ምስጢር የተጠማው ጎልማሳ ቅዱሱን ጽዋ የማየት ጉጉት በ‹‹እመጓ››

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከጥንት ጀምሮ በዓለም ሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ምስጢራዊ ይዘት ያላቸውን አገላለፆችን ማስፈር የተለመደ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ ይዞ ነገር ግን ምስጢራዊነቱንና አወዛጋቢነቱን ይዞ የቀጠለው ‹‹የቅዱሱ ጽዋ›› ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ቅዱስ ጽዋ አንዳንዶች ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ ክቡር ደሙን የመሠለበትን የወይን ጠጅ የሰጠበት ነው ይላሉ፤ አንዳንዶች ቅዱስ ጽዋ የተባለው የሙሴ ጽዋ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹እመጓ›› የተሠኘው የዶክተር አለማየሁ ዋሴ መጽሐፍ ደግሞ የዚህን ቅዱስ ጽዋ ምንነት ወደ ቀራንዮ (ክርስቶስ ወደ ተሰቀለበት ዕለተ ዓርብ) ይወስደውና ቅዱስ ጽዋ መልአኩ ኡራኤል የክርስቶስን ደም የቀዳበት ነው ብሎ በራሱ መንገድ ይመጣል፡፡

እንግዲህ ይህ እመጓ የተሠኘው መጽሐፍ ዋነኛ ታሪኩ የአንድን ምስጢር የተጠማ ጎልማሳ ቅዱሱን ጽዋ የማየት ጉጉት የሚያትትና የሚተርክ ሆኖ በይዘቱ ግን ታሪክ፣ ኃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ተፈጥሮ፣ ውበት፣ ሰብአዊ ፍቅር እንዲሁም በትዝታ ፈረስ ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚያስጋልብ የትረካ መጽሐፍ ነው፡፡ መቼቱን ሰፋ አድርጎ ቢጀምረውም በዋናነት በማዕከላዊነት ኢትዮጵያ በሰሜናዊ የሸዋ ክፍል መንዝ አካባቢ ያደረገ ነው፡፡ የመጽሐፉ ስያሜም በዚሁ አካባቢ ከሚገኝ እመጓ ኡራኤል ከተባለ ገዳም የተወሰደ ነው፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ልዩ ባህሪያት ባሻገር መጽሐፉ ተቃርኖዎችን የሚገልጽበት መንገድ መሳጭና ልብን የሚነካ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በውስጡም ጽናትን የሚፈታተኑ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች በአንድ ወገን ለየትኛውም ችግር የማይበገር ልዩ ጥናትና ጉጉት በሌላኛው ወገን የሚፋለሙበት ልብ አንጠልጣይ ትረካም ነው፡፡ በመጽሐፉ መንፈስና ሥጋም ሲሟገቱ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ታሪካዊ ፍልስፍናም ጭምር የታከለበት ነው፡፡

የመጽሐፉ ሙሉ ታሪክ ጣዕም ያለውና ማራኪ ከመሆኑ የተነሳ የመጽሐፉን አጭር ታሪክ ቀነጫጭቦ ማቅረብ ቀላል የሚባል ተግባር አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የታሪኩን አበይት ገጾች ለማየት ስንሞክር፡-

ታሪኩ ሲጀምር ‹‹ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ…›› ብሎ ነው፡፡ በዚህም መነሻውን በዘመናዊ መንገድ ማድረጉን እንረዳለን፡፡ ጉዞውንም ወደ ዋሽንግተን ያደረገው ይህ የመጽሐፍ ተራኪ በመጽሐፍ ውስጥ ዋናው ገጸ ባህሪ ነው፡፡ እርሱም ሲሳይ ይባላል፡፡ የሲሳይ የጉዞው መዳረሻ ዋሽንግተን አይደለችም፡፡ ይልቁንም ዓላማው በዋሽንግተን አድርጎ ወደ ሉዚያና ግዛት መሻገር ነው፡፡ የሄደውም በኒው ኦርሊያንስ ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ የኢትዮጵያን አትክልትና ፍራፍሬ ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ነገር ግን በልቡ ከዚህም ባሻገር ሌላ ምስጢራዊና ትልቅ አጀንዳ ይዞ ነው፡፡

ሲሳይ ዋሽንግተን ደርሶ የሆቴል ክፍል ከያዘ በኋላ በፍጥነት ለአንድ ሰው ስልክ ደወለ፡፡ ስልኩን ከወዲያኛው ጫፍ ያነሳው አንድ አሜሪካዊ ሲሆን፤ እርሱም ፕሮፌሰር ዴቪድ ራምስፊልድ ነው፡፡ ሲሳይም አንድ የምርምር ሥራ እየሠራ እንደሆነና የእርሱን ድጋፍ እንደሚፈልግ ገለጸላቸውና አድራሻ ተለዋውጠው ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ፡፡

እንግዲህ ታሪኩ ከአሜሪካዋ ኒው ኦርሊያንስ እስከ ኢትዮጵያዋ እመጓ ቆላ ድረስ የተዘረጋ ሁለ ገብ ትረካ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሲሳይና ፕሮፌሰር ዴቪድ ራምስ ፊልድ በቀጠሯቸው ዕለት ሲገናኙ ስለ ቅዱስ ጽዋ ምንነትና ስለ ሁኔታው ባሉት ግምቶችና መላምቶች ላይ ተወያዩ፡፡ ይህም ለሲሳይ የምስጢሩ ቁልፍ፣ የነገሩ ጅራት ሆነለት፡፡ ዋናውንም ይጀምር ዘንድ በስመ ገናናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪም ላይነር አውሮፕላን ከዋሽንግተን ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞውን ተያያዘው፡፡

አዲስ አበባ እንደደረሰም የሲሳይ የሞባይል ስልክ ጮኸ፡፡ የደወለው ሰውም ከናዳ ማርያም አበ ምኔት ከአባ መርሃ ጽድቅ የተላከ ሰው ነበር፡፡ ሲሳይም አንዳንድ ሠላምታ ካቀረበ በኋላ ዋናው መልዕክት ምን እንደሆነ ጠየቀ፡፡ መልዕክተኛውም ድምጹን ያዝ ለቀቅ በማድረግ እየተቅለሰለሰ ‹‹… ኧኧኧ… አባ እንዳሉህ ታመሃል፣ ታመሃል እኛ የገዳም አባቶችህ ደግሞ መድኃኒቱ አለን እናም ሳይበረታብህ ሳትውል ሳታድር ብቅ በል ብለውሃል›› አለው፡፡ በዚህም ሲሳይ መወዛገብና መቅበዝበዝ ጀመረ፡፡ ምን እየሆነ እንዳለም አልገባውም፡፡

እንግዲህ ሲሳይ ወደ ተጠራበት ወደ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል ማቅናቱን ቀጠለ፡፡ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን አንግቦ አንዳች ምላሽ በመሻት ወደ ዳንግላ ከነፈ፡፡ ዋነኛ መዳረሻውም አስቀድሞ እንደተገለጸው ከዳንግላ ከተማ በምስራቅ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ፣ በምዕራብ ጎጃም በሜጫ ወረዳ የምትገኘው ጥንታዊቷ ፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም ናት፡፡ በሥፍራው ሲደርስ ግን ከአባ መርሃ ጽደቅ ያገኘው የጠበቀውን ምላሽ ሳይሆን የባሰ የተወሳሰበውም የምስጢር ቋጠሮ ነው፡፡ ‹‹ምን ተይዞ ጉዞ›› ሆነበት፡፡ ሲሳይም በድካሙ ብስጭት ብሎ ወደ መጣበት በመመለስ ላይ ሳለ ለአፍታ መኪናውን አቁሞ አካባቢውን በመቃኘት ላይ ሳለ ሁለት ሴት መነኮሳትን አየ፡፡ አንዳቸው በዕድሜ ገፋ ያሉ ናቸው፡፡ ሰላምታ ሲሰጡት አጸፋውን መለሰላቸው፡፡ እኚህ ሰላምታ የሰጡት መነኩሲት የቆላዋ እማሆይ የሚባሉ ሲሆን፤ በታሪኩ መጨረሻ አካባቢ ላይ በድጋሚ ይከሰታሉ፡፡ ለአሁን ግን ጣራው ክፍት ሆኖ ውሃ ወደማያስገባው ወደ ደብረ አሮን ይሄድ ዘንድ ሰበብ ከሆኑት በኋላ እርሳቸውም ገለል ይላሉ፡፡ መከረኛው ሲሳይ ግን ይበልጡኑ ስለ ቆለኛዋ እማሆይ እና ስለ ነገሮች ግጥምጥሞሽ በግርምት ይናጥ ጀመር፡፡ እናም ጉዞውን ወደ ደብረ አሮን ገዳም አደረገ፡፡

አሁን ነው እንግዲህ ለሲሳይ መሪው ኮኮብ ብልጭ የሚልለት፡፡ በደብረ አሮን ገዳም ውስጥ የሶሪያዊው አባ እድሪል አጽም ባለበት ሳጥን ላይ ሲቀመጥና ሲነሳ የገዳሙ አበምኔትም ስለ አባ እድሪል ሲገልጹለት ‹‹በወጣትነቱ በክርስቶስ ፍቅር ተነድፎ ከሶሪያ ምድር ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ከዚያም የሲና በረሃን አቋርጦ፣ አባይን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ተጓዘ… በመጨረሻም ያሰበው ተሳክቶለት እግዚአብሔርን አመስግኖ አረፈ›› ብለው ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ሲሳይ ‹‹ምን ነበር የሚፈልገው?›› ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እርሳቸውም ‹‹ቅዱሱን ቅርስ ነዋ! ልጄ›› ብለው ይመልሱ ለታል፡፡ ሲሳይም እንደገና በጉጉት ‹‹የምን ቅርስ? የትኛውን ቅዱስ ቅርስ?›› ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ጥያቄ እንጂ መልስ የለም፡፡ ጠያቂ እንጂ መላሽ የለም፡፡ እናም ሲሳይ በራሱ መንገድ ምላሽ ማፈላለጉን ተያያዘው፡፡ የአባ እድሪል አጽም ያለበትን ሳጥንም ደጋግሞ ሲያማትረው ከአራቱ ማዕዘናት በአንዱ ላይ በትንሽ የብረት ሰሌዳ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ አገኘ፡፡ አቧራውን በነጠላው ጫፍ ጠረግ አድርጎ ሲያየው በግዕዝ ፊደላት ቁልጭ ብሎ የተጻፈ አጭር መልዕክት አገኘ፡፡ በዚህም አንዳች መፃኢ ውጣ ውረድ የተጠናወተው የእፎይታ ስሜት ተሠማው፡፡ ከአቡነ አሮን ገዳም ከአባ እድሪል አጽም ሳጥን ላይ ያገኘው ጽሁፍም ይህ ነበር፡-

‹‹ለካስዋ ባኮሳ››

‹‹ ውስተ ከርሰ እመ እጓል ሐቃላዊት ይሄሉ››

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቃላት የጥንታዊ ሶሪያ ቃላት ሲሆኑ፤ ትርጓሜያቸው ቅዱስ ጽዋ የሚል ነበር፡፡ የቀጣዮቹ ቃላት ደግሞ የግዕዝ ቃላት ሲሆኑ፤ ትርጓሜያቸውም ‹‹ በቆላኛዋ የልጅ እናት ሆድ ውስጥ ይገኛል›› ማለት ነው፡፡

እንግዲህ በትርጓሜው መሰረት አባ እድሪል ይፈልግ የነበረው ቅዱሱን ጽዋ ማለትም ክርስቶስ ስለ ብዙዎች የሚፈሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ጽዋ ነው፡፡ ሲሳይም የአባ እድሪልን ፈለግ በተከተለ መንገድ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ፍለጋውም ‹‹ቆላማዋ የልጅ እናት ሆድ ውስጥ›› ተብሎ የተገለጸው ነው፡፡ ጽዋውም በዚያ ይገኛል ማለት ነው፡፡ የሆነው ሁሉ ለሲሳይ ጉም እንደመዝገን ያለ የማይጨበጥ ምስጢር ነበር፡፡

መጽሐፉ እንደሚተርክልን ከዕለታት አንድ ቀን ሲሳይ ቤቱ ጋደም ብሎ ቴሌቪዥን በማየት ላይ ሳለ አንድ ዜና በድንገት አስደነገጠውና ትኩረቱን ሳበው፡፡ ይህ ሰው ሲሳይ ባይሆን ኖሮ ዜናው ያን ያህልም ስሜት የሚሰጥ አይደለም፡፡ ዜናው ሲቀጥል፡- ‹‹ በሰሜን ሸዋ ዞን በመንዝ ላሎ ማማ ምድር ወረዳ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ምርታቸው እንደጨመረ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ ›› የሚል ነበር፡፡ አሁን ሲሳይ ልቡ ኮበለለበት በሃሳቡም ወደ መንዝ ላሎ ማማ ምድር ነጎደ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ ወደ ጀመረበት መንዝ ላሎ ማማ ምድር፡፡ ደግሞም በልቡ የጀመረውን ጉዞ በአካልም ተጓዘበት፡፡ ጉዞ ወደ መንዝ የቆላማዋን የልጅ እናት ሆድ ይልቁንም የቅዱሱን ጽዋ አድራሻ ለማየት፡፡

በመጨረሻም የሲሳይ ጉዞ ወደ አባ እድሪል ቆለኛዋ የልጅ እናት፤ ወደ እመጓ እጓል ሐቃላዊት- እመጓ ቆላ- የቆለኛዋ የልጅ እናት ሆነ፡፡ እመጓ ቆላም ደረሰ፡፡ እማሆይ እሴተ ማርያም የተባሉ ቆለኛዋ እማሆይን አግኝቶ ቅዱሱን ጽዋ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ዳገቱን ሁሉ ወጥቶ ተራራው ጫፍ አፋፍ ላይ ደረሰ፡፡ አስቀድሞ ታመሃል እንደተባለ አሁን ደግሞ ተፈወስክ ወደ ልብህም ተመለስ ለመባል ብዙ ደከመ፡፡ ከአባ አክሊሉ ጋርም ብዙ ጊዜ አብሮ በመቆየት ቅዱሱን ጽዋ ለማግኘት ስለሚጠበቅበት ቅድመ ሁኔታዎች በምስጢር ነጋገረ፡፡ ነገር ግን ሲሳይ በችኩልነቱ ቅዱሱ ጽዋ ያለበትን ዋሻ በራሱ መንገድ ገባ፡፡ የቅዱሱ ጽዋ ኃይልም በዕርሱ ላይ ተገለጠ፡፡ አንዳች ጉዳት አደረሰበት፡፡ አባ አክሊሉም ስለሆነው ነገር በሙሉ ‹‹ አሁን ከህመምህ ተፈወስክ ወደ ልብህም ተመለስክ ልቡና ከገዛህና ማስተዋልን ገንዘብ ካደረግክ በጥድፊያ በወረት ከመናጥ ራስህን ካቀብክ ቅዱሱን ቅርስ ማየት ትችል ይሆናል አሉ፡፡

እንግዲህ ምን እላለሁ በስንት ልፋት የተጻፈ መጽሐፍ ስለ ምን እየቆረጥኩ እቀጥላለሁ፡፡ የማልጨርሰውን ጀመርኩ፡፡ ሲሳይ ግን ዳገቱን ሁሉ ወጥቶ ተራራው ጫፍ አፋፍ ላይ ደርሶ አስቀድሞ ታመሃል እንደተባለ ሁሉ አሁን ደግሞ የልቡ መሻት ደርሶ ‹‹አሁን ከህመምህ ተፈወስክ፤ ወደ ልብህም ተመለስክ›› ለመባል በቃ፡፡ እኔም በዚሁ አበቃሁ፡፡ ማስተዋልን የሚሻ ልብ ያለው መጽሐፉን ያነበው ዘንድ እመክራለሁ፡፡

‹‹ለካስዋ ባኮሳ››

‹‹ውስተ ከርሰ እመ እጓል ሐቃላዊት ይሄሉ››

 

አዲሱ ገረመው

Share.

About Author

Leave A Reply