መሀመድ አወል ሃምዛ ያልተዘመረለት የሃበሻው ምድር ባለ አሻራ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ወሎ የኢትዮጵያ እስልምና የስበት ማዕከል ናት። የእነ አባጌትዬ፣ የእነ ፈቀህ ዙበይር፣ የእነ ሀጂ አቡየ ፤የነ ሸህ ጫሌ፤የነ ሸህ ደባትይ፤የዳንይና የአንይ ፤ የነ ሸህ ዳውድ ማርየ፤ የነ ጀማ ንጉስ ኧረ ሥንቱን ልዘርዝረው??? የስንቱ መሻኢክና ወልይ መፍለቂያ ቅዱስ ምድር ናት ወሎ። የእስልምናው ብቻ ሳይሆን በክርስትናውም እነ ሀይቅ እስጢፋኖስን፣ ግሸን ማርያምን፣ ቅዱስ ላሊበላን በውስጧ ያቀፈች የክርስትናው አውታር እና መሰረትም ነች።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ 3000 ዓመት የሚሞላት የተድባበ ማርያም መቅደስ እና ቤተክርስትያን የሚገኘውም በዚሁ በወሎ ውስጥ ነው። መንዙማ የወሎ ሙስሊሞች ለኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ወንድሞቻቸው ያበረከቱት እጅግ አስደናቂውና ተአምረኛው ትውፊትና ስጦታ ነው። ታላቁ ኢትዮጲያዊው ሙፍቲ ሸህ ኡመር ሲናገሩ መንዙማ በመላው አለም ሞልቷል የወሎው ግን አጃኢበኛ ነው ። መደዱ ፤አሰካኩ፤አገጣጠሙ፤ለዛና ወዘናው፤ዝማሬዋና ፍሰቱ የጠመመውን ቀልብ ያቃናዋል ፤ የደረቀውን ልብ በቶሎ ያረሰርሰዋል ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ።

መንዙማማ ሞልቷል ላገር የሚበጅ
አጃኢብ የሚያሰኝ የወሎው ነው እንጅ

የሚባልለት ወሎ በኢስላማዊ ኪነጥበብ መፍለቂያነቱ ወርጅናሌ ባለውለታ ሆኖ ይነገርለታል ። በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው መንዙመኛ የ19ኛው ክፍለ ዘመኑ ዓሊም እና በዓጤ ዮሀንስ 4ኛ እንግልት እና መሰደድ የደረሰባቸው የራያው መሻኢክ ጀማሉዲን አንይ ናቸው። ጀማሉዲን አንይ ሌላ ስማቸው ሞሀመድ ሮብሶ እንደሚባል ከሰሞኑ በከድር ታጁ ጥሁፍ አንብቤያለሁ። ጀማሉዲን አረብኛና ኦሮምኛ ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ እና መንዙማወቻቸውንም በአረብኛ ቋንቋ እንደሚያዘጋጁ ታውቋል። ጀማሉዲን አንይ ትግርኛ ቋንቋን ቢችሉትም አይናገሩም ነበር ለዚህ ምክንያታቸው በምን ቃላት መግለጥ እንዳለብኝ ስለከበደኝ ልተወው። ብቻ ደረሳወቻቸውን ትግርኛ እንዳይናገሩ ይከለክሉ እንደነበር ሰምተናል።
.
የቃሉ ምድር ያስገኘችው ሶብረኛው ሰው መሀመድ አወል ሃምዛ መንዙማን ለዚህኛው ትውልድ በለዛኛውና በሸገነው አማርኛ ለኢትዮጵያውያን ነፍስና ልቡና ያደረሰ ባለ ታላቅ አሻራ ነው። የሚያስገመግመው መግነጢሳዊ ድምጡ ቀልብያን ስብስብና ሽክፍ አድርጎ ወስዶ ሌላ ዓለም ላይ የሚከተውና የሚያሰግረው መሀመድ አወል ሃምዛ የመጀመሪያውን አማርኛ መንዙማ በካሴት ያሳተመው በ1987 አም ነው። መሀመድ አወል ሃምዛ የድምጡን ውበትና ለዛ እንዴት መግለጥ እንዳለብኝ አላውቅም። በተለይ ስርቅርቅ እንጉርጉሮወችን የሰማሁ ጊዜ የሚሰማኝ ስሜት የተለየ ነው። አስገምጋሚ ድምጡን እንዳሻው በጀማው መሃከል በለቀቀው ጊዜ ጆሮውን የማይሰጥ ሰው ካለ ተፈጥሮ የበደለችው መሆን አለበት። በመንዙመኞች መሃል የእኔ ነፍስ መስማት የምትሻው የእሱን እንጉርጉሮ ብቻ ነው፤ በመሀመድ አወል እንጉርጉሮ እጥዋቱና እንሰሳቱ ሁሉ የሚመሰጡ ይመስለኛል። በተለይ ክርስትያን ወንድሞቼና እህቶቼ የመሀመድ አወልን እንጉርጉሮ እስከዛሬ በቸልተኝነት አልያም በሌላ ምክንያት ካልሰማችሁት እጅጉን ቀርቶባችኋ።
.
መሀመድ አወል በሚያስገመግመው አስደናቂ ድምጡ የሚያንቆረቁረው ዜማው ፍሰቱና አብረው የተዋደዱት ግጥሞች እንዴት ባለ አስደናቂ መንገድ እንደተቀናጁ የሚያስገርም ነው። የሀዲስን አልያም የዋናውን መጥሀፍ ታሪኮች ፊደል ላልቆጠሩት ለቀደምቶቻችን ታሪኩን ያውቁት ዘንድ ለሌላውም በቀላሉ ያደምጠው ዘንድ በእንዴት ዓይነት ምትሀታዊ መንገድ አበጃጅቶ በድምጡና በዜማው አዋዶ እንደሚያቀርብ ዘይገርም ያስብላል። መሀመድ አወል የአፈ ታሪክም አዋቂ እንደሆነ ሰምቻለሁ፤ አንድ ወዳጄ ከእሱ ጋር ሊያገናኘኝ እንደሚያመቻችልኝ ነግሮኝ እስከዛሬ ባይሳካልኝም በዚያ ድምጡ ከአጠገቡ ሆኜ ታሪክ እሰማ ይሆናል። መሀመድ አወል ቅርስ ነው፤ እውነት ነው ህይወት ያለው ቅርስ ነው።የአምባሰል ቅኝትና ዝማሬ ለማሪቱ ለገሰ ተተምኖና ተሰፍሮ እንደተሰጣት ሁሉ የኢትዮጲያ ሙስሊሞች መንዙማ ደግሞ ለወሎየው መሃመድ አወል ሃምዛ ተሰፍሮና ተመትሮ የተሰጠ ነው ብየ ብመሰክር ማን ከልካይ አለኝ??? የመሃመድ ሃምዛ እንጉርጉሮወቹ ደግሞ ዘመን የማይሽራቸው ከሃበሻ እስልምና ጀርባ የቆመው ጉልበት ነው ። ለሃገራችንም ተሻጋሪ ህያው ቅርሶች ናቸው።

የራያው ደረሳ Yasin Mohammed /ያሲን ምትክ አልባው በማለት መሀመድ አወልን እንደሚከተለው ይገልጠዋል። << መሃመድ አወል አይፈራም፣ አያጎበድድም፣ አያስመስልም!! አባትነቱንና ትልቅነቱን በጭንቀት የልዩነት ሰኣት እንዲህ ሲል እቅጩን ተናግሯል፥

“ስማ ሽብርተኛ ተው ሽብር አታውራ
ወጋቸው አማን ነው ምንም አያስፈራ”

በማለት አፋኙን የመለስ ዜናዊ አጎንባሽ ሁላ በጊዜው መክሯል!! የእሱን ስራዎች ስንጾም መተናነሻ፣ ስንፈራ ተስፋን ጫሪ፣ ስንሻና ስንመኝ ጀነትን መሪ ናቸው!! መሃመድ አወል የወሎ መንዙማ ዳግም ሰሪ፣ ልህቀትና ጥልቀት ወሰንም ነው!!! ግን ግን የራሱን ጣይ፣ የራሱን ጥበብ አጉዳፊ አበሻዊ ሙስሊም ባለበት አገር መሃመድ አወል ሃምዛ ምንም ነው።” በማለት ይገልጠዋል።

ሙስሊም ላልሆኑት ወዳጆቼ ግን የመሀመድ አወልን እንጉርጉሮ ካልሰማችሁ ብዙ ቀርቶባችኋል እላለሁ። ለመሀመድ አወል ደስታኛና ረጅም እድሜ እመኛለሁ።

ብሩክ አበጋዝና መንግስቱ ዘገየ

Share.

About Author

Leave A Reply