“መቼም አያልፍልኝ! በይ የዘሬን ቁይልኝ” በእውቀቱ ስዩም

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰሞኑን ኑሮ ተወዱዋል:: ትንታኔና ትንቢት ጥንቡን ጥሉዋል:: እኔም አይኔን አጥቤ ድርሻየን ልተነትን ነው:: ቀልዱን እዚህ ላይ ላቆየውና ውደ ቁምነገሩ::

ባጭር ጊዜ እንደ ዶፍ የወረዱት ክስተቶች እንኩዋን ለመተንተን ለመቆጠር እንኩዋ እንደሚያቸግሩ አላጣሁትም::

በሁለት ጉዳዮች ላይ ብቻ ባገር ልጅነት የሚታየኝን ለማካፈል እወዳለሁ::

አብይ አህመድ በዘመነ መንግስታቸው ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ጌቶችን ከቦታቸው አስነስቶ “በክብር” የሸኘበት መንገድ አስደንቆኛል::

እንዲህ አይነቱ ዘዴ በፖለቲካ ፈላስፎች ዘንድ ምን ተብሎ እንደሚጠራ አላውቅም:: አንዲት የጥንት አዝማሪ ” አመንምኖ መጣል” ትለዋለች::

“እንዋጋ ይላል ጉልበቱን ያመነ

መጣል እንዳንተ ነው እያመነመነ”

ያለቺው ትዝ ብሎኝ ነው::

በስልጣን ላይ የነበሩ ጌቶች መስቀል አደባባይ ላይ ቁልቁል ተሰቅለው ማየት ይናፍቅ የነበረ ሰው በጠቅላዩ አካሄድ እንደሚከፋ መገመት ይቻላል:: ዋናው ነገር እንደ ዜጋ ምንድር ነው የምንፈልገው የሚለው ነው:: ከበቀል የሚገኘውን ርካታ ወይስ ሰላም? ሁለቱንም ባንዴ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም:: ጉልበት አለኝ : ቀን ሰጠኝ ብለህ አንዱን ለመቀጣጫ ብትገድለው ከሱ ጋር ንክኪ ያለው ሁሉ ባልሞት ባይ ተጋዳይ መመከቱ አይቀርም:: አገራችን ከወደቀችበት እንድትነሳ ካስፈለገ: የነውጥ የበቀል እና የብድር መመላለስ ፉርጎ የሆነ ቦታ ላይ መሰበር አለበት::

በግርግር ተለባብሶ ያለፈውን ሁለተኛውን ቁም ነገር አንስቼ ላምልጥ::

እነ መብራት ሃይልን ለ “ታምሪን” ብጤ ነጋዴዎች አሳልፎ ለመስጠት የተላለፈው ውሳኔ አሳስቦኛል:: በነገራችን ላይ ታምሪን ማለት በክበረነገስት ውስጥ የተጠቀሰ: ንግስተ ሳባ (ማክዳ) ኢየሩሳሌም ሂዳ ከሰለሞን ጋር ባይነስጋና በግብረስጋ እንድትገናኝ ጎትጉቶ ያሳመነ ነጋዴ ነው:: ሀብታቸውን ተጠቅመው የመንግስትን መንገድ የሚጠመዝዙ ከበርቴዎች ታምሪኖች እንላቸዋለን::

አብዛኛው ያገራችን ድሃ ተስፋው ምንድነው? የመንግስት ድጎማ አይደለምን? መክፈል እና መሸመት የሚችሉ ቱጃሮች ብቻ ሃይል ከመጠቀም አልፈው የሚያባክኑበት : ድሆች በጨለማ የሚኖሩበት ዘመን እንዲመጣ አልመኝም::

ዞሮ ዞሮ የህዝብ ትግል ግብ -መሰረታዊ ነገሮች የሚሰጡ እንጂ የሚሸጡ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው::

ሰሞኑን የህዝብን ሀብቶች ለነጋዴዎች ለመሰጠት የተወሰነው ውሳኔ አሪፍ አርጎ የሚገልጠው ሰሞኑን ከሃያሁለት ወደ የረር በር ስሄድ አንድ ታክሲ ሹፌር ያወጋኝ ወግ ነው::

አንድ ድሃ ገበሬ በክፉ ቀን : እየቀላወጠ የሰውድግስ ሲነፋ ይውልና ወደ ቤቱ ይመለሳል::

ሚስቱ እና ልጆቹ የሚላስ የሚቀመስ ሳይሸታቸው ስለዋለ ለዘር ተብሎ ደጅ ጣራ ላይ የተንጠለጠለ በቆሎ ቆልተው ለመብላት አሳብ ያቀርባሉ:: አባዋራው ግን ” አይደረግም!! በኔ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር ይህ አይደረግም ” ብሎ ቀወጠው:: በማግስቱ የሰውየው ጥጋብ እንደ ጉም አለፈ:: የልጆቹና የሚስቱ ራብ ተጋባበት:: እና ሲጨንቀው ሚስቱን ጠርቶ

” መቼም አያልፍልኝ!

በይ የዘሬን ቁይልኝ” አለ ይባላል::

 

የህዝብ መገልገያ ሀብቶችን ለነጋዴ መሸጥ ለዘር የተቀመጠ በቆሎ እንደመሸጥ ያለ ቀቢፀ ተስፋ ነው እላለሁ::

Share.

About Author

Leave A Reply