መንግስት ባለበት ሃገር እንዲህ ባደባባይ?” የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በአክቲቪስት ሰናይት መብራቱ ጽሁፍ ላይ ቁጣውን አሰማ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የዚህ ፅሁፍ መነሻ ሰናይትመብራሃቱ Senait Mebrahatu በተባለች አክቲቪስት የፌስቡክ ገፅ ላይ ከስድስት ቀናት በፊት (እ.ኤ.አ በሜይ 30 ቀን 2018) የወጣውን የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የሚጥስ እደገኛ መልዕክትን ይመለከታል፡፡ ፅሁፉም ከታች በስክሪን ሾት የምትመለከቱት ሲሆን እንዲህም ይነበባል “ሃገር የደፈረ እየተፈታ ሴቶች የደፈረ አይፈታም ማለት የአመቱ ምርጥ ቀልድ ነዉ“ ይላል፡፡

እዚህ ላይ ግለሰቧ ማስተላለፍ የፈለገችዉ የፖለቲካ መልዕክትም ሆነ አንድምታ ምንም ይሁን ምን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን የሚመለከት አይደለም!! ምክንያቱም ማህበራችን ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ሕጋዊ ተቋም ነዉና!!! ነገር ግን የሴቶች መብቶች ጥሰትን ለማስቆምና ሴቶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑባትን አገር ለመገንባት ላለፉት 23 ዓመታት የደከምንለትን ጉዳይ እንዲህ ሃላፊነት በማይሰማቸዉ፤ ለፆታ እኩልነት መከበር ዳተኛ በሆኑ እና የሴቶችን ጥቃት የሚያበረታቱ ኢ-ፍትሐዊ እና ኢ-ሕገመንግስታዊ ሃሳቦችን የሚያራምዱ ግለሰቦችንም ሆኑ ቡድናት አልያም ተቋማት ሕግን ተከትለን አጥብቀን እንደምንቃወም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

በመሆኑም ሊሰመርበት የሚገባዉ ጭብጥ በዋናነት የሴቶችን መደፈር እንደ ኢምንት አልያም እንደ ቀልድ የታየበት መንገድ እንጂ የፖለቲካ አንድምታዉንም ሆነ የተጠቀሱትን ንፅፅሮች ፈፅሞ አይመለከትም! ምንያቱም የእኛ ጉዳይ ይህ አይደለምና፡፡ ነገር ግን ሃገራችን ብዙ ደሃ፤ ያልተማሩ፤ ፍትሕ ሩቅ የሆነባቸዉና ለበርካታ ፆታዊ ጥቃቶች የተጋለጡ ሴቶች ያሉባት ሃገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ መንግስትና ተቆርቋሪ አካላት የሴቶችን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታቸዉን ለማሻሻል ቁርጠኛ በሆኑበት በዚህ ወቅት ከላይ እንደተጠቀሰችዉ ግለሰብም ይሁን መሰል አስተሳሰብን የሚያራምዱ አካላት ሚዲያ ስለተገኘ፤ አድማጭ ስላለ ወይም መድረክ ስለተመቻቸላቸዉ ብቻ እንዲህ ኢ-ሰብአዊ ፤ ኢ-ፍትሐዊ እና የሴቶችን ክብር የሚያጎድፉ የወረዱ ሃሳቦችን መሰደራቸዉ መንግስት ባለበት ሃገር እንዴት ይታያል? የሚለዉን መሰረታዊ ተጠይቅ እንድናነሳ እንገደዳለን፡፡

ሃሳብንስ በሰለጠነና ማንንም በማይጎዳ መልኩ ማስተላለፍ ጉዳቱስ ምንድን ነዉ ??? እንዲህ አይነት የሴቶችን መብት መጣስ አልያም መደፈር በአደባባይ ማወጁ ለሃገር፤ ለወገን፤ ለትዉልድስ ምን ይበጃል??? የሴቶች ጉዳይ የሃገር ጉዳይ መሆኑን ካለመረዳት የመነጨ ጨለምተኛ አመለካከት በመሆኑ ሃሳቡን በጥብቅ እናወግዛለን!!!

ለሴቶች መብቶች መከበር ሁላችንም ዘብ እንቁም!!!

(የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር)

Share.

About Author

Leave A Reply