መርበብት የተሰኘው የዶክተር አለማየሁ ዋሴ መጽሓፍ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ትንቢት ወይስ ልብ ወለድ ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ አሊ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት መርበብት በሚለው የዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ልብወለድ መጽሐፍ ኢትዮጵያን ለመምራት ሰለሚመጣው አዲስ መሪ በምዕራፍ 20 እንዲህ ተጽፎ ነበር፡፡ . . .

. . . ጨለማው ሲነጋ፣ የደፈረሰው ሲጠራ፣ አቧራው ሲሰክን ከመካከላችን ይነሳሉ፡፡ በግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ ሥልጣን አይሹም ሕዝቡ ግን ይሾማቸዋል፡፡ ታውቃላችሁ ይባላሉ እንጂ እናውቅላችኋለን አይሉም፡፡ ክብር አይፈልጉም ሕዝቡ ግን ያከብራቸዋል፡፡ . . ~

. . . ሀይማኖታቸው ፍቅር ነው፡፡ ሐረጋቸው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ወገናቸው ሰው ነው፡፡ ሀገር እንጅ መንደር የላቸውም፡፡ ኃላፊነት እንጅ ስልጣን የላቸውም፡፡ የሚቃወማቸው ሞረዳቸው ነው፤ የሚደግፋቸው ምርኩዛቸው ነው፡፡ . . . ከምዕራብ ከምስራቅ፣ ከሰሜንና ከደቡብ ቢሰባሰቡም፣ ሀሳባቸው የሰመረ ዓላማቸው የተዋሀደ ነው፡፡ . . .

. . . በይሁንታ እንጅ በግርግርና በደም አላባ ሥልጣንን አይፈልጉም፡፡ ሥልጣን አይቀሙም፤ ይረከባሉ እንጅ፡፡ . . . በእነሱ ዘንድ በሰው ልጆች ደም የሚመጣ ሥርየት የለም፡፡ በማንም ላይ አይፈርዱም፤ ያስፈርዳሉ እንጅ፡፡ ከመንቀል ይልቅ፣ መትከልን ይመርጣሉ፡፡ . . .

. . . በወደቀው ላይ ምሳር አያበዙም፡፡ በመጭው ዘመንና ትውልድ ሚዛን ቀልለው እንዳይገኙ ይተጋሉ እንጅ ወደ ኋላ ሂደው ባለፈው ዘመን በተጻፈ ታሪክ ራሳቸውን ተክተው አይመጻደቁም፡፡ በየትኛውም ዘመን የተሰራን በጎ ሥራ ለማስታወስ አያግደረደሩም፡፡ . . . በበጎ የታሰበን ያስጀምራሉ፣ የተጀመረን ያስጨርሳሉ፣ የፈረሰን ይጠግናሉ፣ የተጣመመን ያቃናሉ፣ የሄደን ያስመልሳሉ፣ የተለያየን ያገናኛሉ፡፡ . . .

. . . ለአገራዊ ችግር አገረኛ ቀመር፣ አገረኛ ስልት፣ አገራዊ መፍትሔ አላቸው፡፡ የአየር ጸባይ፣ ከገጽ እስከ ከርሰ ምድሯ ያለውን ጸጋ፣ የልጆቿን አቅም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ዕቅዳቸው ጥንቁቅ፣ አፈጻጸማቸው ፈጣን ነው፡፡ . . .

. . . በጥልቅ እሳቤያቸው የስንፍናና የጥላቻ አረንቋን ያደርቃሉ፡፡ በእናት ምድር ውስጥ የበይ ተመልካች እንዳይኖር ፍትሕ ይበየናል፡፡ ፊቱ ለወዛ አያዳሉም፡፡ በወርቃማው ዘመን ሳይደርሱ ለሞቱት ይለቀስ እንደሆነ እንጅ በፍትሕ እጦት የሚፈስ የሕዝብ እንባ የለም፡፡ . . .

. . . ልዑካኖቻቸው ለብስራት እንጂ ለልመና ወደ ዓለም አያሰማሩም፡፡ ብዙዎች “ኢትዮጵያ ተነሳች!” ይላሉ፡፡ ከእስራኤል እስከ ካርቢያን ከአሜሪካ እስከ አወስትራሊያ “ኑ እንሂድ! ምጽአተ ኢትዮጵያ ደርሷልና” ይላሉ፡፡ . . .

በመጹሐፉ የመሪው ወደ ስልጣን የሚመጡት እንዲህ ሲሆን ነው ተብሏል።

“ . . . በየማዕዘናቱ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በአገር ፍቅር ስሜት፣ በወገን መከራ ቁጭት ነደው፣ በመለያየት እሳት ተፈትነው ነጥረው እስኪወጡ፣ እስኪሰባሰቡ፣ ምላተ ጉባዔያቸው እስኪሟላ ድረስ ጥቂት ዘመን ይጠብቃሉ፡፡

. . . ሕዝቡ በግልጽ ይሁንታ እስኪሰጣቸው፣ ያለመታከት በትዕግስት ሕዝቡን መስለው፣ ከሕዝቡ መሐል ሁነው፣ የሕዝቡን ብያኔ ይጠብቃሉ፡፡ ይህ ትንቢት አይደለም፤ ዘመኑ የደረሰ እውነት እንጅ . . .”

Share.

About Author

Leave A Reply