ምዕራባዊያንን እኩል አሸነፉ፣ ምኒሊክ በሰይፉ ማንዴላ በአፉ! (መጋቤ ሀዲስ እሸቱ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

” ከጥንት መሪዎቻችን ትተን ቴዎድሮስ፣ ዮሃንስ፣ ምኒሊክ፣ ኃይለሥላሴ፣መንግስቱ፣ መለስ፣ እና ኃይለማርያምን ብንወስድ መልዕአክም—ሰይጣንም አይደሉም! እነዚህ ሁሉ ሰዎች ናቸው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው ሰይጣን እንደምታውቁት ለምስጋና አይመችም፣ እንዲሁም መልዕአክቶችም ለትችት አይመቹም። ሰው ከሆነ ግን ለትችትም ለምስጋናም ይመቻል። ኔልሰን ማንዴላ በሞቱበት ሰሞን አንድ የግዕዝ ቅኔ አቅርቤ ነበር። ይሄ ግጥም ምኒሊክና ማንዴላን አነፃፅሬ ያቀረብኩት ግጥም ነበር። እስኪ በአማርኛ መለስ አርጌ ልንገራችሁ።

ምዕራባዊያንን እኩል አሸነፉ፣ ምኒሊክ በሰይፉ ወ ማንዴላ በአፉ!

ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣ ምኒሊክና ማንዴላ ሁለቱም ጀግኖች ናቸው። ልዩነቱ ማንዴላ ያሸነፈው በትህትና፣ ደም ሳያፈስ፣ በለስላሳ ዲፕሎማሲ ይቅር በሉን፣ ይቅር ብለናችኋል ብሎ ነው። አሁን ዜና ስንሰማ ደቡብ አፍሪካ ነፃ ከወጣች 23 አመት ሞላት ይባላል፣ ነገር ግን ብዙሃኑ ደቡብ አፍሪካዊያን “እውነት አሁንም ነፃ ወጥተናል ወይ?” እያሉ ይጠይቃሉ። በወቅቱ ሀገሪቱ ነፃ ስትወጣ የነበረው ድርድር ነጮቹ የያዙትን ሀብትና ርዕስት ይዘው እንዲቀጥሉ፣ ጥቁሮቹ ደግሞ ባሪያ የሚለው ስያሜ ከላያቸው እንዲነሳላቸው ነበር፣ ግን የማይካደው እውነታ በተዘዋዋሪ ያው ባሮች ናቸው። በእኛ ሀገር ባለሃብቶቻችንን ብትወስዱ በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ተክከብርሃን አምባዬ የሚባሉ ባለሃብት አውቃለው፣ ሳሙሄል ታፈሰ የሚባሉ ባለሀብትም አውቃለው፣ ፀጋዬ የሚባሉም ኽንዲሁ ሁሉም ባለሃብቶች የሀገሬ ልጆች ናቸው! እንዴት ደስ ይላል?

ደቡብ አፍሪካ ብትሄዱ ግን እያንዳንዱ ሪልስቴት፣ እያንዳንዱ ባንክ፣ እያንዳንዱ ኢንሹራንስ በእነ ፒተር እና በእነ ጆንሰን የተያዙ ናቸው። ጥቁሩ ምናልባት ባንክ ቤት ገንዘብ ያስቀምጥ ይሆናል እንጂ ባንክ ቤት የለውም። በግልባጩ እውነቱን ለመናገር ይሄ የአድዋ ድል ውጤት ነው። አንድ ሰው ኽንዳውም ስልክ ደውሎ በዚያ ሰሞን “እንዴት ምኒሊክና ማንዴላን ታነፃፅራለህ? ለእኔ ምኒሊክ ይገዝፉብኛል!” አለኝ። አሁን እንግሊዛዊያን ለንደን ከተማ ላይ ለማንዴላ ሃውልት እንዲቆምለት እየተደራደሩ ነው አሉ። አሁን እውነት ጥቁሩን አክብረውት ነው ወይ ይሄን የሚያደርጉት? አይደለም!!ነጮቹ ሃብትና ንብረታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ለዚያ የሚከፈል ዋጋ ነው። ሌላ ምንም ተዓምር የለውም።

አፄ ምኒሊክና የያኔው የኢትዮጵያ ጀግኖች ግን አዋርደውና ማቅ አልብሰው በቅሌት ስለላኳቸው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትኖር በፍፁም የሚፈልጉ አይመስለኝም። በእርግጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁሉም ነገር መግባባት የለብንም፣ በተቃራኒው በወረደ አስተሳሰብና በቋንቋ መጠላለፍም የለብንም። መንግስት ክልል ሲያቋቁም ለአስተዳደር ይመቸው ዘንድ እንጂ ለአስተሳሰብ ክልል አልታጠረለትም። በሌላ በኩል ለአክሱም የሰጠነውን ክብር በአክሱም ለሚኖሩት ለእነ ጎይቶም፣ ለእነ ትርኃስ እንዲሁም በአድዋ ድል የተመካነውን ያህል በአድዋ የሚኖሩትን እነሃዳስ፣ አስገዶምና አብረኽትን እናውቃቸዋለን ወይ!? የወንዶ ገነትን ፓፓዬ እና ማንጎ እየበሉ የወንዶ ገነትን ገበሬ ንቆ የት ሊገባ ነው? የጎጃምን ቅቤ እና ማር እያጣጣሙ ጎጃምን “ቆምጬ” ማለቱ ያዋጣል ወይ? የወለጋን ወርቅ እየቋመጥን እነቶሎሳን መናቅ የት ያደርሳል። መግባባት ያስፈልጋል።

የአሁኑ ጦርነት የአስተሳሰብና የአመለካከት ጦርነት ነው። አሉላ አባነጋን ለማድነቅ ግዴታ ትግሪኛ ማውራት አይጠበቅብኝም! በላይ ዘለቀን ለማድነቅ አልበልጠውም ማለት የለብኝም፣ ንጉስ ሚካሔልን ለማድነቅ ደሴ መወለድ የለብኝም።

ይሄንን አስፍተን ልናየው ይገባናል። አድዋ የእኛ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ የቀየረ መመኪያ ድል ነው። የኢትዮጵያዊያን እና የአፍሪካ ኩራት ነው። ስለአድዋ ስናወራ የተወሰነ ክልል ታሪክ እየመሰላቸው፣ አሜሪካ ገብተው አሜሪካ ያልገባቻቸው ብዙ ሰዎች ገጥመውኛል። ይሄ የአስተሳሰብ ዝቅጠት በቃህ ሊባል ይገባል፣ እኔ እንዳውም የሐረር ባለሃብት አድዋን እንዲያለማ እፈልጋለሁ! አድዋ ውስጥ ቶሎሳ ሆቴል ታንፆ ማየት እሻለው።

ይሄን መጥፎና የመከፋፈል አስተሳሰብ ካላፀዳነውና ካላከምነው የዛሬ 120 አመት የምንተርክለት አድዋ አየር ላይ ተንሳፎ ይቀራል። ጀግኖቹ ግንባራቸውን ለጥይት አቀብለዋል ደምተዋል! ሞተዋል! ግን መሬት እና ነፃነት ሳያስነጥቁ ለእኛ አውርሰውን አልፈዋል! አድዋ የእኛነታችን እና የአንድነታችን መተሳሰሪያ የብረት ገመድ ነው። ስለአድዋ ሼኹ በመስኪድ፣ ፓስተሩ በፀሎት ቤት፣ እኔም በቤተክርስቲያን ልንሰብክ ይገባል። እኔ በቀደም መስጊድ ሄጄ አስተምሬያለው፣ የሞተው መሓመድ ይሁን እንጂ የሞተው ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ነው። ወገኔ ነው! አካሌ ነው!!

“ኢትዮጵያዊነት” በመስኪድ ከቁርዓን ቀጥሎ፣ በቤተክርስቲያን ከመፅሓፍ ቅዱስ ቀጥሎ፣ በሰርግ ቤት ከሙሽራው፣ በለቅሶ ቤት ከአስክሬኑ ቀጥሎ ሊሰበክ ይገባል። እንኳን ጤነኛ ሆኖ ለመኖር ይቅርና፣ እብድ ሆኖ ለመኖር ኢትዮጵያ ታስፈልገናለች። ተመልከቱ እስኪ ሰዎች አዕምሯቸው ተነካ ተብሎ ከአሜሪካ ይባረራሉ! ግን እቅፏን ከፍታ የምትቀበላቸው ኢትዮጵያ ናት። አብዶ ጨርቅ ለመጣልም ሀገር ያስፈልጋል፣ ለምኖ ለማደርም ሀገር ያስፈልጋል። ሀገራችንን ለመጠበቅና ለመደገፍ ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት የለብንም።”

Share.

About Author

Leave A Reply