ማርታን ምን ሰወራት? [ክፍል ሶስት] (የትነበርክ ታደለ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

…….ፊት ለፊቴ የሺሻ እቃ ተቀምጧል። ብርማ አንገት ያለው ጠርሙስ ላይ ወርቅማ ፈርጥ ያለው መሳብያ ገመድ በቄንጥ ተጠምጥሞበታል። የተቀመጥኩበት መደላድል ከፍራሽ ከፍ ያለ ከሶፋ ደግሞ ዝቅ ብሎ እግርን እንደፈለጉ ለመዘርጋት የተመቸ ነው። በግራና በቀኝ እቅፍ አድርገው የሚይዙ ሁለት ትራሶች አሉ።……ፊት ለፊቴ አንድ ትልቅ መስኮት የመሰለ ቴሌቪዥን ድምጹ ቢጠፋም የሆሊውድ ሙዚቀኞች ይሯሯጡበታል።…….

ማርታ ከደጅ እንደተቀበለችኝ እዚህ ክፍል አስገብታኝ..”ጀምረህ ጠብቀኝ” ብላ ጥላኝ ሄዳለች!

..በተገናኘን በአምስተኛው ቀን ስትደውልልኝ ልታገኘኝ እንደጓጓች በጣም ያስታውቅባት ነበር።…… በጣም የቅርብ ወዳጅነት እንዳለው ሰው ሆና ነበር ያናገረችኝ!…….. እርግጥ እኔም ጓጉቻለሁ!…. በተለይ ስለ ቤተሰቦቿ አንጠልጥላ የተወችው ነገር ልቤን ሰቅዞ ይዞኛል!…. “ምን ሆነው ይሆን›”

……የነገረችኝን ሰፈር ማግኘት ከባድ አልነበረም በጌታሁን በሻህና በኦሜዳድ ህንጻ መሀል ለመሀል የተሰራውን አዲስ አስፋልት ይዤ ቀጥ ብዬ ወረድኩ……የትኛው ጊቢ እንደሆነ ለመለየት ግን አቃተኝ!… አንድ የጫት መደብር ጎራ ብዬ “ማርታ ዲም ሀውስን ታውቀዋለህ?” አልኩት።….. ከላይ እስከ ታች አተኩሮ ተመለከተኝ።…. “አላውቀውም!….. ምን ፈለክ?” አለኝ ጥርጣሬ በገባው አይን እያየኝ።….ሚስጥራዊ ቤት መሆኑ ገባኝ!

…… “አይ…ማርታ ዘመዴ ናት!…. ዛሬ እንድንገናኝ ቀጥራኝ ነበር እና ከምደውልላት ብዬ ነው…እዚህ አካባቢ መሆኑን ነግራኛለች” አልኩት ተረጋግቼ። …ራሱ ደወለላት!….
“ሀሎ!…. ይሄውልሽ ቅድም የላኩልሽ አይነት ጫት አሁን ገብቷል!..ሰው ላኪና ውሰጂ! ደሞ አንድ ልጅ እግር ቤትሽ ጠፍቶበት ሱቄ በር ላይ ቆሟል….እሺ! በቃ! ቻው!»”
…ወዲያው የኔ ስልክ ጠራ!…. “አንተ ከረፈፍ….ሀሀሀ….”

እሷን በስልክ እያወራሁ ወደምትነግረኝ አቅጣጫ ዞርኩ። ከግቢው አቅራቢያ አጠገብ ነበርኩ!…. በር ድረስ መጥታ ተቀበለችኝ።….ግቢ ውስጥ ብዛት ያላቸው መኪኖች በስርአት ተደርድረው ቆመዋል።…. ሁለት ዩኒፎርም ያልለበሱ ዘበኞች ከመግብያው በር ግራና ቀኝ ቆመዋል።

….ከዝያ በተረፈ ጸጥ ረጭ ያለ ነው።…..ትልቅ ቪላ ቤት።….የቤቱ በሮች ተዘግተው መስኮቶች ላይ ያሉትመጋረጃዎች በቀስታ ይንቀሳቀሳሉ።…… ንጹህ ግቢ…….በስተጀርባ በኩል አራት ሰርቪስ ክፍሎች አሉ።…..ከነዚህ ወደ አንዱ ክፍል አስገብታኝ ወጣች።……

“አንተ! እስካሁን አልጀመርከውም?” አለች በሩ ላይ የተሰቀለውን መጋረጃ ከፍታ ወደ ውስጥ እየገባች።… “እ..ኧረ ጀምሬዋለሁ!” ..”ሂድ! አትዋሽ! የተጀመረ ሺሻ በደምብ ያስታውቃል!” ብላ ከአጠገቤ ቁጭ ብላ ገመዱን እንቅ አድርጋ ይዛ ከጠርሙሱ አናት ላይ ያለውን እሳት እየነካካች ማንደቅደቅ ጅመረች።…..ለደቂቃዎች ያህል በተመስጦ ሳበች።…ወሬ እንዴት እንደምጀምር ግራ ገብቶኝ ዝም አልኩ።….

“ሌላ ይምጣልህ? ይሄኛው ትንሽ ደረቅ ይልብሀል! ሜንት ይምጣልህ እሱ መካከለኛ ነው!” … “ሄሎ!” ደወለች!
“እስኪ አንድ ሜንት ይዘሽ ነይ! ስምንት ቁጥር ነኝ! ከናሲር ጫት ላይ ደግሞ ግማሹን አምጪ!” አዘዘች።
“ግን እኮ እኔ…..” አላስጨረሰችኝም!…”ማርታ ትሙት ትጣላኛለህ!…አታፍርም እንዴ?! ደግሞ ብዙ የማወራህ ነገር አለኝ!….ስለዚህ እምቢ እንዳትለኝ በአባቢ ሞት!”

….የታዘዘው መጣ!….እኔ ግን አትኩሮቴ ሺሻውንና ጫቱን ይዛ ከመጣችው ልጅ ላይ ሆነ!!…..የመድሀኒያለም ያለህ! “እዚህ ቤት የገባ ሰው ምንም መውጫ መንገድ የለውም!” ስል አሰብኩ! ….እንዴት ነው የምታምረው?!….”በቃ የሱስ ሰንሰለት መፍጠር!” … ልጅቱ አስተካክላ ወጣች!….

“ኡህ! ኡህ! ኡህ!…” ሳል በሳል ሆንኩ!…. መሳብ አልቻልኩም። ጭሱን እኔ ወደ ውስጥ ነው የሳብኩት። ግን ከምኔው አንጎሌ ውስጥ ገባ?! ልክ ሰናፍጭ እንደበላ ሰው ለሰከንዶች ያህል አእምሮዬ ዛል አለበኝ።…..

“ማርቲ በፈጠረሽ ይቅርብኝ! ባይሆን ሌላ ግዜ አስቤበት መጥቼ ባጨስ ይሻለኛል። በዚህ ላይ ማታ ክላስ አለኝ እና ሁለቱም ይቅርብኝ?!” ለመንኳት።…. እግዜር ይስጣት ተለመነችኝ።…..
“አሁንም ትማራለህ?” በአግራሞት ጠየቀችኝ!….. “ምን ላድርግ ብለሽ ነው?” ተቅለሰለስኩ።….”ካልተማርኩ ህይወትን እንዴት መጋፈጥ እችላለሁ?! ለሁሉም ነገር ደግሞ መማር አይከፋም!”

“ስማ! እዚህ ቤት አንድ ሁለት ጊዜ ብትመጣ ህይወትን እንዴት መጋፈጥ እንዳለብህ ታውቅ ነበር! የኔ ወንድም መማር ያለብህ እንዴት ከጊዜው ጋር መሮጥና እንዴት ጥለህ ማምለጥ እንደምትችል ነው። እሱ ደግሞ በዩኒቨርስቲ ትምህርት የሚገኝ አይደለም!….ሀሀሀ…ያሁኗን ቆንጆ አየሀት? ሰሞኑን ወደ ፈረንሳይ እልካታለሁ! ሀሀሀ…ዋናው ማምለጫ መንገድ ማግኘቱ ነው!…”

…..ጫቷን እየቀነጣጠሰች ወደ አፏ ትጨምራለች።…. ትንሽ ታወራና ስልክ ታናግራለች!…ትደውልና ደግሞ የተለያዩ ስሞች እየጠራች…ሺሻ እዚህ ቦታ አድርሺ፣ ጫት እንትና ጋ ጨምሪ፣ ውሀ ፍሪጅ ውስጥ ጨመራችሁ? እንትና መኪና ውስጥ ትጠራላችሁ፣ ሮዝማን አልቋል እያሉህ ነው ቶሎ ላክ…እሺ የኔ ጌታ!…”

‘ዶቅዶቅዶቅዶቅ…ቡልቅ አድርጋ ወደእኔ መለስ ትላለች!
“በቃ ወጣቱ ውሎው ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ሆነ ማለት ነው?” በድፍረት ጠየኳት!…
“ሀሀሀ..ወጣቱ?! የምን ወጣት? ..እዚህ ቤት ወጠጤ አናስተናግድም! ደንበኞቻችን በሙሉ ሴሌብሪቲ ወይም ደግሞ ከፍ ያለ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሞጃዎች ናቸው። ባለስልጣኖች ደግሞ ቀኝ እጃችን ናቸው….ሀሀሀሀ” የወሬ መሸጋገርያዋ ሳቅ ነው።

ቃም ቃም..ምንዥግ ምንዥግ…ቡልቅ ቡልቅ……. ደግሞ ስልክ ታወራለች!…. “ይለወጣል ምንም ችግር የለም። የት ነህ? እዝያው ነህ?…በቃ አሁን ይመጣልሃል!..ይቅርታ!….. አትቆጣ ደግሞ! ሀሀሀሀ..”
“ቤት ለቤትም ታደርሳላችሁ እንዴ?”
“የኔ ጌታ ደንበኞቻችን ያሉበት ቦታ ሁሉ እኛ በዝያ አለን። ሀሀሀ ቀልደኛ ነህ። መኪናቸው ውስጥ ሆነው ነው የሚያጨሱት ባክህ….ሰው እንዲያያቸው አይፈልጉም።”

“ለመሆኑ ቤተሰብ እንዴት ነው?”

…እሷ ከዝያ ቤት ከጠፋች በኋላ እኔም ብዙ አልቆየሁም። ለስራዬም ለትምህርቴም የሚመች ቤት ተከራይቼ የገባሁት ከወር በኋላ ነበር። ምን ቢቀራረቡ አከራይን ዘመድ አድርጎ መጠየቅ አልተለመደም። በዚህ ላይ የህይወት ሩጫ ለቤተሰብም ጊዜ አያሰጥም።

“ፋዘር ድሮም የሚያሰቃየው የስኳር ህመሙ ብሶበት አረፈ። አራት አመት ሆነው። ማዘርም ቤቱን ለኔ አስረክባ ጓዟን ጠቅልላ እንግሊዝ ሀገር ወዳሉ ዘመዶቿ ሄደች።” እኔም ቤትና ንብረቱን አንድ ላይ ሸጥኩና ‘እሾህን በሾህ እንዲሉ ይሄው የምታየውን ቤት ተከራይቼ ስራ ጀመርኩ። ” ..እያወራችኝ መጣሁ ብላ ወጣች።…

….”እሾህን በሾህ!” ለብቻዬ አወራሁ!….. ‘ማን ያወረሳት እሾህ? ለማንስ የምታወርሰው እሾህ?’ ያውም እንደ አንድ ትልቅ ድርጅት የተቋቋመ የእሾህ ፋብሪካ!……ለወጣቶች ስንፈራ ታላላቆች የተተበተቡበት የቆንጥር እሾህ! ….

እናቷ በወቅቱ ሲነግሩኝ ቤተሰቡ በማርታ ላይ ፍጹም ተስፋ ነበረው። በስተእርጅና የተገኘች ልጅ እንደመሆኗ ወራሽም፣ ጧሪ ቀባሪም ተደርጋ ትታሰብ ነበር። የሷ በሱስ ተጠልፎ መውደቅና ከትምህርት አለም መሰናበት ቤተሰቡን ለተስፋ ቢስነትና ለመፈራረስ እንዳበቃው ለመገመት አያዳግትም።

“ማርቲ የክላስ ሰአት ደርሶብኛል! በቅርቡ ተገናኝተን በደንብ እንጫወታለን። አሁን ልሂድ!” አልኳት ተመልሳ እንደመጣች።

“ውይ በቃ?…ብዙ የማወራህ ነገር ነበረኝ!”…
“ምንም ችግር የለውም። በቅርቡ እመጣለሁ።” እርግጠኛ ነበርኩ! ተነሳሁ!
“እኔ ምልህ?” አለች የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ሰው።
“የሞተውን ፍቅረኛዬን እንደምታስታውሰኝ ታውቃለህ?” …. “ምን?!…ማለቴ እንዴት?”…..”ቁርጥ እኮ እሱን ነው የምትመስለኝ!” ቅጭም አለች!
ይቀጥላል?

 

Share.

About Author

Leave A Reply