ምርጫ 97ን ተከትሎ “መንግስት መጠነ ሰፊ ጉልበት መጠቀሙን ይፋ ያደረገው አጣሪ ኮሚሺን ህዝብ እውነቱን ይወቀው ይላል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ቀጥሎ ያለውን መግለጫና ለተወካዮች ም/ቤት ልከነው የነበረውን ደብዳቤ በተቻለ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው በማድረግ እንተባበር (ቀጥሎ ለምንወስደው እርምጃ መሰረት ስለሆነ ከሁሉ በፊት ሁሉም ሰው ጉዳዩን ይረዳልንና የህልና ፍርድ ይስጥበት)፡፡

ውድ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግስት ለነጻነት እና ለፍትህ ድመጻችሁ እዲሰማ ለቆሰላችሁ ለታሰራችሁ እና መጫረሻ ላይ ፍርዳቸሁን ለተቀማቸሁ ወገኖቻቸን፤ እንዲሁም ለሰው ሕይወት፤ ለፍትህ ለሰብኣዊ መብት የሚገዳችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ!

በ1997 ዓ.ም. የነበረዉን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገርቱ ክልሎች የተነሳዉን ሁከትና መንግስት ሁከቱን ለማስቆም በሚል የወሰደዉን እርምጃ በሚመለከት 1ኛ/ መንግስት የወሰደዉ እርምጃ ተመጣጣኝ መሆን አለመሆኑን፤ 2ኛ/ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ ህግን የተከተለ መሆን አለመሆኑን፤3ኛ የደረሰዉን የህይወትና የንብረት ጉዳት መጠን መርምሮ ለፓርላማ ሪፖርት እንዲያቀርብ አስራ አንድ አባላት ያሉት አንድ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 478 /1998 ተቋቁሞ እንደነበር ሁላችንም የምናስተዉሰዉ ነዉ፡፡

በወቅቱ የፌዴራል ፖሊሲ ኮሚሽን ኮሚሽነር ህዳር 1/1998 ዓ.ም. ለተወካዮች ም/ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በሁከቱ ውስጥ የተሳተፉ ዜጎች ከተተኳሽ እስከ ቦንብ የጦር መሳሪያ የታጠቁ፤ በቀድሞ የጦር ሰራዊት አባላት እየታገዙ ሲያጠቁንና ባንኮችንም ሲዘርፉ የነበሩ የነውጥ ሀይሎች ስለነበሩ የሃይል እርምጃ ተወስዶባቸው የተገቱ ስለመሆኑ ሪፖርት አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኮሚሽናቸን ለሰባት ወራት ጥልቅ ምርመራ ካደረገ በኃላ መንግስት በዜጎቹ ላይ እጅግ የከፋና ያልተመጣጠነ እርምጃ መዉሰዱን፤ በዚህም በአዋጁ በተጠቀሱት ጥቂት ቀናት ዉሰጥ ብቻ 193 ሲቪሎችና ስድስት (6) ፖሊሶች መገደላቸዉን፤ ሰባ አንድ (71) ፖሊሶችና 763 ሲቪሎች መቁሰላቸውን፤ ከ30000 በላይ ዜጎች ለእስርና ለኢሰብአዊ አያያዝ መዳረጋቸዉን፤ አንዳንዶቹ በታሰሩበት እስር ቤት መገደላቸዉን ፤ የሰዉነት ክፍሎቻቸዉ የተቆረጡና የተኮላሹም እንደነበሩ፤ በርካቶች ክፉኛ መገረፋቸዉን፤ ንብረታቸዉ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መፈተሹንና መወሰዱንና ለባለቤቶቻቸዉ አለመመለሱን፤ የለበቂ ምክንያት ቤቶቻቸዉ ድረስ በመሄድ ከአንድ በላይ የቤተሰብ አባላት ላይ ግድያ መፈጸሙንና ማንም ለእንደዚህ አይነቱ ህገ-ወጥ ድርጊት አለመጠየቁን፤ ሁሉም ሲቪሎች መሳሪያ ይዘዉ አለመዉጣታቸዉን፤ ሆኖም ግን አብዘኞቹ በጦር መሳሪያ መገደላቸውን፤ የፖሊስ አባላት በገዛ ባልደረቦቻቸዉ መገደላቸውን..ወዘተ ካጣራ፤ካረጋገጠና በሰፊዉ ከተወያየ በኃላ በደረሰዉ ድምዳሜ መንግስት የወሰደዉ አርምጃ የልተመጣጠነ መሆኑን፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት መዉደሙን፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብት አያያዝም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸዉን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶችንም ሆነ የህገ-መንግስቱን ድንጋጌዎች የጣሰ ነዉ ሲል 8 ለ 2 በሆነ ድምጽ ሰኔ 26/1998 ዓ.ም. ወስኗል፡፡

በወቅቱ የኮሚሽኑ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ከላይ የተገለጸዉን የሰኔ 26/1998 ዓ.ም.ን ዉሳኔ ከወሰኑ በኋለ ዉሳኔዉን እንዲቀይሩ በደረሰባቸዉ ጫናና ማስፈራሪያ ምክንያት ህይወታቸዉን ለማትረፍ ውሳኔውን እና ተያያዥ ማስረጃዎች ይዘው ከሃገር በሸሹበት፤ የዉሳኔ ቃለ-ጉባኤና ሰነዶች እንዲቃጠሉ እና አባላቱም ያለምክርቤቱ እዉቅና ለተጨማሪ ጊዜ ተገደው እንዲቆዩ በማድረግ የዉሸት ሪፖረት በግዳጅ እንዲዘጋጅ፤ እንዲቀርብና ለምክርቤቱ እንዲነበብ ተደርጓል፡፡ ይህ የሀሰት ሪፖርት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሚቀርብበት ወቅት የአሜሪካን መንግስት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት (ኮንግሬስ) እዉነተኛዉን ዉሳኔ ከቪዲዮ ቅጅ ጋር ትክክለኛነቱን ካረጋገጠ በኋለ የኮሚሽኑን ሰብሳቢ የዳኛ ፍሬህይወት ሣሙኤልን እና የኮሚሽኑን አባል አቶ ምትኩ ተሾመን ምስክርነት እንዲሁም የም/ል ሰቢሳቢውን ዳኛ አቶ ወልደሚካኤል መሸሻን የቪዲዮ መልእክት እ.ኤ.አ ኖቬመበር 16/2006 የሰማ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ አባላት በዝህ ምስክርነታችን የሚንኮራበት ሆኖ ሳይሆን በወቅቱ በገዛ አገራችን እዉነትን ለመስማት ካለመፍቀድ አልፎ ይህን እዉነታ መናገር የሚያስገድል በሆነበት ሁኔታ ከሃገር ሸሽቶ እዉነትንና ፍትህን ዋጋ ሰጥቶ ለመስማት ለሚፈልግ ሁሉ መናገር መቻል ተገቢ ነበር፡፡

ይህን የተዛባዉን የሃገርና የዜጎች ፍርድ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኀላፊነት በተሞላ መልኩ አይቶት በእጃችን ያለውን እዉነተኛዉ ሪፖርት በኮሚሺኑ አማካይነት በይፋ ተሰምቶ በማህደር ውስጥ እንዲቀመጥ ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም.ጀምሮ ለወራት ስንጥር ቆይተን በቅርቡ የተወካዮች ም/ቤት እውነተኛውን ሪፖርት መስማት እንደማይችል ገልጾ ይልቁን ደብዳቤያችን በጥቆማ ደረጃ ታይቶ ለጠቅላይ አቃቤ ህግና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማቅረብ እንደምንችል መገለጹን ሰምተናል፡፡ በዚህ ውሳኔው የተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤና ም/ቤቱ የጉዳቱ ሰላባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቊስል ላይ ጨው ነስንሷል፡፡ በመሰረቱ በአዋጁ መሰረት ለም/ቤቱ ያቀረብነው ሪፖርት የለም፡፡ ሪፖርቱ በእጃችን ነው ያለው፡፡

ይህ የአሁኑ የም/ቤት ውሳኔ ለፍትህና ለእዉነት መቆምን እና እውነተኛ ዳኝነትን በሃገር ደረጃ ዋጋ ያሳጣ፤ ብሎም የፍትህ ስርዓቱ ዉስጥ ለፍትህና ለእዉነት ከመቆም ይልቅ አድርባይነት እና እከከኝ ልከክህ እዲስፋፋ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ ሁላችንንም ክፉኛ አሳዝኖናል፡፡ በሌላ በኩል ለተወካዮች ም/ቤት ያቀረብነውን አቤቱታ ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ራችን እንድደርስ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር አማካይነት ልከን የነበረ ቢሆንም በውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት በተደረገው ዳባ ዳብዳቤው ለጠቅላይ ሚ/ሩ እንዳይደርስ ተድርጎኣል፡፡ አሁን ዘግይቶ መረዳት እንደቻልነው ይባስ ቢሎ ለጠቅላይ ሚ/ሩ ቢሮ በፈክስ የላክነውም አቤቱታ ጭምር እንዳይደርሳቸው መደርጉን፤ እንድሁም በአሜሪካ ለኢትዮጵያ ኢምባሲ የላክናቸው የፈክስ መልእክቶች ለሚመለከተው አካል እንዳይደርስ መደረጉን በአካል ጭምር በመገኘት ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ይህ ሀላፍነት የጎደለው የተወካዮች ም/ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሀላፊዎች ተግባር ጠቅላይ ሚ/ራችን ዶ/ር አብይ አህመድ በመንግስት እርምጃ ለተጣሰው መብትና ለጠፈው ህይወት የጠየቁትን ይቅርታ የሚያንኳስስ እና ትርጉም የለሽ የሚያደርግ ነው፡፡ የ1997 ዓ.ም. አጣሪ ኮሚሽን አቻ ተቋም ሆኖ በህግ የተቋቋመ እና በህጉ መሰረት ውሳኔ የሰጠ እንጂ ለሌሎች ኮሚሽኖች ጥቆማ እነዲሰጥ የተቋቋመ አይደለም፡፡

ስለሆነም ከአሁን በኋለ ይህ ጉዳይ ተጎጂዎችና ሀላፊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተሳትፎበት እልባት ለመስጠት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘጋጀን መሆናችንን ከመግለጽ ጋር ጉዳዩ ሌላ አቅጣጫ ከመያዙ በፊት የተወካዮች ም/ቤት መነጋገር ከፈለገ በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት ማንንም ግለሰብ ሆነ ቡድን እላማ ሳይደረግበት ቢሎም የለውጡንም መንፈስ ሳያሻክር፤ የህዝብ ፍትህ ሳይጓደልና እውነት ሳይንኳሰስ ሚዘኑ በተጠበቀ ሁኔታ በማቅረብ ፋይሉን ለመዝጋት እንደምንሻ፤ ለዝህም አቀራረቡ እንዴት መሆን እንዳለበት በዝርዝር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በድጋሚ እየገለፅን፤ ይህ ሳይሆን ቢቀር ለፍትህና ለእውነት ቢሎም ሰሰብአዊ መብት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እያረጋገጥን ይህንኑ በሚመለከት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት፤ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሰብኣዊ መብት ተቋማት ጋር ለቀጣይ እርምጃዎች እየተዘጋጀን መሆናችንን በአክብሮት ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ከሰላምታ ጋር

Share.

About Author

Leave A Reply