ሰራዊቱ ህዝባዊነቱን በማጠናከሩ ለአፍሪካውያን ኩራት ሆኗል -አቶ አባዱላ ገመዳ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአገር መከላከያ ሰራዊት ህገ-መንግስታዊ መርሆውን በሚገባ በመተግበሩና ህዝባዊነቱን በማጠናከሩ ለአፍሪካውያን ኩራት ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ አቶ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።

በወታደራዊ ማዕረጋቸው ሜጀር ጀኔራል እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እንደገለጹት፤ ሰራዊቱ ህዝባዊነቱን እያስቀደመ መንቀሳቀሱ በሚሳተፍባቸው የአገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ግዳጆች የላቀ ስኬት እንዲያስመዘግብ ረድቶታል።

ተቋሙ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት መፈጸም የሚችል ህዝባዊ ሰራዊት መገንባቱን የተናገሩት አቶ አባዱላ፤ መነሻውም መድረሻውም አገርን መጠበቅና ህዝብን ማገልገል ብቻ ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ የህገ-መንግስቱ የመጨረሻ ደጀን መሆኑን “በተለያዩ ጊዜያት በፈጸማቸው ግዳጆችና ባስመዘገባቸው ውጤቶች አስመስክሯል” ያሉት አቶ አባዱላ፤ የሰራዊቱ የጥንካሬ ምንጭም መቼም የማይነጥፈው ህዝባዊ ዕምነቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በማንኛውም ጊዜ ለህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያን መስሎ የተገነባው የየትኛውንም አገር ህዝብ እንደራሱ የሚያይ ሰራዊት ማፍራት መቻሉ ህዝባችንን የሚያኮራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሰራዊቱ የተላበሳቸው ባህሪያትና ዘወትር የሚተገብራቸው እሴቶቹ የሰላም ኃይል እንዲሆን የልማት ተሳትፎ እንዲጎለብትና በየተሰማራበት ተልዕኮ ድል እንዲያስመዘግብ እንዳስቻለው ጠቁመዋል።

ሰራዊቱ ያልተነገረለት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት አቶ አባዱላ መገለጫዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ህዝቡ በተገቢው እንዲያውቃቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

እያንዳንዷ ዕለት ለሰራዊቱ የአዳዲስ አቅም መፍጠሪያ ነች ያሉት አቶ አባዱላ ሰራዊቱ ከአገሩ ባለፈ ቀጣናዊና አህጉራዊ የሰላም ኃይልነቱን ሚና በላቀ ብቃት እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ መናገራቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ለኢዜአ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ENA

Share.

About Author

Leave A Reply