ሰው ለጥያቄው መልስ የሚያገኘው ሲያምፅ ከሆነ፥ ኑ እናምፅ (ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መሣሪያ አንሥተው በኢሕአዴግ ላይ ያመፁ ቡድኖች፥ ኢሕአዴግ “ግቡ” ብሎ ጋብዟቸው አገራቸው ገብተዋል። ስለ አመፁና “አንታዘዝም” ስላሉ፥ ድምፃቸው ተሰማ፤ ጥያቄያቸው ተመለሰ። አንዳንዶቹማ ሲጋበዙ ትጥቅ እንዲፈቱ እንዳልተጠየቁ ሲናገሩ ሰምተናቸዋል። ይህ “የአፍ ወለምታ” ሊሆን ይችል እንደሆነ ነው እንጂ፥ “አሉ ባልታ” ወይም “ተረት ተረት” አይደለም። ይኸው ከመንግሥቱ የጦር ሠራዊት ጋር እየተዋጉ ነው። “ብፈልግ ኢትዮጵያን ልከፋፍላት እችላለሁ” የሚለውና ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሲያንጓጥጥ የኖረው፥ ሳንጃውን በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ሲመዝ በይፋ የታየውም ተጋብዞ፥ ኢትዮጵያ ገብቶ፥ በሸራተን ሆቴል መሽጎ ይዶልታል አሉ። እኛ ግን፥ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ጎሳዎች የተውጣጣን አንድ ሕዝብ ነን እንጂ፥ ጎሰኞች አይደለንም፤ ጎሰኞች አታድርጉን” እያልን ጉሮሯችን እስኪደርቅ ብንጮህ፥ ብዕራችን እስኪነጥፍ ብንጽፍ፥ ጆሮ ዳባ ልበስ ተባልን። ለምን?

የአለመሰማት ጉዳይ የጥንት ነው፤ “ደግን ልጅ እናቱም አትወደውም” ይባላል። ኩበት የምታስለቅመው፥ ጌሾ የምታስወቅጠው፥ መንደር ለመንደር የምትልከው፥ “እሺ እማየ” የሚለውን ልጅ ነው። ቅዱሱ መጽሐፍም መስክሯል። ከአባቱ ድርሻውን ወስዶ በወሮበላነት የኖረው ልጅ ተመልሶ ሲመጣ ለጨዋውና ለታማኙ ወንድሙ ያልተደረገለት ታላቅ ድግስ ተደረገለት። ጨዋው ልጅ፥ “መልካም ልደት” እንኳን አልተዘመረለትም። “እነሆ ይህን ያህል ዓመት እንደባሪያህ ተገዝቼልሃለሁ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍኩም። ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት እንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድክለት” ብሎ በአባቱ ላይ ቢያጕረመርም፥ የተሰጠው መልስ፥ “አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ” የሚል ነበር። እኛንም፥ “እነሱ ምንም ቢያጕረመርሙ፥ ከኢትዮጵያ አይለዩም” ተብለን የሚሰማን አላገኘንም።

እውነት ነው፤ ብዙዎቻችን እንኳን አለመሰማት ሥቃይም ቢሆን ከእናት ኢትዮጵያ አይለየንም። ግን ቀስ በቀስ በበሽታው እየተለከፍን ነው። ጥቂቶቻችን ከኢትዮጵያ ይልቅ ለነገዳችን ማሰብ ጀምረናል። “ብሔር፥ ብሔረሰብ” የሚባሉትን ቃላት ከአፋቸው አስገብተው የማያውቁ ሰዎች፥ ዛሬ የፖለቲካ ንግግራቸውን የሚጀምሩት በነዚህ ቃላት ሆኗል። በዚህ የጎሳ ፖለቲካ መግነን ምክንያት ቍጥራቸው እንዳይጨምር በሥጋት ላይ ነን።

ጩኸታችን ያልተሰማለት ብሶታችን ጎሰኝነት ነው። ያ አፄ በጉልበቱ፥ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚዋጉ ከኦነጎች ጋር ሆኖ፥ ኢትዮጵያን እየቈራረሰ ካከፋፈለን ከ1983 ዓ. ም. ጀምሮ፥ “እኛ ኢትዮጵያውያን ጎሳችን የተለያየ ቢሆንም፥ አንድ ሕዝብ ነን” እያልን ስንጮህ፥ ባለሥልጣኖቻችን ከኛ ጋራ እልህ የገቡ ይመስል፥ በአነጋገሩን ቍጥር፥ “ብሔር፥ ብሔረ ሰቦች፥ ሕዝቦች” ማለታቸውን አባብሰውታል። እኛ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነን ሳለ፥ ጆሯቸውን የሚሰጡት ለጠባቡ ሕዝብ ነው። ጎሰኝነት ሲያጋድለን እያዩ፥ ከዚያም አልፈው፥ የመንግሥት ሥልጣን ለጎሳዎች ከማከፋፈል ችግር ውስጥ ገቡ። የገቡት ከማጥ ውስጥ መሆኑ ሲታያቸው፥ ሐሳባቸውን በመለወጥ ፈንታ፥ የምናዝንላቸው ይመስል፥ ከማጡ ለመውጣት እንዴት እንደተቸገሩ ይነግሩናል። የንጹሓን ክልል እንደሌለ እየታወቀ፥ ሥርዓቱን አንዱ ሲጠላው ሌላው የሚወደው ለምን ይሆን? ሌላውን ኢትዮጵያዊ በመግደልና በማባረር ለማጽዳት ይሆን?

እንግዲህ አንሰማችሁም ካሉን፥ አምፀው እንደተሰሙት ድርጅቶች እንድንሰማ፥ ኑ እኛም እናምፅ፥ ኑ እናድም። በነዚህ ከፋፋይ መጠሪያዎች ሲጠሩን አንስማቸው፤ እንደ ደብረ ጽሙና መነኮሳት፥ ዝም፥ ጭጭ እንበል። ወደኛ ሲያዩ ፊታችንን ወደሌላ እናዙርባቸው። “አቤት ወይም እመት ያለ የኢትዮጵያ ጠላት ይሁን” ብለን እንማማል። መሣሪያችን ኵርፊያ ነው።

ውድ ጠቅላይ ሚንስትራችን በነዚህ ጆሯችንን በሚቆረቍሩ ስሞች ይጠራንና ከዚያ ቀጥሎ፥ በሚጥሙን ቃላት እንደ አንድ ሕዝብ ያነጋግረናል። ምናልባት፥ “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝቦች” የሚለን በመሐላ የተረከበው ሕገ መንግሥት እስኪሻሻል ድረስ ማክበሩ ይሆን? ምክንያቱ እውነት ይህ ከሆነ፥

(ሀ) ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበት ቀን ወይም ሁኔታ ይነገረን፤

(ለ) ጥያቄያችን አጀንዳ ውስጥ እንደሚገባም ይረጋገጥልን፤

(ሐ) (1) ኢትዮጵያን የከፋፈሏት ሁለት የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠሉ ድርጅቶች መሆናቸው፥ (2) የተረፈውን በቅርጫ ያከፋፈሉን ለራሳቸው የፈለጉትን ያህል ወስደው መሆኑ፥ (3) እነዚህ ወንጀለኞች ይህን ወንጀል የፈጸሙት በቅርችጫው ጊዜ የተበደሉ እንዳይቃወሟቸው፥ ተደብቀው መሆኑ ይታወቅልን።

እነዚህን ጥያቄዎች አንድ ሰው ያርቅቃቸው እንጂ፥ የብዙዎች፥ የእጅግ ብዙዎች ጥያቄዎች መሆናቸው በየቀኑ የሚታይ፥ የሚሰማ፥ የሚነበብ ሐቅ ነው። “እናንተ እነማናችሁ?” የሚለን ካለ፥ “ዶክተር ዐቢይ ሕወሐትና ኦነግ በማህላችን የገነቡትን የከፋፋይ ድምበር ያፈርስልናል” በሚል ጽኑ እምነትና ሙሉ ተስፋ፥ በሄደበት ቦታ ሁሉ “ዐቢይ፥ ዐቢይ” እያልን የምንጠራው ኢትዮጵያውያን ነን። መጠናችንን ለማወቅ ከፈለገ፥ እኛ አኵርፈን ከቀረንበት ቦታ ይሂድና ስንት ሰው እንደሚያጅበው ይይ። “የሕዝብ ድምፅ መሰማት አለበት ብሎ” ቈርጦ የተነሣ መሪ ይኸንን የሕዝብ ድምፅ ችላ ብሎ በሰላም መኖር አይችልም። ደግሞም እኮ፥ በጎሳችን መጠራት “ኋላ-ቀሮች ናችሁ” ማለት ነው። ኢትዮጵያ ኋላ-ቀር ልጆች እንዳሏት እናውቃለን፤ ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ጥቂቶች ከሆኑ፥ በዘመነ ዲሞክራሲ የብዙዎች ድምፅ በጥቂቶች ድምፅ አይጨቈንም።

ጥያቄዎቻችን ከለውጡ አጀንዳ ውስጥ መግባታቸውን እስክንሰማ ድረስ እናምፃለን። “ለአመፃችን መሪ ያስፈልገናል” የሚል ካለ፥ አግኝተናል። ክቡር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ዑመር ይባላል። አዲስ የተሾመው የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዴንት ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያለውን ትልቅ ኀላፊነት ትቶ ወደ ሀገሩ የተመለሰው፥ የምንፈልገው መሪ ለመሆን ነው። የመጣው ኢትዮጵያን ከለከፋት የጎሰኝነት በሽታ ለማላቀቅ መድኃኒት ይዞ ነው። ተጠራጣሪዎች ካላችሁ፥ ይህ እንደ ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና እንደ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ለኢትዮጵያ በጭንቋ ጊዜ የደረሰላት ልጇ ከአቶ ካሣሁን ነገዎ ጋራ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ስሙት፤ https://www.sbs.com.au/yourlanguage/amharic/en/audiotrack/mustafa-builder-my-somali-ethiopian-identities-are-intertwined

ጎሰኞች፥ “መብታችን ይከበርልን” ሲሉ ይሰማሉ። መብታቸው ተጥሶ ከሆነ ጥያቄያቸው የሚገባ ነው። የመብት መከበር ጉዳይ የብዙዎቻችን ጩኸት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ “የሌላው መብት ይጣስ” የሚሉ ጎሰኞች ብቻ ናቸው፤ “ለኛ ተከልሎ በተሰጠን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የሌላ ክልል ኢትዮጵያዊ አይምጣብን” ይላሉ። የሌላውን መብት መጣስ ማለት ይህ ነው። ብዙዎቻችን፥ “የዲሞክራሲ ያለህ” እያልን የምንጮኸው የዲሞክራሲ ዋና ጥቅሙ የማንንም ዜጋ መብት እኩል የሚያስከብር ስለሆነ ነው። ዲሞክራሲን ተቀብሎ፥ ዲሞክራሲ የሚፈቅደውን መብትና የሚጠይቀውን ግዴታ አናከብርም ማለት አይቻልም። ጎሰኞች ግን ጎሳቸውን ለማዳበር ሙሉ ነፃነት ከመጠየቅ አልፈው ተጨማሪ መብት ይሰጠን ሲሉ ይሰማሉ። “ከሌሎች መብት ላይ ተቀንሶ ለኛ ይጨመርልን” ማለታቸው ነው። “አትንኩኝ፤ ለሌላው የሚሰጥ ማናቸው ነገር ለኔ አይነፈገኝ” ከማለት በቀር ሌላ ምን የመብት ጥያቄ አለ?

ኋላ-ቀር ለመሆን ያልተማረ መሆን አያስፈልግም። ለምሳሌ፥ በዚህ ጉዳይ የሊቁን የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን አቋም እንመልከት፤ የለንደኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአዘጋጀው የምሁራን ውይይት ላይ፥ ፕሮፌሰር በየነ ይኸንን ጥያቄ እንደኛ የሚያሣውን ሁሉ፥ “ለስንትና ስንት ዓመታት በነሱ የፖለቲካ ቅኝት የገዙን ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው” አለው። የስብሰባው አዘጋጅም ትዝብቱን አደነቀለት። ፕሮፌሰር በየነ፥ “አለባብሶ ቢያርሱ” የሚለውን ምሳሌ ጠቅሶ፥ የወረፈው አማራዎቹን መሆኑን ፊት ለፊት ሳይናገር፥ አለባብሶ አለፈው። አላወቀውም እንጂ፥ የወረፈው የኵርፊያችን መሪ ያደረግነውን አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ዑመርንና አያቶቹን ጭምር ነው። የወረፈው ዶክተር ብርሃኑ ነጋንና አያቶቹን ጭምር ነው። የወረፈው ጎሰኝነትን የሚነቅፉ የብዙ ጎሳዎች ልጆችንና አያቶቻቸውን ጭምር ነው።

እስቲ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ጠይቁልን፤ እነዚህ ከላይ ያነሣኋቸው የተከበሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን “ለስንትና ስንት ዓመታት ገዙን” የሚላቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው ወይስ አይደሉም? ካይደሉ፥ እነሱ የሚሉትን ሲሰማ፥ አማራውን ከመንቀፍ ይልቅ መሳሳቱን ቢገነዘብ አይሻልም ነበር? የአቶ ሙስጠፋ መሐመድ ዑመርን የትምህርት ደረጃ ባላውቅም፥ የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ትምህርት የመጠቀ ነው። በአሳተማቸው ጥናቶች ምክንያት በዓለም ደረጃ በመከበሩ ኢትዮጵያንና አስተማሪዎቹን (እኔን ጨምሮ) አኵርቷል። ሆኖም፥ ማን ወደፊት ማን ወደ ኋላ እንደሚያይ ስትመለከቱ፥ “ኋላ-ቀር ለመሆን ያልተማረ መሆን አያስፈልግም” ያልኩበትን ምክንያት ትረዱልኛላችሁ።

ኢትዮጵያ በነፃ ለዘላለም ትኑር። የነፃነት ጮራ ለፈነጠቁልን ለክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፥ ለክቡር አቶ ለማ መገርሳ፥ ለክቡር አቶ ደመቀ መኰንን፥ ለክቡር አቶ ደጉ አንዳርጋቸው ሙሉ ጤናና ረጅም እድሜ ይስጣቸው። ከያዙት የቀና መንገድ የሚያስወጣ ደንቃራ አያጋጥማቸው። እኛንም ዶክተር ዐቢይ በፍራንክፈርቱ ንግግሩ ላይ ለኢትዮጵያ ተስፋ ያደረገላት አንድ ባንድ ሲፈጸም ለማየት ያብቃን። አሜን።

Share.

About Author

Leave A Reply