ማርታን ምን ሰወራት? [ክፍል አራት] (የትነበርክ ታደለ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

…..ሀያ ሁለት ሳይ ካፌ ደጅ ቁጭ ብዬ አሻግሬ ሊዲያ ካፌ የፈረሰችበትን ቦታ እቃኛለሁ። ከአመታት በፊት አጠገቧ ባለው ሆቴል መስፋፋት ሳቢያ ሳትፈርስ ሊዲያ ካፌ የብዙ ሰው ምርጫ ነበረች። እኔማ አብዝቼ ጎራ እልባት ነበር። ….. የአገልግሎቱ ጥራት፣ የዋጋው አሳማኝነት፣ የአስተናጋጆቹ ጸባይና ቅልጥፍና…ፍጹም የምትወደድ ካፌ!….. ዛሬ በስደት ወደ ቀበና ሄዳለች።

….ሰአቴን አየሁት…. አስር ደቂቃ ይቀረኛል!….ማርታ በቅርብ እንገናኛለን እንዳላለችኝ ባላወኩት ምክንያት “ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ” እያለች ከሁለት ወራት በላይ ሳላገኛት ቀረሁ። ዛሬ እንደምንገናኝ ቃል ገብታልኝ ይሄው ከቀጠሮው ሰአት ቀድሜ ተገኝቻለሁ።… “ለምን ሺሻ ቤቷ እንድመጣ አልፈለገችም?” ሌላ ጥያቄ ሆኖብኛል! .. ዝናብ በስሱ እየዘነበ ነው። ሳይ ካፌ ደጁም ውስጡም በሰው ተሞልቷል።

..ሀሳቤን ለማሰባሰብ ደጅ ላይ ከተኮለኮሉት ጋዜጣ አዟሪዎች አንዱን ጠራሁና ሁለቱን ገዝቼ ማገላበጥ ጀመርኩ።…… ‘ከጋዜጦቻችን ግን ምን አዲስ ነገር ይሆን የምንፈልገው? የአቀራረብ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር በያዝኳቸው ሁለት ጋዜጦች መካከል ምንም ልዩነት የለም። ተመሳሳይ ዜና! ….

….ስልኬ ጠራ!… ማርታ ናት!…’ቀረሁ ልትለኝ ባልሆነ!’
“ሀሎ!”
“ስልኩን ሳትዘጋው እያናገርከኝ ውጣ ደጅ ላይ መኪና ውስጥ ነኝ!”
“እ! እንዴት!”
“ነገርኩህ!” ጠረጴዛው ላይ ያለውን የደረሰኝ ማቀፍያ ውስጥ ሂሳብ አስቀምጬ ስልኩን ጆሮዬ ላይ እንደ ያዝኩ ወጣሁ….
ፊት ለፊት ከተደረደሩት መኪኖች መካከል የቆመ አንድ ጥቁር ሰማያዊ ትዮታ ኮሮላ መኪና ፍሬቻውን ‘ቦግ ብልጭ ሲያደርግ አየሁትና ትኩረቴን ወድዝያው አደረኩ። ደገመው!…..ቀጥ ብዬ ሄድኩ….
ቀረብ ብዬ ሳይ ማርታ ሌላ ሰው መስላ መሪ ጨብጣ አየኋት!…. “ህም!”… ጋቢና ከፍቼ ገባሁ!….በፈገግታ ብቻ ሰላም ብላኝ የመኪናዋን መስታወት አንድ ሶስት ጊዜ ሞዠቅ ሞዠቅ አድርጋ ጉዞ ጀመረቸ።

“ወዴት ነው?” ተረጋግቼ ጠየኳት መቼም በዚህ ዝናብ ፈራርሻ ከመቃም ውጪ ሌላ ሀሳብ ይኖራታል ብዬ አላሰብኩም።
“መኪና ውስጥ ሆነን ብናወራ ይሻላል ብዬ ነው።”
“ለምን? ምኑን?”
“ለጥንቃቄ!” አስፈራችኝ!….. “ምነው ችግር አለ እንዴ?” …..ዝናቡ እየረገጠው ነው። እሷም መኪናዋን በስተ ግራ አዙራ ቁልቁል ወደ ቺቺኒያ አቅጣጫ አስወነጨፈቻት። አትላስ ሆቴልን በስተግራ ትታ ቀጥታ ወደ ደሳለኝ ሆቴል የሚወስደውን መንገድ ያዘችና ከሆቴሉ ጎን ካለ አንድ የመኪና ማከራያ ግቢ ፊት ለፊት ስትደርስ የአስፋልቱን ጥግ ይዛ ቆመች።

…..አንዳች ነገር መጠርጠር ጀምርያለሁ!…. የሆነ የምትደበቀው ነገር አለ!….”ወዴት ልትወስደኝ ነው?” ጨነቀኝ! ዝናቡ ደግሞ ጨምራል።

“ይቺን መኪና ከሶስት ቀን በፊት ነው ከዚህ ድርጅት የተከራየኋት!….አሁን እመልሳታለሁ!…” ያወራቸው ነገር ምንም አልገባኝም!….
“ምን ሆነሻል ማርታ?”
“ከጥቂት ሰ አታት በኋላ እሄዳለሁ!”
“የት? የት ነው የምትሄጂው?”
“ሀገር እለቃለሁ!”
“ለምን? ምን ሆነሻል? እስኪ በደምብ ንገሪኝ!”…መቀመጫውን ወደ ኋላ ሳብ አደረገችና ጋለል አለች።…… ምንም ልትረጋጋ አልቻለችም።….”ሰዎቹ እርስ በርስ ተያይዘዋል!…”
“እነማን?”
“አንተ አታውቃቸውም!..ከብዙ ሰዎች ጋር ነው የምሰራው!..ስራችን ሺሻ ማስጨስ ወይም ጫት ማስቃም ብቻ እንዳይ መስልህ!….ይህ እንደ መሰባሰብያ የምንጠቀምበት ስራ ነው። እርግጥ ሙዋሰልና የሺሻ እቃዎችን እናስገባለን። ነገር ግን ዋናው ስራችን ወደ ሀገር ውስጥ የተለያዩ እጾችን ማስገባት፣ ሴቶችን ለውጭ ሀገር ሰዎች መደለል እና ማገናኘት፣ ከዝያም አልፎ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ነው… አንተ አሁን የምንገርህ ነገር በደምብ አይገባህም…”

ኦ! አምላኬ! ፍርሀቴ ጨመረ…በውስጥ መስታወት ወደ ኋላ ተመለከትኩ!…”ማን ተከትሎን ይሆን?…..
“አትፍራ! ዛሬ ሁላችንም ሺሻ ቤት ተቀጣጥረናል! ሁሉም ወደዝያው ነው የሚሄዱት!…”
“ምንድነው የተፈጠረው?”
“ከሳምንት በፊት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል የተባለ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀሺሽ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ የት እንደደረሰ አልታወቀም። ከመካከላችን አንድ ሰው ተጠርጥሯል።….እሱም ሰሞኑን ስራ በዛብኝ ብሎ መጥፋት አብዝቷል..እና ዛሬ በሰውየው ላይ ለመፍረድ ነው ቀጠሮው።”
“ምን? ማለቴ የምን ፍርድ!” “ትከሻዋን እርግፍ አደረገችው! ..”እግዚኦ መሀርነ ክርስቶስ!” አማተብኩ!….
“እና አንቺስ?” ….”በቃኝ! ቀድሜ ተዘጋጅቻለሁ! ሁሉን በቦታው በቦታው አድርግያለሁ….በረራዬ ከአንድ ሰአት በኋላ ነው!”……..
ዝብርቅርቅ አለብኝ!…..ምንድነው የምትነግረኝ?!….ለምንድነው የምትነግረኝ!….
“ለምንድ ነው አሁን ይሄን ሁሉ ለኔ የምትነግሪኝ?!” በመገረም ጠየኳት!….
“ፍቅረኛዬን ካጣሁ በኋላ በውስጤ ያለህ አንድ ወንድ አንተ ብቻ ነህ!….እወድሀለሁ!…የምትረዳኝ ይመስለኛል..እና ይህን ሳልነግረህ መሄድ አልፈለኩም!….አፈቅርሀለሁ!…የነገን ደግሞ ማን ያውቃል!….

ጆሮዬ እንጂ ልቤ እዝያ የለም!…. ድም! ድም! ድም! ከበሮ እየመታ ነው።

“እሺ አሁን መኪናውን አስገቢና ወደ ኤርፖርት እየሄድን የቀረውን እንነጋገራለን!…. እሺ ብላ መኪናዋን አስነሳችና ታጥፋ ወደ መኪና ማከራያው ገባች። ወረድኩ! እሷ ክፍያ ልትፈጽም ወደ ቢሮ ገባች!…መሰስ ብዬ ከግቢው ወጣሁና በሩጫ አጠገቡ ወዳለው ደሳለኝ ሆቴል ገባሁ!…… ፊት ለፊት ላለው ዘበኛ በጆሮው ሹክ አልኩት!… በፍጥነት የጥበቃዎቹን ሀላፊ ይዞልኝ መጣ!…. እሱ ወደ ፖሊስ ጣብያ ስልክ ሲመታ እኔ ደግሞ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ቆሜ ቁልቁል እከታተላለሁ!…..

…..ከአስር ደቂቃ በኋላ ፖሊሶች ለዘበኞቹ አለቃ በሰጠሁት ምልክት ታግዘው ከመኪና ማከራያው ግቢ ማርታን ይዘዋት ሲወጡ አየሁና ተንደርድሬ ወረድኩ!….ከማርታ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጥን….ሀሳቡ የቀለለለት ሰው እንጂ የደነገጠች ወይም የከፋት አትመስልም!…. ለፖሊሱ ጠቋሚው እኔ መሆኔን ነግሬ ቀሪውን ለማስረዳት አብሬ ጉዞ ቀጠልኩ……
ተ ፈ ጸ መ !
ከስሜ በስተቀር ~ልቦለድ!.

 

Share.

About Author

Leave A Reply