Thursday, January 17

ስለ አዲሱ የአማራ ፓርቲ የግል አስተያየት (ግርማ ካሳ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የሚል የአማራ ድርጅት ተቋቁሟል። ማንም ዜጋም ሆነ ድርጅት የሌላዉን መብት እስካልነካና እስካልደፈረ ድረስ በፈለገ መልኩ የመደራጀት መብት አለው። እዚያ ላይ ይህ ድርጅት መቋቋሙ ያላስደሰተን ካለን፣ ባንደሰትም የሌላውም መብት ማክበር መቻል አለብን።

ይሄ ድርጅት የተቋቋመው “የአማራ ሕዝብ ወኪል የለዉም። እየተፈናቀለ ነው፣ በኦነጎች በሕወሃቶች እንደ ጠላት እየታየ ተለይቶ እየተጠቃ ነው፤ ይህ ሕዝብ ተደራጅቲ ራሱን መመከት አለበት …….” ከሚል ይመስለኛል። ምንም መካካድ የለብንም አማራ በሚባለውና በአማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ላይ ፤ላለፉት 27 አመታት ትልቅ ግፍና ጭካኔ ሲፈጸም ነበር። አሁንም እየተፈጸመነው። ይህ ጉዳይ ዝም ሊባልና ሊደባበስ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ዜጎች በአገራቸው እንደ መጤ የሚቆጠሩበት አሰራር ምንም ዜጋ ሊታገሰው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።

የኔ ትልቁ ጥያቄ ግን፣ “ይሄ አዲሱ የአማራ ድርጅት መስራቾች፣ አማራ የሚሉትን ብቻ በማቀፍ እንዴት ነው በአገር ደረጃ አማራ የሚሉትን ማህበረሰብ ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉት? “ የሚለው ነው። ራሱን አማራ ብሎ የሚጠራው ማህበረሰብ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 30% አካባቢ ነው።ከዚህ 30% አብዝኛው የኢትዮጵያ ብሄረተኛ ነው ። እንበል ቁጥሩ ላይ ቸር ሆነ ግማሹ የአማራ ብሄረተኛ ነው ብንል የኢትዮጵያ ህዝብ 15% ብቻ ነው የሚሆነው።

አንድ ደርጅት ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለው የፖለቲካ አቅም ሲኖረው ነው። የፖለቲካ አቅም ደግሞ የሚመጣው ከሕዝብ ድጋፍ ነው። 15% የሚሆንን ማህበረሰብ ብቻ በማቀፍ የፖለቲካ ሃይል ማግኘት አይቻልም። የፖለቲካ ኃይል ካላገኘ ደግሞ ጥቅሙን እናስጠብቅለታለን የሚሉትን ማህበረሰብ ጥቅም ማስጠበቅ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በአጭሩ አነጋገር የአማራ ድርጅት ያቋቋሙ ወገኖች የተቋቋሙለትን አላማ ከግብ የማድረስ አቅማቸው በጣም ውስን ነው የሚሆነው።

እኔ የአንድነት ሃይሉ አካል ነኝ።ወልቃይት አማራ ነው በሚል ሳይሆን (ወልቃይት አማራ ነው የሚለውን ስለማልቀበል)፣ “ወልቃይት ትግሬ ነው በሚል ወደ ትግራይ መጠቃለሉ ትክክል አይደለም፤ ወደ ጎንደር መግባት አለብት፤ ወይንም ራሱን የቻለ ክልል መሆን አለበት” ብዬ ከማንም የአማራ ብሄረተኛ ባልተናነሰ የጻፍኩና የተከራከርኩ ነኝ። አማራ ባልልም አማራዎችን ጨምሮ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ በኦሮሞና በሌሎች ክልሎች እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ በማጋለጥ፣ የነርሱ መብት እንዲከበር ድምጼን እያሰማሁ ነው። እንደ አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ ያሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ለኦሮሞና የኦሮሞ ብቻ ከሆነ አፓርታይዳዊ ክልል ወጥተው አዲስ አበባን ጨምሮ ራሱን የቻለ ሁሉም እኩል የሆኑበት የሸዋ ክልል እንዲኖር ከማንም የአማራ ብሄረተኛ ባልተናነሰ ጽፊያለሁ።ተሟግቻለሁ።

እንደ መኢአድ፣ ሰማያዊ ቀደም ሲል ደግሞ አንድነት ያሉ ፓርቲዎች በተፈናቀሉ ወገኖች ዙሪያ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እንዳደረጉ የሚታወቅ ነው። በምእራብ ሸዋ በኖኖ ከሁለት አመታት በፊት አማርኛ ተናጋሪዎች ሲፈናቀሉ መኢአዶች ነበሩ በቦታው ሂደው ከተፈናቃዮች የተሟገቱትና የነርሱን ጉዳይ ሕዝብ እንዲያውቀው ያደረጉት። በጉሩፈርዳ የነበረውን መፈናቀል ሕዝብ እንዲያውቀው ያደረጉት መኢአዶች ነበሩ። በቤኔሻንጉል ከጥቂት አመታት በፊት በነበረው መፈናቀል የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ቦታው ድረስ በመሄድ በክልሉ መንግስት ላይ ክስ መስረተው እንደነበረ የሚታወቅ ነው። በአጭሩ የአንድነት ሃይሉ ምንም አላደረገም ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በተፈናቃዮች ዙሪያ ሳይሆን በሁሉም አጀንዳዎች ዙሪያ የአንድነት ሃይሉ ተዳክሟል። የአንድነት ሃይሉን አጠናክሮ የተነሱ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ቢደረግ ኖሮ የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻል ነበር። አማራው እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ነው። በመሆኑን በማንም ዜጋ ላይ የሚደረግ መፈናቅል እንዲቆም መታገል ለአማራውም መታገል ነው።

ይሄን በማለቴ አንዳንድ ወገኖች ቅር ሊሰኙ ይችላሉ። ግን ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ ነው የማስቀምጠው። ይሄ አዲሱ ድርጅት በአማራ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች ውጭ ድግፍ አያገኝም። በርግጠኝነት በአዲስ አበባ ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ ባሉ አካባቢዎች ለዚህ ድርጅት የሚኖረው ድጋፍ ዜሮ ነው።

ይህ የአማራ ድርጅት ምን አልባት የፖለቲካ አቅሙን ለማጠናከር ከሌሎች አገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር ቅንጅት የመፍጠር ሐሳብ ሊኖረው ይችላል። ግን ከማን ጋር ሊቀናጅ ይችላል ? አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አረና፣ ኦፌኮ ..ለብቻቸው፤ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ስለገባቸው ነው መድረክ የሚል ስብስብ ውስጥ የሚገኝት። የዶር አባይ ኦህዴድ ፣ የነገዱን ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ ይሄን ጊዜ ወያኔ እስር ቤት ወርዉራቸው ነበር። ለአመታት እነ ጃዋር የኦሮሞ ብቻ አጀንዳ ይዘው ሲታገሉ ፣ ሌላውን ማህበረሰባት በማግለል የትም አልደረሱም። ትርፉ የበለጠ ሰቃይ ነበር። ወያኔ በአንድ በኩል፣ የሶማሌ ክልል በሌላ በኩል ሲመጡባቸው፣ ለ27 አመታት እንደ ጠላት ሲያዩትና ሲያፈናቅሉት ከነበረው ከአማራው ጋር መስራት አለበን ብለው፣ ታክቲካል ለውጥ አደረጉ። እነ ለማ ወደ ባህር ዳር በመሄድ የኦሮሞን ሳይሆን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ቢያንስ እዚያ ባሀር ዳር ላይ አንጸባረቁ። ያን በማድርጋቸው ወደ ስልጣን ለመዉጣት ቻሉ። ኦነግ፣ ለ40 አመትታ፣ ኦህዴድ ለስንት አመታት ያላገኙትን ኢትዮጵያ በማለታቸው፣ የሌላውን ድጋፍ በማግኘታቸው ነው የጠ/ሚኒስተር ጽ/ቤትን የተረከቡት።

ከላይ እንዳልኩት በአማራ ስም የመደራጀትን መብት አክብራለሁ። በአማር ስም የተደራጁ ወገኖችም የተደራጁበት ምክንያት በጣም እረዳለሁ። ሆኖም ግን ጊዜያዊ ነጥብ ከማስቆጠር ያለፈ፣ አላማቸውን ለማሳካት ግን አቅም አይኖራቸው። 85% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገለለ ድርጅት፣ እዚያው አማራ ክልል እንኳን፣ አገዉን፣ ኦሮሞዎች፣ ቅማንቱን፣ ትግሬው፣ድብልቁንና አማራ ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ብሄረተኛ ነኝ የሚለውን አግለው ጥቂት እርምጃዎች ከመኋዝ ባለፈ ረቀው ሊሄድ አይችሉም።

የጊዜው ፖለቲካና ግለት ይገባኛል። ግን ታክቲካል ሆነው የዛሬው ሳይሆን የነገዉን እናስብ እላለሁ። ይሄ በአማራ ስም የተደራጀው ድርጅት፣ በሂደት እነ ፕሮፌሰር አስራት ከመአህድ ወደ መኢአድ እንደተሸጋገሩት፣ አንድ ጎሳ ወይም ዘር ከመወከል አገር አቀፍ ወደ መሆን የመሸጋገር አላማ እንዳለው በግልጽ ቢያስቀምጥ ጥሩ ነው።ያን ካደረገ ምን አልባት የድግፍ መጠኑ ትንሽ ሰፋ ሊል ይችላል።

ይሄን ስጽፍ አዲስ ተየቋቋመው ድርጅት ተቃዋሚ መሆኔ አይደለም። በጭራሽ ልሆንም አልችላም። ይህ ድርጅት ፡

1) ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የሚደረሰውን ግፍና መራ፣ መፈናቀል በተመለለተ ፣ የዜጎች መፈናቀል እንዲቆም

2) የፌዴራል አወቃቀር በኦነግና በሕወሃት ብቻ ስለተሸነሸነ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት ያሉባባቸው አካባቢዎች መብታቸው እንዲከበር፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ፣ ከፈለጉ የራሳቸውን ክልል ማቋቋም እንዲችሉ

የመሳሰሉ አጀንዳዎችን ይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከጀመረ በነዚህ ሁለት አጀንዳዎች ዙሪያ የአላማ ልዩነት ስለማይኖረኝ የድርጅቱ አባል መሆን ባልቻልም (የኢትዮጵያ ብሄረተኛ ስለሆንሉ) አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ። በአማራ ስም ባይደራጁ ደስ ይለኝ የነበረ ቢሆንም የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን አብዛኞቹ የኔም ጥያቄዎች ስለሆኑ ልደግፋቸው ነው እንጂ የምችለው ልቃወማቸው አልችላም። ባለኝ መረጃ ይሄ አዲሱ የአማራ ድርጅት የአማራ ኦነግ ከሚባለው ዘረኛ ቤተአማራ ድርጅት በጣም፣ በጣም የተለየው ነው። እነዚህን ሁለት ደርጅት አንድ አደርጎ ማየት ዶር መራራን እና ኦነጎችን አንድ አድርጎ እንደማየት።

(ግርማ ካሳ)

Share.

About Author

Leave A Reply