ጊዜም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ሃገር ውስጥ ያለው ዜጋ ስራውን እንዳያከናውን የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እግር ብረት ሆኖ ይቀይደዋል፡፡የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ያገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጥ ወደ ማጥ ይከተዋል፡፡ይህ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ተፅዕኖ የሚያመጣው ተራዛሚ ውጤት ይሆናል፡፡ ይህ ተራዛሚ ውጤት ሃገሪቱን መልሶ ወደ አለመተማመን ፖለቲካ፣ ወደተስፋ መቁረጥ እና በኋላቀር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ወደመመራት ልማዷ ይከታታል፡፡ተከባብሮ ተማምኖ መኖር ይጠፋል፡፡መብለጥን እንጅ እኩልነትን እንደ መፍትሄ የማያየው የዘር ፖለቲካ መጨረሻው ሃገር ማፍረስ ነው፡፡ በሰለጠነ ዘመን፣በነቃ ህዝብ ላይ የበላይ ሆኖ መኖርን ማሰብ፣በልብ ሌላ ይዞ በአፍ ሌላ እያወሩ ሰውን ለማመሞኘት የሚደረግ ሩጫ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን እንደይጎዝላቪያ “ነበረች” ወደ ምትባልበት ተረት ሊቀይራት ይችላል፡፡

የኬኛ ፖለቲከኞች ሁሉን ለእኔ በማለታቸው የገፉት ይህን ሁሉ ስለማያውቁ አይደለም፡፡ይልቅስ የያዛቸው የዘረኝነት አባዜ ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሚያ ልታብብ እንደምትችል ስለሚነግራቸው ነው፡፡ይህ እጅግ ስህተት ቢሆንም ተገፍቶበታል፡፡ልጓም ያልገባለት ምኞታቸው የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የአንድ ጎጥ ንብረት ለማድረግ እስከመሞከር ሄዷል፡፡ይህ ሳይታፈርበት በመግለጫ እስከመነገር ደርሷል፡፡ይህን ህገ-ወጥ እና ዘረኛ መግለጫ ፈርመው ያፀደቁት ባለ ብዙ መልኩ ጠ/ሚ አብይ ሳምንት ቆይተው ደግሞ “አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊ ሁሉነች” ማለት ጀምረዋል፡፡ይህ ኢህአዴጋዊ ተንኮል ያለበት ንግግር ነው፡፡አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው እውቅና እየሰጡ ያሉት ከኬኛ ፖለቲካቸው ጋር የማይጋጨውን የአዲስ አበባን የፌደራል ከተማ የመሆን ነጠላ ማንነት ብቻ ነው፡፡ሁለተኛውን እና እያጨቃጨቀ ያለውን፣ለኬኛ ፖለቲካቸውም ጋሬጣ የሚሆነውን አዲስ አበባ የኗሪዎቿ የመሆኗን ሃቅ ሊናገሩት አልደፈሩም፡፡

አዲስ አበባን በትክክል እና በተሟላ ሁኔታ የሚገልፃት ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ያላት ከተማ እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና የመሆኗ መንታ ማንነት ነው፡፡ራሷን በራሷ የምታስተዳድር የኗሪዎቿ ከተማ መሆኗን መግለፅ ከተማዋን በማስተዳደሩ በኩል ለኦሮሞ ከፈጣሪ የተሰጠችነች ከሚለው የኬኛ ፖለቲካ ጋር ስለሚጣረስ አብይ በዘዴ አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ይህ ማደናገሪያ ነው፡፡እውነተኛው በመግለጫ ተነግሮናል፡፡መግለጫውን ተረድቶ ሃገርን ከጥፋት ለማዳን የሚደረገውን ማድረግ ወይም የማደናገሪያውን ማደንዘዣ ተወግቶ ሃገር ሲጠፋ ማየት የሰሚው ምርጫ ነው፡፡

የኬኛ ፖለቲካ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን አላማ እንዲያሳካ እና ከተማዋን እንዲቆጣጠር መፍቀድ ለማንም ኢትዮጵያዊ የሚሆንለት ነገር አይደለም፡፡በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውም አብይ እንዳት የሱሉልታ እና የሆለታ ኦሮሞ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርብ ርቀት ደብረብርሃን እና ቡታጅራም አሉ፡፡አዲስ አበባን የመሰለች የኢትዮጵያዊነት ምልክት ለመታደግ ሰመራም፣ጅጅጋም፣ባህርዳርም፣ድሬዳዋም ፣አርባምንጭም፣ሆሳዕናም፣ወላይታ ሶዶም፣ዱረሜም፣አሶሳም፣ደብረማርቆስም ሩቅ አይደሉም፡፡በሰለጠነ ዘመን የሃገር ሩቅ የለም! በቅርብ ያለሁ እኔነኝና አርፋችሁ ተቀመጡ የሚለው ቂልነት የማያጣው ሃሳብ ይልቅስ ከተማዋን የእልቂት አምባ ያደርጋታል፡፡

አዲስ አበባ ስትታመስ የምናጣው ብዙ ነው፡፡አዲስ አበባችን ከኒውዮርክ እና ጄኔብ ቀጥላ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መዲና በመሆን ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ ከተማ ነች፡፡ይህ ክብራችን ነበር! ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፤ ይህ የሆነው እኛ በዘር መባላቱ አዳርሶን በሰራነው ስራ አይደለም- በነጋ በጠባ የምንረግማቸው አባቶቻችን ሞተው ባመጡልን ክብር የተገኘ እንጅ!የኬኛ ፖለቲካ ዝቅታ እንዲህ ላለው ለአዲስ አበባ ዓለማቀፋዊ ግዝፈት የማይመጥን የኦሮሙማ ጠባብ ጥብቆ ሊያለብስ የሚንገታገት ነው፡፡ግዙፏ፣አለማቀፏ አዲስ አበባ በዚህ ጠባብ ጥብቆ ለመግባት ትልቅነቷ አይፈቅድላትም፡፡

በጠባቡ ጥብቆው እንድትገባ የሚደረገው አሽቆልቋይ ትግል አዲስ አበባን እጅግ ያዉካታል፤መረጋቷን ይነጥቃታል፡፡ባልተረጋጋ ከተማ ለመኖር የሚፈቅድ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ደግሞ አይኖርም፡፡ሁሉም አንዳንድ እያለ በኬኛ ፖለቲካ የምትታመሰውን አዲስ አበበን እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ይሄኔ የአፍሪካ መዲናነት ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ይህን ክብር ለማግኘት ሌት ተቀን ሲሰሩ የኖሩ የአፍሪካ ሃገራት መባላታችንን ጠቅሰው የአፍሪካ መዲናነት ወደሚመጥነው ከተማ እንዲያቀና ይከራከራሉ፡፡ያኔ ምን እንደምናወራ አላውቅም!የሜንጫ እና የዱላ ትርኢት በሚታይበት፣በገዛ ጠ/ሚኒስትር ጦርነት በሚታወጅበት ከተማ መኖር አለባችሁ ብሎ ማስገደድ ይቻላል? ላስገድድ ቢባልስ ማን ይሰማል? ስለዚህ የኬኛ ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችንን ሊነጥቀን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪካዊ፣ዲፕሎማሲያዊ፣ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ውርደት ያመጣል፡፡ከዚህ ውርደት ለመዳን ኦህዴድ ሃይ መባል አለበት፡፡እንዴት? ለሚለው ሌላ ቀጠሮ ልያዝ::

Share.

About Author

Leave A Reply