ምን ሰወራት? [ክፍል ሁለት] (የትነበርክ ታደለ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

….ሳሎን ገብቼ ቁጭ ብያለሁ!… ሰዎቹ የማያስታውቁ ባለ ጠጎች ናቸው!… ያውም የድሮ ሀብታሞች!…(( አዲስና ነባር ሀብታም በጣም ይለያያል!…)

ማዘር ቡና እያፈሉ ነው…እኔ ክፍሉን በአድናቆት አማትራለሁ!…

እዚህ ቤት ውስጥ ያሉትን እቃዎች አንድ በአንድ የሚያይ ሰው ማስታወሻ መያዝ አለበት…የተለያዩ ሀገር እቃዎች ..የቱርክ ምንጣፍ የድሮ፣ የጃንሆይ ዙፋን የመሳሰሉ ሶፋዎች፣ የክፍሎቹ በሮች ደግሞ የቤተመንግስት ግምብ የመሳሰሉ ጥርብ የቀረሮ ጣውላ ስሪቶች፣ አንጸባራቂ መብራቶች፣ ልዩ የፎቶ ፍሬሞች…. ሁሉም ነገር በስር አት የተደረደረ ብራንድ ኒው እንደምትሉት አይነት ነው።…. ቤቱ በራሱ የቤተ መንግሥት ድባብ አለው።

..ማዘር ቡናውን አቅርበው፣ እየጠጣን ወሬ ጀመርን።….”ምን እባክህ የልብ የሚያደርስ የቤት ሰራተኛ ጠፋኮ!..ሴቶቹ ሁሉ ውጭ ሀገር ካልሆነ እዚህ ሀገር ሰው ቤት መቀጠር አይወዱምኮ!..” የወሬ መጀመርያ ወሬ መሆኑ ገብቶኝ..”ህምም” አልኩ እጄን እያሻሸሁ!..

“ይሄውልህ…” ዋናውን ወሬ ጀመሩት!..

“ምን የመሰለች ልጄን በክፉ አይን አዩብኝ!”…. በእምባ ጀመሩት!..ደነገጥኩ!… ወይኔ ጉዴ? ምን አቅብጦኝ ነው በሰው ታሪክ ውስጥ ዘው ብዬ ገብቼ አላቃሽ የሆንኩት? ምነው አፌን በቆረጠው?

አንዴ እያለቀሱ..አንዴም እያቆሙ..የልጃቸው የማርታን ታሪክ ይተርኩ ገቡ!!…

….የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራት ኪሎ ተማሪ ነበረች።…. በጣም ጎበዝ ተማሪ!…. ለቤቱ ብቸኛ ሴት ልጅ ከመሆኗም በተጨማሪ የቤተሰብ ትኩረት ታክሎበት ለከፍተኛ ትምህርት ደረሰች። ግን ምን ያደርጋል! …..

….ማርታ ገና የመጀመርያ አመት ተማሪ እንዳለች ከአንድ የክፍል ጓደኛዋ ጋር በፍቅር ወደቀች!..ከነፈች!…. ትምህርት የታባቱ!…ስንት አመት ተማረች!…አሁን ጊዜው ከቤተሰብ መሀል ወጥታ የነጻነት አየር የምትተነፍስበት ወቅት ነው!…..እናስ? እናማ በመውጫ በመግብያው ሁሉ ተዛዝለው እስከ መሄድ ደረሱ!…..አበዱ!

ማፍቀር ምን ክፋት አለው? ምንም!….ክፋቱ ግን ያፈቀሩትን ሰው ማንነት አስቀድሞ አለማወቅ ነው!…ማርታ ይህንን ሳተች!…ፍቅረኛዬ ያለችው ሰው የሱሶች ሁሉ መናሀርያ ነበር!….የሱስ ገደል ውስጥ ገብቶ ለመውጣትም ምንም ሀሳብ የሌለው!….. ደልቶታል!…

….ማርታ ሳታስበው ተከተለችው!….ከክላስ ይልቅ መገኛቸው ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ሆነ!….በየትኛውም አጋጣሚ የሚያገኙትን ገንዘብ ጫት እያመነዠጉ ሲጋራ እየማጉ ሺሻ ያንዶቆድቁበታል!……

..ቀን ይመጣል..ቀን ይሄዳል!…ሁሉም የዘራውን ያጭዳል!….. አመቱ ሲያልቅ ማርታም ፍቅረኛዋም ዳግም ወደ ዩኒቨርስቲው እንደማይመለሱ አወቁት! ተባረሩ! (ፍቅረናዋ ግን ከዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ከህይወትም ጎደለ! ሞተ!)

….ማርታ በአንድ አመት ውስጥ ህይወት ተዘበራረቀችባት!….ተስፋ የተጣለባት ጭምት ልጅ ተስፋ ቢስ ሆና አረፈችው!…..ያዳቆነ ሰይጣን እንዲሉ የጀመረችውን ሱሷን አጠንክራ ቀጠለች!….

..አባቷ እሪሪ አሉ!…ያለሳቸው ፈቃድ በፍጹም ከቤት እንዳትወጣ አደረጉ!….በተቃራኒው እናቷ የምትፈልገውን ነገር እቤት ድረስ በድብቅ እያመጡ ይሰጧት ነበር!….ቀጠለ!

(((ተከራዮች መቼም በአከራዮቻችን አጓጉል የገንዘብ ጭማሪና ንዝንዝ ብንማረርም ቅሉ አንድ ጥሩ እድል ደግሞ አለን!…ገመናቸውን ብልት አድርገን እንወጣለን!…ሰዎች እንዴት እንደሚኖሩ እንማርባቸዋለን!….)

………ማርታን ከአምስት አመት በኋላ ካዝንችስ ለታክሲ ስንጋፋ አገኘኋት!……..ቀድማ ገብታ ቦታ ያዘችልኝ! አላመንኩም! ግዙፍ ሴት ሆናለች!….ያን የመሰለ ቅሽር ቁመና እንዲህ ሆነ?! ዝብርቅርቅ ያለ ስጋ!

“አውቀሀኛል አይደል?”

“ማርታ?” አልኳት በጥያቄ አይን!…. “አዎ አልረሳሀኝም! ያኔ ከእናቴ ጋር ጫት ቤት ለጫት ቤት እየዞራችሁ ስትፈልጉኝ እንደነበር አውቃለሁ! ..ሀሀሀ (ትስቃለች!) ቅዥቅዥ ትላለች። …ያ ኩራቷ ናፈቀኝ!…ያ መንቀባረር ያምርባት ነበር ለካ!…

… ግን ምንም ማድረግ አልቻልኩም!….. ቤተሰቤን መተው ነበረብኝ! ከሱስ መላቀቅ አልቻልኩም!..ሀሀሀ..” ቶሎ ቶሎ ታወራለች!

ኡራኤል ጋ መውረድ ነበረብኝ! ግን ጉዞዪን ቀጠልኩ!…… ሀያ ሁለት ዘሪሁን ህንጻ ጋ ስንደርስ አብረን ወረድን!……ወሬዋን አልጨረሰችም!… እኔም ላወራት ፈልግያለሁ!”እንዴት ሆና ይሆን?” እያሰብኩ ነው።

“ለመሆኑ ከቤተሰብ ጋር ትገናኝያለሽ?!”

“ወይ ቤተሰብ!..ምንም አልሰማህም ማለት ነው?…..በል እንካ ቁጥሬን ያዝና ተገናኝተን እንጫወታለን!…መቼም እስካሁን ሺሻ ማጨስ አልጀመርኩም እንደማትለኝ እርግጠኛ ነኝ!…..ሀሀሀ…ምን የመሰለ ባለ አራት ክፍል ስታንዳርዱን የጠበቀ ሺሻ ቤት ከፍቻለሁ መሰለህ!…እውነቴን ነው ምልህ ምድረ አርቲስት በለው፣ ባለስልጣን፣ ወላ ሀብታም…የከተማው ምርጥ ሰዎች እኔ ቤት አሉልህ!…..ልንገርህ? ባሁን ጊዜ ሺሻ ካላጨስክ ማንንም በቀላሉ አታገኝም!…ሁሉም እኔጋ ናቸውኮ!….ሀሀሀ… ስምህ ማን ነበር?”…ቁጥሬን ስልኳ ላይ ጻፈችው

“እደውልልሀለሁ!! ዋ! እንዳጠፋ!! ሀሀሀ..”

ይቀጥላል?

Share.

About Author

Leave A Reply