ማስታወቂያና መልዕክቱ አራንባና ቆቦ- አንበሳ ቢራ ( ናታን ዳዊት )

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ለወራት የአገራችን ሚዲያዎችን የአየር ሰዓት ያጣበበ ማስታወቂያ፣ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ቆይቷል፡፡ ማስታወቂያው ከሚዲያ ባሻገር፣ የተለያዩ የማስታወቂያ መንገዶችን በመጠቀም ፍዳችንን ሲያበላን ከርሟል፡፡ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በማጣበብ መልካም ምግባር የሚሰብከውን ማስታወቂያ በምን ይሆን ሲያስነብበንና ሲያብሰለስለን ቆይቷል፡፡

እነዚህን ማስታወቂያዎች አሁንም ድረስ በየሚዲያው እየተመለከትን፣ እያደመጥንና እያነበብን እንገኛለን፡፡ የከተማችን የባቡር ጣቢያዎች ወይም ፌርማታዎች ሳይቀሩ ለዚህ ማስታወቂያ ተፈቅደው ማንነቱን ሳይገልጽልን በቆየው ማስታወቂያ ተሸፍነዋል፡፡ ‹‹ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም›› ይላል የማስታወቂያው መልዕክት፡፡ በውስጡም ሌሎች ተስፋ ሰጪ መልዕክቶች ያጀቡት ነበርና ብዙዎቻችን መልካምና አዲስ ነገር ይዞ የሚመጣ ምን ነገር እናይ ይሆን በማለት በልብ አንጠልጣዩ ማስታወቂያ የሚገለጠውን ዕውነት መጨረሻ ለማወቅ ጓጉተን ነበር፡፡

‹‹ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም›› ከሚለው ማስታወቂያ ጀርባ ከመልካም ነገር በላይ ምንስ ይጠበቃል? በማስታወቂያው መልካም ምግባር መግለጫ በሆኑ ቃላት የታጀቡ መልዕክቶች ምን ይሆኑ ብሎ ራሱን ያልጠየቀ፣ እርስ በርሱ ያልተነጋገረና ከሰዎች ያልተወያየ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ግብረገብነትን ተላብሶ ሲዥጎደጎድ የከረመው መልዕክት ግን የአልኮል መጠጥ ለማስተዋወቅ ነው ብሎ ማን ያስባል፡፡

ማንስ ቢሆን ልባምነትን፣ መልካም ምግባርን በምንም መልኩ ቢሆን ከአልኮል መጠጥ ጋር ለማያያዝ እንዴት ይዳዳዋል፡፡ የልባምነት መገለጫ አገርን የሚጠቅም ተግባርና ጀግንነትን፣ ብልህነትን የሚያፀባርቅ፣ ትጋትና አስተዋይነትን የሚያነግሥ እንጂ ቢራን ማን ልባም ያደርገዋል፡፡ ማስታወቂያውን የሠሩት የሽያጭ ሰዎች ወይም በዘመኑ የግብይት ሥርዓት መሠረት የማስታወቂያ ዘመቻ ቀማሪዎች ልብ ሰቀላው ቢሳካላቸውም የመጨረሻው ግባቸው ግን ውግዘትን ማትረፍ ሆኗል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply