ምን ሰወራት?! (የትነበርክ ታደለ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

….ምንም ቆንጆ ብትሆን የሚኮሰኩስ ጸባይ ያላት ሴት በጣም ነው የምታስጠላኝ! የምትኮሰኩሰኝ ሴት ደግሞ በሰፈሩ ያለኔ ቆንጆ የለም የምትል አይነት…ይህንንም በአካሄዷም፣ በአነጋገሯም በቃ በሁሉ ነገሯ እኔን ብቻ እዩኝ! እናንተ አስቀያሚዎች!” የሚል መልእክት በሁኔታዋ ሁሉ ለማስተላለፍ ትሞክራለች። እና ደስ አትልም!

….ክፉ እድል ሆነና እንዲህ አይነት ልጅ ያለችበት ግቢ ውስጥ ቤት ተከራየሁ።…..አቤት እዳዬ?! እስኪ አሁን በኔ ላይ ምን እንዲህ ያደርጋታል? እኔ ራሴ የቤት ኪራይ ሳልከፍል አንድ ቀን ባሳልፍ አባቷ ጆሮዬን ይዘው ከደጅ የሚጥሉኝ ምስኪን ነኝ!….እንኳን እሷን ቀርቶ ውሻቸውንም “ተው ቤቢ?” እያልኩ እየተለማመጥኩ ነው የምኖረው።….

…እሷ እናቴ!…. በፊት በር ስገባ …በጓሮ በር እሷ ስትመጣ በቃ ግልምጥምጥ ታደርገኛለች!..ኩራቷ ንቀት ይመስላል!. “ይቺን ልጅ ምን አስቀይምያት ይሆን?” በቃ ከማክበር አልፌ እፈራት ጀምርያለሁ….

…እርግጥ ነው ልጅቷ በጣም ቆንጆ ናት (ታምራለች)፣ በተለይ የምትቀያይራቸው ልብሶች አብዛኞቹን በሌላ ሴት ላይ አይቼ አላውቅም…ትዘንጣለች!…. እኔ ግን ከዚህ ነገር ሁሉ ምንም ጉዳይ አልነበረኝም! (እውነቴን ነው! ጊዜዬ ገና ነበር!)… “ታድያ ለምን ታፈጥብኛለች?” ራሴን እጠይቃለሁ!….

….አንድ ቅዳሜ ረፋድ ላይ ሻወሬን ወሳስጄ ልብሴን ቀያይሬ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እየተዘገጃጀሁ ነው። (እማር ነበር…እየሰራሁ ደግሞ እማራለሁ….ይሄን ሁሉ እዳ ተሸክሜ የሰው ኮረዳ የማይበት ሀሳቡም ወኔውም አልነበረኝም!)…..የቤቴ በር ተንኳኳ……

…አንዲት ጥንጥዬ ክፍል በሯ ገርበብ ብሎ ከተከፈተ ውስጧ ያለው ኮተት ሁሉ ይታያል። በሩን ገፋ አድርጋ ገባች!….

“ይቅርታ! ማን ነበር ስምህ?” አለች ቁንጥርጥር ብላ! ይቺን ይወዳል የሰውዬው ልጅ!…. ይህን ሁሉ ጊዜ እዚህ ቤት ስኖር ስሜን ሳታውቅ ነው እንዴ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ጠጉሬ ስትገላምጠኝ የከረምኩት?

“የትነበርክ” ነገርኳት!

“ለዛሬ ክፍልህን ታውሰኛለህ?”

“ለምን?”

“ፈልጌው ነው!” የኔ ክፍል ለሷ ምን ሊያደርግላት እንደሚችል አላውቅም! ቤቴን አይታ ልትታዘበኝ ይሆናል እንጂ መቼም እዚህ ክፍል ውስጥ አትውልም! ሚጢጢ ቴሌቪዥን እና ሚጢጢ የመሬት ላይ ፍራሽ!…ቁልፉን ሰጥቻት ወደ ክላሴ ሄድኩ!

……. አሄሄ….ያን ቅዳሜ ክላሱ ክላስ አልሆነልኝም….ቀልቤ ሁሉ የለም! ይቺ ልጅ በዝያች ክፍል ውስጥ ምን እያደረገች ይሆን? እያልኩ በሀሳቤ ሀሳብ እየሳልኩ…..አለቀ!….

የዝያን ቀን አንበሳ አውቶብስ መጠበቅ ቆሞ ለመጠበቅ ትዕግስቱ ፈጽሞ አልነበረኝም!…በጣም ቸኩያለሁ!….ክፍሌ ምን መስላ ይሆን?…እንዴት ውላ ይሆን?…….. ታክሲ ይዤ ደረስኩ!……

….በሬ እንደተዘጋ ነው…አንኳኳሁ….ዝም….ደግሜ አንኳኳሁ… ቀስ ብላ መስኮቱን ከፈት አድርጋ አየችኝና በሩን ከፈተችው…. ገባሁ!

የመድሀኒያለም ያለህ!….

….ክፍሏ በጭስ ታፍና ደመና የውቀደቀባት መስላለች!…ልጅቷን እንኳ በቅጡ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው!… “ቶሎ ግባ!” በሩን ከውስጥ ዘጋችው!…መብራቱን አበራሁት!….

“በጣም ይቅርታ! አሁን እጨርሳለሁ!”…… ዶቅዶቅዶቅዶቅ!!ቡልቅ!…ዶቅዶቅዶቅ!!!…ቡልቅ!….. ሺሻ የሚባለውን የጭስ ጠርሙስ በህይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ አየሁት!….. ድምጹ እንዴት ይቀፋል! ህጻን ልጅ ካካ ሲያደርግ ወይም አሜባ የያዘው ሰው ሽንት ቤት ሲቀመጥ የሚያሰማው ድምጽ! ዶቅዶቅዶቅዶቅ!!!

ልጅቷ አይኗ ፍጥጥ ብሏል….. በሩን ከፍቼ ልወጣ ስል “ኖኖ…በቃ ጨርሻለሁ” ተነሳች! ድሪያዋን አወለቀች! ልብሷን ቀያየረች!….

“እስከ ዛሬ አካባጅ ትመስለኝ ነበር! አመሰግናለሁ!” ድምጿ ስልል ብሏል!

“ይህቺን ክፍል ድሮ ተደብቄ አጨስባት ነበር!…በኋላ ፋዘር ነቃብኝና በንዴት አከራያት!….በየቀኑ ሺሻ ቤት መመላለስ አይደብርም? በዚህ ላይ ውድ ነው እዝያ!…የሰው ብዛትስ ብታይ! በተለይ የካልሲው ግማት!… እዚያኮ ከሺሻው ይልቅ የጫማ ሽታና የሰው ላብ ነው ቶሎ አናትህ ላይ የሚወጣው….እና በቃ እንግዲህ ካሁን በኋላ…..” ልታግባባኝ ሞከረች!

ለካስ አጅሪት ያን ሁሉ ጊዜ ስታሳቅቀኝ የከረመችው ለዚሁ ነው? ለካስ ሱሷ ነበር ሲገላምጠኝ የከረመው?! አቤት ሰው ከውጭና ከውስጥ እንዴት ይለያያል?! ሰው የራሱን ሽንፈት ለመከላከል ሌላውን ለማሸነፍ ይሞክራል! ያ ሁላ ኩራቷ ለካስ ሽፋን ነበር?!

“በጣም ይቅርታ አድርጊልኝ!”ኮምጨጭ አልኩ! እኔ ሺሻ አላጨስም! ሌላም ሰው እንዲያጨስ አላበረታታም! ቅድምም ለዚህ ጉዳይ እንደሆነ ብትነግሪኝ ኖሮ አልፈቅድልሽም ነበር!..እና ድጋሚ ክፍሌን አልፈቅድልሽም!” አስጠነቀቅኳት!

….. ምርቃና ላይ ናት የሰማችኝ አልመሰለኝም! ግን ውስጧ ሲሰባበር ይታወቀኛል! ንግግሬ ደረቀባት መሰለኝ ደነገጠች! …እና ኮተቷን በጨርቅ አሳስራ ወጣች!..ሄደች።..ቤቴ ውስጥ ያለው ጭስ ግን ሶስት ቀን ፈጀበት!..

….ከዝያን ቀን ወዲህ ልጅቱ አይኔን ሸሸች!……እኔ ቤት ውስጥ ካለሁ በጓሮ በኩል ድርሽ አትልም (ክፍሌ በስተ ጓሮ ነው!)…..ይባስ ብሎ ሳላያት ቀናት አለፉ!…. ጨነቀኝ!..አስቀየምኳት እንዴ?….ምን ላድርግ!? …..

“ማዘር ደህና አደሩ?!”

“እንደምን አደርክ?”

“ምነው ሰሞኑን ማርታን አላየኋትም?!”….. እናቷን ፈራ ተባ እያልኩ ጠየኳቸው!…… እጄን ይዘው ወደ ሳሎን ገቡ!…

ይቀጥላል?

Share.

About Author

Leave A Reply