ሻሸመኔ ከተማ ወደ መረጋጋት መመለሷን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሻሸመኔ ከተማ በአሁኑ ወቅት ወደ መረጋጋት መመለሷን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አለማየሁ እጅጉ በሰጡት መግለጫ፥ በሻሸመኔ ከተማ የኦ.ኤም.ኤን ዳይሬክተር አቶ ጃዋር ሞሃመድ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት አቀባበል ለማድረግ በከተማዋ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ለይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ በተፈጠረ አለመረጋጋት በሰዎች አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በተሳሳት መረጃ አማካኝነት አንድ የሻሸመኔ ከተማ የፀጥታና አስተዳደር በሮ ተሽከርካሪ መቃጠሉንም አስታውቀዋል።

ተሽከርካሪው ፀጥታ የማስከበበር ስራ ላይ በተሰማራበት ወቅት ቦምብ ጭኗል በሚል በተሳሳተ መረጃ በእሳት መቃጠሉ የተገለፀ ቢሆንም፤ ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ማጣራት ምንም ፍንጭ አለማግኘቱንም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

እስከ አሁን ፖሊስ የግርግሩ መነሻ ምክንያት ለማጣራት በምርመራ ላይ መሆኑንም ኮሚሽነር ጄኔራል አለማየሁ እጅጉ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ሻሸመኔ ከተማ እና በዙሪያዋ የነበረው ግርግር መረጋጋቱንም ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ፖሊስም በቀጣይ ቀናት ምርመራውን በማጠናቀቅ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ ይሰራል ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ህብረተሰቡም በመረጋጋት ትክክለኛ መረጃዎችን ከፖሊስ ማግኘት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፥ በሻሸመኔ ከተማ በተፈፀመ የወንጀል ተግባር ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

ዶክተር ነገሪ ከኦ.ቢ.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በሻሸመኔ ከተማ ቦምብ ተገኝቷል በሚል የተሳሳተ መረጃ ግርግር እንዲፈጠር መደረጉን ገልፀዋል።

ሆኖም ግን ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ማጣራት ቦምብም ይሁን ምንም አይነት ከቦምብ ጋር የሚመሳሰል ነገር እንዳልተገኘ አስታውቀዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply