ሠዎች ዛሬ በሻሸመኔ የዱር አራዊት ሆነዋል! (ሐይሉ አባይ ተገኝ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የዛሬው የሻሸመኔ ሠውን የመስቀል አረመኔያዊ ተግባር “የጎሣ ፌደራሊዝም” ውጤት፣ ችሮታና ሠዎች ሠዎችን ለመብላት ጅብ የሆኑበት ክስተት ነው፡፡ የሠው ልጅ ሠውን ሲሰቅልና ሲገድል አየን። አይሁዶች እንኳን ከርስቶስን ዘቅዝቀው አልሰቀሉትም።

በጎች ለረጅም ጊዜ በተኩላ ላለመበላት ሲዳክሩ ቢቆዩም መጨረሻ ላይ በእረኛቸው ይበላሉ:: እረኛቸውም “የጎሣ ፌደራሊዝም” ነውና!!!

“የጎሣ ፌደራሊዝም” ወይም ጎሠኝነት ተፈጥሮአዊ (innate) ሣይሆን በማህበረሰቡ የሚገነባ (social constructs)ነው:: የጎሣ ማንነትና ጎሠኝነት “በጎሣ ፌደራሊዝም” የፓለቲካ ስርዐት ውስጥ የሚያድግና የሚጠነክር ነው::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” የሰው ልጅን የሞራል ስብዕና ግላዊ የማገናዘብ ችሎታ ማህበሪዊ ንብረት አድርጎ ይወስዳል::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” ህዝብን ከህዝብ ማባላት ብቻ ሣይሆን እራሱ ህዝብን ይበላል:: መብትና ነፃነቱ “በጎሣ ፌደራሊዝም” ይጠበቃል ብሎ የሚያምን የዋህ ከገዳዩ ጋር ብርድልብስ ይጋፈፋል::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” በጅምላ ማሰብ፣ መፈረጅ፣ መፍረድና መቅጣት አይነተኛ ባህርይ ያደርጋል:: የወል ወይም የጋራ አመለካከትና ሃሣብን ስለሚደግፍ ህሊናና ሃሣብን የማህበር እስረኛ ያደርጋል::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” አንዴ ከተዋቀረ ፓለቲካን በድጋሜ በጎሣ መስመር ከተረጎመ በሁዋላ ሁሉንም ነገር አከራካሪ የጎሣ ጉዳይ ያደርገዋል::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” የጭካኔና የፀረ-ሠውነት (anti human) መለያ የሆነ እንሠሣነት ነው:: የጎሣ ፌደራሊዝም” እንሠሣዊ ነው የምንለው የሰው ልጅን ማሰቢያውን ደፍኖ ለሁከትና ብጥብጥ ስለሚያዘጋጅ ነው:: “የጎሣ ፌደራሊዝም” ሠዎችን ከህሊናቸው ይልቅ እንደ እንሠሣ በደመ ነፍስ እንዲያስቡና ህይወታቸውን እንዲመሩ ስለሚያደርግ ነው::

“የጎሣ ፌደራሊዝም” ሠው የሠው ልጅ ወገኑን የሚበላበት (human cannibalism) ሥርዐት ነው::

“በጎሣ ፌደራሊዝም” ሙጥኝ ብለን የምንቀጥል ከሆነ እንደ ጎሣ ሌላውን ጎሣ ብቻ ሣይሆን እንደ ሠው ከሌላውና ከራሳችን የሠው ፍጡር ጋር እንበላላለን:: እንደ ሃገር እንፈርሣለን:: እንደ ሠው እንበተናለን:: እንደ ዱር እንሠሣ አንዳችን ሌላውን እንበላለን::

“የጎሣ ብሔረተኝነትም” ህዝብን ለማደራጀትና ለመቀስቀስ ቀላል መንገድ ተብሎ የሚታሰብ በጎሣዎች ጥምረት የሚገነባ ሃሣባዊና ሃሣብ-ወለድ አደረጃጀት ነው:: ይህ አደረጃጀት ዓላማውን ሲያሣካ መልሶ በንዑሣን ጎሣዎች ተከፍሎ ይናቆራል:: የልዩነት መስመርን እስከ ጎጥና ቀበሌ ያወርዳል:: ወደለየለት እንሠሣዊ ሥርዐት ጋር ተጣብቀን እንሠሣም ሆነናል::

“በጎሣ ፌደራሊዝም” መብትና ነፃነት የማህበር ስለሆነ የጎሣ መሪዎቹ እንጂ የጎሣ አባሉ ለጎሣ ቡድኑ ባርያ ነው::

“በጎሣ ፌደራሊዝም” መብትና ነፃነት፣ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት አይታሰብም::

“በጎሣ ፌደራሊዝም” ሠዎች ሠዎችን የሚበሉበት እንሠሣዊ የፓለቲካ ሥርዐት ነው!

“በጎሣ ፌደራሊዝም” መርህ ስር የምናዳብረው “የጎሣ ብሔረተኝነት” እንሠሣዊ በመሆኑ: መጠቃትና መማጥቃት (prey & predator) የእንሠሦችን ተፈጥሮአዊ ሕግ እንደማንቀይረው “የጎሣ ፌደራሊዝምን” የመጠቃቃት ሕግ እንደዚሁ ልንቀይረው አንችልም:: ይህን ጥቃት የምንታደገው በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በሰውነታችን መኖር ስንችልና እንደ ሠው ማሰብና መተሣሰብ ስንችል ነው::

ሞት እንሠሣዊ ለሆነው “የጎሣ ፌደራሊዝም” !

 

Share.

About Author

Leave A Reply