ቁርጡ ከታወቀ አምባገነን መንግስት ይልቅ ህግና ሃይማኖት የማይገዛው አንድ ሰው ያስፈራኛል። (መላኩ ብርሃኑ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አምባገነን መንግስት በፈለገው ሰዓት የሚተኩሰው መሳሪያ አለው። የፈለገውን የሚያጉርበት እስር ቤት አለው። አፋኝና ደፍጥጠው የሚገዙ ህጎች አሉት። ንጹሁን ሰው ወንጅለው ዘብጥያ የሚያወርዱ ፖሊሶችም አሉት። ወንጀል ያልሰራውን ሰው አመታት አከናንበው ወህኒ የሚልኩ ዳኞችም አሉት። ሙሰኛና ጨካኝ ባለስልጣናትም አሉት ። ቢሆንም አምባገነን መንግስትን አልፈራም።

አምባገነን መንግስት ክፉ ፖሊሶች ቢኖሩትም ደግ ፖሊሶችም አይጠፉትም። የማልስማማበት ህግ ቢኖረውም ለስሙ ሲል መብቴን የሚጠብቅ ህግም ያወጣል። ቅን የማይፈርዱ ዳኞች ቢኖሩትም ሃቅ ፈራጆች ከመሃል አላጣም። ጉቦ ወዳድ ባለስልጣናት ቢኖሩትም ለህሊናቸው ያደሩ ባለስልጣናትም ይኖሩታል። እስር ቤት መወርወር ቢችልም ከእስር ቤት የሚያወጣ ይቅርታም አይጠፋውም።

አምባገነን መንግስት የሚፈልገውን ስለማውቅ ደህንነቴ በገዛ ምርጫዬ ላይ ነው። ካልነካሁት አይነካኝም። ጸጥ ለጥ ካልኩ አይጣላኝም። ዝም ካልኩ ሰላሜን አይነሳኝም። ህጉ፣ ፖሊሱና ፍርድ ቤቱ ስራ ስለማይፈቱ ቢያንስ የመኖርና ያለመኖር ስጋት አያስበረግገኝም።

አምባገነን መንግስት ካሰመረልኝ መስመር ያለፍኩ ቀን፣ ስላልፈለገ ሳይሆን መንግስት ስለሆነ ብቻ ተደብቆ ይገርፈኝ ይሆናል እንጂ አለም እያየው በአደባባይ አይወግረኝም። በዘዴ ወንጀል ፈጥሮልኝ ታፔላ ለጥፎልኝ ለእስር ያመቻቸኝ ይሆናል እንጂ አለም እያየው በአደባባይ ዘቅዝቆ አይሰቅለኝም። አለም በቃኝ ከትቶ ቢቸነክርብኝ እንኳን አንድ ቀን የመፈታት ህልም አላጣም። ቢከፋ ቢከፋ በሀሰት ሞት ያስፈርድብኝ ይሆናል እንጂ በህይወት እያለሁ እሳት አይለኩስብኝም። አምባገነን መንግስት አሰቃይቶ ቢገድለኝ ቢያንስ የኔ ሞት በርሱ ላይ አንድ ጥቁር ነጥብ ስለሆነ ከንቱ ሆኜ አልቀርም።

ዝምታ በቅቶኝ ቆርጬ ልታገለው የተነሳሁ ቀን ደግሞ ምርጫዬ ነውና ለሚመጣው ነገር ራሴን ለማዘጋጀት ጊዜ አላጣም።

ልሸሸውና ልደበቀው ስለምችል እስኪይዘኝ ድረስ እጎዳዋለሁ። ቢያሳድደኝ ቀን ካልጣለኝ በቀር ላመልጠው እድል አለኝ።ቢከፋ ተሰድጄ ከመዳፉ እርቃለሁ። በለስ ቀንቶት ቢይዘኝ ለርሱ ድል ስሆን ለሌሎች ወኔ እሆናለሁ። ወህኒ ቢወረውረኝ ከስሜ ፊት “ጀግና” የሚል ቃል አተርፋለሁ። “ወፌላላ” ቢገርፈኝ ለእርሱ ሽንፈት ለእኔ አሸናፊነት ይሆናል። ቢገድለኝ ሞቴ ተራ ሞት ስለማይሆን ባለታሪክ ነኝ ። እኔ ባልኖር ስሜ ግን ህያው ይሆናል። ጊዜ ቢፈጅም የታገልኩለት ዓላማ አንድ ቀን አሸንፎ ሌሎች ነጻ ስለሚወጡ በነገው ለውጥ እጽናናለሁ።

እኔ ብቻ ልድፈር እንጂ አምባገነንነትን መታገል ራስን በመስጠት ከሚገኝ ትርፍ ውጪ ደመከልብ የሚያደርግ ኪሳራ የለውም። አምባገነን መንግስት የሚፈራ ቢሆን ኖሮ አለም ታሪካቸውን በኩራት የምትዘክርላቸውን ጀግኖች ባላፈራች ነበር።

ይልቅስ የህግና ሃይማኖት አጥርን ሰብሮ የወጣ አንድ ሰው ከማንም ከምንም በላይ ያስፈራኛል። ህሊናውን ማዘዝ ያልቻለ አንድ ሰው ከአውሬ በላይ ያስደነግጠኛል።

በምክንያት ስለማያስብ ፣ በምክንያት ስለማይወስንና ለሚያደርገው ነገር ምክንያት ስለማይፈልግ ከአንድ “ጉልቤ” መንግስት ይልቅ እንዲህ ያለ አንድ ሰው በጣም ያስፈራኛል።… ከሁሉ በላይ ግብታዊ ነውና ተጠንቅቄ ልሸሸው ወይም ፊትለፊት ገጥሜ ልታገለው ስለማልችል አጥብቄ እፈራዋለሁ።

ዘሬ ዘሩ ካልሆነ ባገኘው ነገር ይወግረኛል። ብሄሬ ብሄሩ ካልሆነ ባገኘኝ ቦታ ያሳድደኛል። ሃይማኖቴ ሃይማኖቱ ካልሆነ ባገኘኝ ስፍራ እንደእባብ ቀጥቅጦ ይደፋኛል። ያለክስ ይፈርድብኛል። ያለምክንያት ንብረቴን ያወድማል።ባልገመትኩት ቀን ከመኖር ወዳለመኖር ይለውጠኛል። ከጨከነ ሬሳዬን መንገድ ላይ እየጎተተ ይጨፍራል። በጣም ከጨከነ አስከሬኔን አቃጥሎ እሳት ይሞቃል። ወይም አይኔ እያየ ጉድጓድ ከትቶ አፈር ይመልስብኛል። ወይም ገድሎ ዘቅዝቆ ይሰቅለኛል። የሚገዛበት ሞራል፣ የሚፈራው አምላክ፣ የሚያከብረው ህግ ፣የሰከነ ህሊና የለውምና ከምንም አብልጬ እፈራዋለሁ። ህይወቴን ታሪክ አልባ ፣ ደሜን ደመ ከልብ የሚያደርገው እሱ ብቻ ስለሆነ በጣም እፈራዋለሁ።ይህን አይነት ሰው የትም ቦታ የትም አለም ላይ አለ።የህግ መኖር በመንጋ ሃሳብ ስር ሊወድቅ ሲል በምልክትነት የሚከሰት ሰው ነው። ይህ ሰው እኛ ራሳችን ነን።

Criminology እንዲህ ይላል “በህግ፣ በሃይማኖት እና በባህል አጥር ታስሮ እንጂ በምድር እንደሰው የከፋ ጨካኝ ፍጡር የለም” ። ልክ ነው። ሰው ከነዚህ አጥሮች ራሱን ፈትቶ የለቀቀ ቀን በምድር የመጨረሻው አውሬ ይሆናል። ይህንን ጭካኔ በደቡብ አፍሪካ xenophobia ጊዜ አይቼው በጣም ፈርቼው ነበር። ይህን የጭካኔ ጥግ በሩዋንዳው የሁቱ ቱትሲ ኢንተርሃምዌይ ዘመን መከሰቱን አይቼ ፈርቼው ነበር። ይህ የሰው ልጅ ጭካኔ በደርግ-ኢህአፓ ዘመን እኛው ጋ ተከስቶ ትናንት ለትውልድ መማሪያ እንዲሆን የ “NEVER AGAIN” ሃውልት ሲቆምለት በቦታው ነበርኩ። እነሆ አሁን ደግሞ የሞራል አልባ ሰዎች ጭካኔ በሌላ ገጽ እየመጣብን ነው ብዬ በጣም ፈራሁ።

አሁን ህግን ማክበር ምርጫ ሳይሆን ግዴታነቱ ይሰመርበት። Mob justice “በቃ !” ይባል። በምንፈልገውና በምንደግፈው ዴሞክራት መሪ የሚመራ መንግስት አለን። የህግ ማስከበር ሃላፊነቱን ይወጣ። ጸጥታ ሃይሉ ስራ ይጀምር። ህጉ በስራ ላይ መሆኑን ያስመስክር። በደካማው የሰው ባህሪ ገብተው የአውሬነቱን ፈረስ ኮልኩለው የሚጋልቡትን ሁሉ ይቅጣ። እዚህም እዚያም የምናየው ይህ ጥፋት ዛሬ በእንቁላሉ ካልመከነ የነገውን ጽንስ ማጨንገፍ እንዳይከብድ እሰጋለሁ። ከሁሉም በላይ ግን እግዚአብሄር ይህችን የቃልኪዳን ሃገር ከመከራ ይከልላት ዘንድ ጸሎት ግድ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply