ሜቴክ ሀገራችንን በእብቅና በገለባ ከመሙላቱ በፊት…. (በአሳዬ ደርቤ ~ የቃሊቲ ፕሬስ ተጋባዥ ጸሀፊ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

‹ብክነትን የሚያስቀረው የካይዘን ፍልስፍናና ሜቴክ ላይ ሲተገበር በብክነት ፈንታ ምርትን እንዴት ማስቀረት ቻለ?›

ካይዘን ከለውጥ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

የካይዘን ፍልስፍናን በመጠቀም መበልጸግ ከቻሉ አገሮች ጃፓን ተጠቃሽ ስትሆን… ፍልስፍናውን በመተርጎም ማደግ ከቻሉ ግለሰቦች መሃከል ደግሞ ዶክተር አቡሽን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ካይዘንን ከጃፓን አገር ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት አቶ መለስ ሲሆኑ ፍልስፍናው ተግባራዊ ከሆነባቸው ተቋማት መሃከል ስኳር ኮርፖሬሽን እና ሜቴክ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

የካይዘንን ፍልስፍና በዋናነት ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መሃከል የምርት ብክነትንና የስራ መጓተትን ማስቀረቱ ሲሆን ‹ይሄውም ከላይ በጠቀስኳቸው ተቋማት ውስጥ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል› ስላችሁ ስኳር አልባ ሻይ እየጠጣችሁ ‹‹የአባቴ አምላክ ይረጋግጥህ›› ብላችሁ ለመራገም ባትቸኩሉ ጥሩ ነው፡፡

ምክንያቱም ከላይ ያለውን መረጃ በምንጭነት ያቀበለኝ ተመስገን በየነ በመሆኑ… ከዚህ በፊት ‹እንደቀጠፍክ ኑር› በሚል እርግማን የኢቢሲ ዜና አንባቢ መሆኑ ሳያንስ ሌላ እርግማን መጨመር አግባብነት የለውም፡፡

“kaizen”የሚለው ቃል ሲተረጎም “kai” = change “zen” = good, simply means “change for better” ማለት ሲሆን… METEC- የሚለውን ምህፃረ–ቃል ደግሞ አንዳንድ ጸረ-ልማቶች May Twenty Expansion of Corruption በማለት ሳይተነትኑት አይቀሩም፡፡

ያም ሆነ ይህ ሜቴክ ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በምታደርገው ሽግግር ውስጥ በሁሉም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ከረዥም የግንባታ መጓተት በኋላ በስኬት ፈንታ ውድቀትን የሚያስረክብ ተቋም መሆኑ በሁላችንም ዘንድ ቅቡል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ በስኳር ምርት ያንበሻብሹናል ስንል ሟምተው የቀሩትን የስኳር ፋብሪካዎቻችን ናይትሮጅን ያመርታል ሲባል እንደ ኦክስጅን ተንኖ የቀረውን የያዮ የማዳበሪያ ፋብሪካችንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይሄም ሆኖ  ግን ከላይ ያስቀመጥነውን ግምገማችንን እኛና ቋሚ ኮሚቴዎቻችን እንጂ ሜቴክ አይስማማበትም፡፡ ‹‹የእኛ ፋብሪካዎች ምርት ባይታፈስባቸው እንኳን በቂ እውቀት ስለሚገኝባቸው ሊናናቁ አይገባም›› ባይ ናቸው፡፡

ለነገሩ እውነታቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን ብንወስድ… ምንም እንኳን የአርሶ አደሩን መሬት የሚያዳብር ማዳበሪያ ማምረት ባይችልም በውድቀቱ ጭንቅላታቸውን፣ በበጀቱ ደግሞ ኪሳቸውን እንዳዳበሩበት አይጠፋንም፡፡ የእኛ ቅሬታ በትምህርት ሚኒስቴር ስር መተዳደር የሚገባው ተቋም ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር መሆኑ ነው፡፡ በጀቱም ቢሆን በፕሮጀክት ስም ከሚመደብ ይልቅ ለትምህርት ተብሎ ቢሰጣቸው ከስራቸው ጋር ሊዛመድ ይችላል፡፡

ይሄን ብዬ ወደ ካይዘን ስመለስ በዚህ ተቋም ውስጥ ለሚሰራ ጓደኛዬ ‹‹ብክነትን የሚያስቀረው ካይዘን ሜቴክ ላይ ሲተገበር በብክነት ፈንታ ምርትን እንዴት ማስቀረት ቻለ?›› ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ ‹ችግሩ የተከሰተው ካይዘንን በጥልቀት ከመረዳት እንጂ ካለመተግበር አይደለም› የሚል ነበረ፡፡

‹እንዴት?› አልኩት

‹‹ካይዘን በግንባታ ምዕራፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የሚከሰት የስራ መጓተትንና የምርት ብክነትን ማስቀረቱ የተረጋገጠ ቢሆንም ፍልስፍናው በጣም ሲሰርጽህ ግን ብክነቱን ብቻ ሳይሆን ምርቱንም የሚያስቀርበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ስኳር ፋብሪካ መገንባትም ሆነ ስኳር ማምረት የስራ መጓተትንና የምርት ብክነትን የሚያመጣ ከመሰለህ… ፋብሪካውን እንደ ብክነትና ቅንጦት በመቁጠር እርግፍ አድርገህ ትተወውና በጀቱን ወደ ካዝናህ ታስገባለህ…›› ይለኝ ያዘ፡፡ ሆኖም ግን ማብራሪያው እንዳልገባኝ ሲረዳ ‹ምን መሰለህ! ሶሻሊዝም እየዳበረ ሲመጣ ወደ ኮሚኒዝም የእድገት ደረጃ እንደሚሸጋገረው ሁሉ የካይዘን እድገት ደግሞ ‹አለመከወንን› ይወልዳል፡፡ ይሄም በዐጭሩ ሲጠቃለል ‹ምንም ላለመሳሳት ምንም አለመስራት› እንደሚባለው  ‹ምንም ላለማባከን ምንም አለመከወን መፍትሔ ነው› በማለት አስገራሚ ገለጻውን አጠቃለለ፡፡

ልክ እንደ ጓደኛዬ ሁሉ እኔም ሃሳቤን ጠቅለል ሳደርገው አገራችን ወደ ኢንዱስትሪው ለምታደርገው ሽግግርም ሆነ ድንግርግር ሜቴክ መጠቀስ ያለበት በአሸጋጋሪነት ሳይሆን በእንቅፋትነት ነው፡፡ እንደውም አንድ ፕሮጀክት በሚታቀድበት ወቅት ‹ስጋት› በሚለው ርእስ ስር ከዶላር እጥረትና ከብረታ-ብረት መጥፋት ጋር ‹የሜቴክ ተቋራጭነትም› አብሮ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም ቢሆን ‹እየተማርኩ እሰራለሁ.. እየሰራሁ እማራለሁ› በሚል መርህ የሚመራውን ሜቴክን ሲገመግም ‹የእናንት ትምህርት የሚያበቃው መቼ ነው?› ከማለት ይልቅ ‹የምትፈርሱት መቼ ነው?› ብሎ ቢጠይቅልን መልካም ነው፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ‹‹በግንቦት ሃያ ፍሬዎች የተደራጀው ሜቴክ አገራችንን በገለባና በእብቅ ከመሙላቱም በላይ የገነባናቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ሳይሆን ክሸፈት የሚታፈስባቸው መጋዘኖች ማድረጉ አይቀርም፡፡

አሳዬ ደርቤ

Share.

About Author

Leave A Reply