ቅድሚያ ! ከምርጫው በፊት ለዴሞክራሲ ተቋማት !

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዶን ትሬሲ የተባለ አሜሪካዊ ምሁር ይህንን ይላል። “የመንግሥት ተቋማት በሙሉ የሕዝብ ጌታ እንሁን እስካላሉና አገልጋይነት ባህሪያቸው እስከሆነ ድረስ በተፈጥሮአቸው ዴሞክራቲክ ናቸው ማለት ይቻላል። ለማገልገል ተብሎ በተያዘ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ዕድሜ ልክ ለመኖር መሞከር ጌታ ነኝ ባይነትና ኢዴሞክራሲያዊ መሆን ነው። ዴሞክራቲክ ተቋማት እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ሁሉንም ሕዝብ በሕግ እና በእኩልነት ብቻ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። የሕግ የበላይነት ዴሞክራቲክ ነው የሚባለው በሕግ ፊት እኩልነትን ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነው። አምባገነን መንግሥታትም በሕግ የበላይነት እንገዛለን ይሉ ይሆናል።

ነገር ግን በሕግ ፊት እኩልነትን ስለማያረጋግጡ ዴሞክራሲያዊ ለመባል ብቁ አይደሉም። አብዛኞቹ መንግሥታትና ሃገራት ሲፈጠሩ ባላባታዊ እና ኢዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ይዘው ነው። በዚህ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የዚሁ “ህዝብን ጌታ ሆኖ የመግዛት” ተፈጥሮ ቅሪት አለበት። ይህ ከሥርዓቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት ጊዜ ይፈልጋል” ዶን ትሬሲ እንዳለው በኢትዮጵያም ዴሞክራሲያዊ ተብለው የተመሠረቱት መንግሥታት በሙሉ የህግ የበላይነትን እና በሕግ ፊት እኩልነትን አጣምረው በማክበር በተግባር መተርጎም ስላልቻሉ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት የመሆን መመዘኛን አላለፉም። ከነዚህ ሁለቱን የቅርብ መንግሥታት ነጥሎ ማየት ይቻላል። ደርግ እና ኢህአዴግ።

ደርግ ንጉሱን ከዙፋናቸው ነቅሎ ስልጣን ላይ ከወጣበት ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ኢህዲሪን ለመመስረት አንድ አመት እስከቀረው 1979 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን ያለምንም ሕገመንግሥት ‘በጨበጣ’ አስተዳድሯል።

ከዚያ በፊት አገር በአዋጅና ድንጋጌዎች ትመራ ነበር። ደርግ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ ከደርዘን ዓመት በኋላ ሕገመንግሥት አርቅቆና አጽድቆ ለሕዝቡ መተዳደሪያ ብሎ ቢሰጥም ፣ ያንን ተከትሎም በ1980 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢህዲሪ)”ን ቢያፀድቅም ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ ግን በአግባቡ መረዳት ሳይችል ቀረና “ዴሞክራሲያዊ” ያላትን ሃገር ከስም ያልዘለለ የቃሉ እዳ ተሸካሚ አደረጋት። የደርግ ዘመን “ከንጉሱ ዘመን ከፍቶ” ዴሞክራሲ ዜሮ የገባበት፣ ዜጎችም የገዛ ትንፋሻቸውን ማመን አቅቷቸው የኖሩበት መጥፎ ዘመን ሆኖ አለፈ።

ደርግ ገና በለጋነቱ የተገዳደሩትን እንደ ኢህአፓም ይሁን መኢሶን ያሉ ግራ ዘመም የማርክሲስት ሌኒኒስት አቻ ፓርቲዎችን ቀስ በቀስ ውጦና ሰልቅጦ ከምድረገጽ በማጥፋት ከማንም ጋር መወዳደር ሳያስፈልገው ኢሰፓን በመሪ ፓርቲነት መሠረተ። ቀጥሎም ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ወደ ኢህዲሪ ሽግግር በማድረግ ራሱን ከወታደር ወደሲቪል መንግሥትነት ቀይሮ አገር መምራት ጀመረ። ብቻውን የሮጠ የሚያሸንፈው የለም እንደሚባለው ደርግም ያለምንም ተቀናቃኝ ብቻውን አስተዳዳሪ ሆኖ መንግሥትነቱን በማወጅ የለየለት አምባገነንነቱን አሳወቀ። ደርግ አገሪቱን “ዴሞክራሲያዊ” ብሎ ቢሰይማትም ያለቦታው ከተደነቆለው ቃል ባለፈ ግን በተግባር አንዲትም ቀን የዴሞክራሲን ሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳያሳይ አለፈ።

ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ ሕገመንግሥቱን እስካጸደቀበት 1987 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የቆየው በሽግግር መንግሥት ቻርተር ነው። ከዚያም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሎ የሰየማትን ኢትዮጵያ ለራሱ በሚስማማው መልክ አርቅቆና አጽድቆ ሥራ ላይ ባዋለው በ1987 ሕገመንግሥት ማስተዳደር ጀምሯል። እንዳለመታደል ሆኖ የመጣው ሁሉ ስሟ ውስጥ “ዴሞክራሲያዊ” የሚል ቃል የሚቀላቅልባት ነገር ግን የዴሞክራሲን ጭራ ይዛ የታማውቀው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ላም አለኝ በሰማይ እያለች እንድትኖር ተፈረደባት።ከላይ የጠቀስነው አሜሪካዊ ምሁር እንዳለውም “አምባገነን መንግሥታትም በሕግ የበላይነት እንገዛለን ይሉ ይሆናል። ነገር ግን በሕግ ፊት እኩልነትን ስለማያረጋግጡ ዴሞክራሲያዊ ለመባል ብቁ አይደሉም።”

ብዙዎች እንደሚተቹት ዴሞክራሲን በተመለከተ በደርግ እና በኢህአዴግ መካከል ያለው ልዩነት ደርግ ዴሞክራሲን በሃሳብም በተግባርም መከልከሉ ሲሆን ኢህአዴግ በተቃራኒው ዴሞክራሲን በሃሳብ ፈቅዶ በተግባር ግን እንቁልልጭ እያለ መኖሩ ነው። በዚህ ስሌት ደርግ እውነተኛ ማንነቱን አውጥቶ በማሳየት እንቃወማለን ከሚሉት ጋ ፊት ለፊት መጋፈጡ የመንግሥትነት ባህሪውን ምንነት ለማወቅ የረዳ ሲሆን ኢህአዴግ ደግሞ ዴሞክራሲን ሕጋዊ ሥርዓት አድርጎ ሲያበቃ በተግባር ግን የቱንም ለመፈጸም ፍቃደኛ አለመሆኑ የማንነት ውሉን ለመረዳት ከማዳገቱ በላይ እንደመንግሥት መስራች ፓርቲነቱ ከርሱ የማይጠበቅ ተለዋዋጭነትን የተላበሰ ፓርቲ ሆኖ ታይቷል። በዴሞክራሲ ሚዛን ሲታዩ ከሁለቱ መንግሥታት ውስጥ ደርግ የማይፈጸም ሕግ ደንግጎ ዴሞክራት መንግሥት ከመባል ይልቅ ዴሞክራሲን በይፋ ከልክሎ አምባገነን መባሉ ቢያንስ በህግ ሕግ የሚያላግጥ አሿፊ መንግሥት መሆኑን ያመላክታል ።

ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ሽግግር ሊባል የሚችል ነው። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ውስጥ የሰነበተ አቅም መንገዱ ለኢትዮጵያ አላዋጣ ማለቱን ተገንዝቦ ሕዝቡን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ተነስቷል። በዶክተር ዐብይ እና በአጋሮቹ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት ከኖረችበት የስም ዴሞክራሲ ወጥታ በተግባር የሚመነዘር የዴሞክራሲ ፍሬ እንድታፈራ መንገዶች እየተመቻቹ መሆኑም ታይቷል። ይህ ሂደት እውን እንዲሆን ቀዳሚው እርምጃ ብሄራዊ እርቅ እና ይቅርታ ነውና በመንግሥት ወገን እስካሁን ለጠፉት ጥፋቶች እና ለተካሔዱት “ቆሻሻ ተግባራት” ሕዝብ በይፋ ይቅርታ ተጠይቋል ኢህአዴግ የሕዝቦች ወኪል ነኝ ብሎ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ከ1983 ወዲህ ሕዝብን እና ሃገርን ራሱ የፈጠራቸው እስኪመስለው ድረስ እንደልቡ በፈለገው መንገድ ሲገዛ እንዳልኖረ ዛሬ ዘመን ተለውጦና ከውስጡ በመጣ ለውጥ ተገፍቶ ለሰራው ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ በኩል ይፋዊ ይቅርታ አቅርቧል። ይህ የመጀመሪያው ሥራ ሲሆን ቀጣዩ ደግሞ ዴሞክራሲ በሕገመንግሥቱ ለሕዝብ ተሰጥቷል ብለው በዚሁ ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ሃሳባቸውን በነጻ የገለጹ፣ የተደራጁና የተሰባሰቡ፣ ፓርቲ መስርተው በተፎካካሪነት ለመታገል የተነሱ እንዲሁም የኢህአዴግን የተጣመመ መንገድ በአንድም ይሁን በሌላ ለማቃናት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ዜጎች በዚሁ ተግባራቸው ብቻ ከታጎሩበት እስር ቤት በይቅርታ እና በምህረት መልቀቅ ነው። ይህም ለህዝብ ጥቅም እንጂ ለራስ ባልሆነ የፖለቲካ ትግል ውሰጥ ገብተው ከኢህአዴግ ጋር ፊት ለፊት በተያዩ ዜጎች ሳቢያ ኢህአዴግ የአምባገነንነት ካባውን ደርቦ አገሪቱን የዴሞክራሲ ከርቸሌ ያደረገበትን ዘመን አሳጥሯል።

እነዚህ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ዘንዳ ቀሪው የመንግሥት ተግባር የነበረው በውጭ ያሉ፣ ለአንዲት ኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅም ነፍጥ አንስተውም ይሁን በሃሳብ ተግተው የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደሃገር ቤት ገብተው ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያካሂዱ መጋበዝ ነበር። ይህም እጅግ ስኬታማ በሚባል ሁኔታ ተከናውኗል።

እነሆም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ የአሸባሪነት ካባ ተደርቦላቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ተሰድደው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ወደሃገራቸው ተመልሰዋል።የህሊና እስረኞች (PRISON OF CONSCIENCE) ተለቅቀዋል። ሃገር ውስጥ ተደራጅተው የተሰደዱም ይሁኑ በውጭ ሃገር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደኢትዮጵያ ገብተዋል።እንደአርበኞች ግንቦት ሰባት እና ኦነግ እንዲሁም ኦብነግ ያሉ በትጥቅ ትግል ጭምር የታገዘ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ድርጅቶችም ተመልሰዋል። ከዚህ በኋላ ምን ቀረ? በኢትዮጵያ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዶ ህዝብ የመረጠው ፓርቲ አገር እንዲያስተዳድር መምረጥ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በተለያዩ መድረኮች ላይ እንደተናገሩት የርሳቸው ብቸኛ ግብ በኢትዮጵያ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ በማካሄድ እውነተኛ ዴሞክራሲ መስፈኑን ማረጋገጥ ነው።ለዚህም በውጭ ሃገር የሚኖሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደሃገር ቤት ገብተው ሁለት ዓመት ለቀረው የ2012 ምርጫ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል። ይህንን ጥሪ የተቀበሉም ገብተው ዝግጅት እያደረጉ ነው። ግን ከ2012 ምርጫ በፊት የሚቀድም ዐብይ ጉዳይ አለ። የዴሞክራሲ ተቋማት የአመለካከት እና አሰራር ለውጥ አድርገው የዴሞክራሲ ሂደቱን በአግባቡ መምራት እና መዳኘት በሚችሉበት አቅም ማጠናከር።

ዶን ትሬሲ እንዳለው “የመንግሥት ተቋማት በሙሉ የሕዝብ ጌታ እንሁን እስካላሉና አገልጋይነት ባህሪያቸው እስከሆነ ድረስ በተፈጥሮአቸው ዴሞክራቲክ ናቸው ማለት ይቻላል። ለማገልገል ተብሎ በተያዘ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ዕድሜ ልክ ለመኖር መሞከር ጌታ ነኝ ባይነትና ኢዴሞክራሲያዊ መሆን ነው።” በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት ችግር የለም። ፍርድ ቤቶችም፣ ምርጫ ቦርድም፣እንባ ጠባቂ ተቋምም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም፣ ሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔና ፕሬስን ጨምሮ ሌሎችም አሉ። በአንጻሩ በበጎ አድራጎት ማኅበራት ተፈቅዶላቸው በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚሰደሩ አገር በቀል እና የውጭ ተቋማት ግን ከመድረኩ እንዲገለሉ ተደርገዋል። የግሎቹን እንተዋቸውና በመንግሥት የተቋቋሙትና አሁንም ያሉት የዴሞክራሲ ተቋማት በርግጥም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ሰርተዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ግን ያስፈልጋል።

ምርጫ ቦርድ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ አለ የሚባለውን ዴሞክራሲ የሚያረጋግጡ ናቸው ተብለው የተቋቋሙት የዴሞክራሲ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ እና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ተግባር ሳይሆን መንግሥት ያዘዛቸውን ብቻ ሲተገብሩ አይተናል። ይህ ደግሞ ሕዝብ በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ቢበደል አቤት የሚልበት ቦታ ቢኖርም ፍትህ ግን እንዳያገኝ አድርጎታል።

በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ኢህአዴግ በግልጽ የሕዝብ ድምጽ አጭበርብሯል ተብሎ ክስ እየቀረበበት ምርጫ ቦርድ ግን የኢህአዴግ የራሱ ስለሆነ የኢህአዴግን አሸናፊነት ከማጽናት በቀር የወሰደው አንዳች እርምጃ የለም። ምርጫ ቦርድ በውስጡ ያሉት ሰራተኞች ጭምር የኢህአዴግ አባላት መሆናቸውን ሕዝብ በማስረጃ እያረጋገጠ ነጻ ተቋምነቱን ማሳመን አልቻለም።በኢትዮጵያ ኢህአዴግን ተቃውመው የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድም ቀን ምርጫ ቦርድን አምነውት አያውቁም። ብዙ ጊዜም ወቀሳ ያቀርቡበታል። ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ቦርዱን ራሱን ለመክሰስ ብዙ ርቀት የተጓዙም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።

“ፍሪደም ሃውስ” የተባለው በዓለም ዙሪያ በየአገሮቹ የሚታየውን የነፃነትን ሁኔታ የሚከታተለው ተቋም በአንድ ወቅት ባደረገው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የተካሄዱትን ምርጫዎች “ነፃ ያልሆነ” (not free) በሚል ገልፆታል:: ምርጫዎች የሚለኩት በሂደቱ ዴሞክራሲያዊነትና አሳታፊነት፣ ተአማኒነትና ፍትሐዊነት እስከሆነ ድረስ እስከዛሬ በአገራችን የተካሄዱት ምርጫዎች እነዚህን መለኪያዎች ያለሟሟላታቸውን ለመረዳት ከባድ አይሆንም::

አንደኛ ነገር ምርጫዎቹ በሙሉ በኢህአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል መተማመንን አልፈጠሩም:: ምርጫዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከ134 ሀገራት በላይ እንደሚንቀሳቀሰው “The International Foundation for Electoral Systems” እንደተሰኘው ተቋም ጥናት ከሆነ በዘመነ ኢህአዴግ በተካሄዱት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምርጫዎች የተቃዋሚዎች የመወዳደር አቅም እጅግ ደካማ የነበረ በመሆኑ “ኢህአዴግ በምርጫዎቹ ዴሞክራሲያዊ መሆን ወይም አለመሆን ብዙም አልተጨነቀም” በሌላ በኩል ግን በአራተኛው ወይም በምርጫ 97 ተቃዋሚዎች ተጠናክረው ሲቀርቡ “ኢህአዴግ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሲኮንንና ለመቀልበስም የተሳካ ጥረት ያደረገበት ወቅት ነበር” ተብሏል::

በተለይ አሉ የተባሉ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተሸነፉበት ምርጫ በሚገርም መልኩ ገዢው ፓርቲ ምርጫው እንደተጭበረበረ አድርጎ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በመውሰድ በዳግም ምርጫው ባለስልጣናቱን እንዲመለሱ ሲያደርግ በሻሸመኔ ደግሞ በግልፅ የምርጫ ኮርጆዎች እንዲዘረፉ በማድረግ “በተሰረቁ የሕዝብ ድምፆች” የድርጅቱ ባለሥልጣናት ዳግም የምርጫው አሸናፊ እንዲሆኑ መደረጋቸው “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ” ላለበት ድክመት ጉልህ ማሳያ ተደርገው የሚወሱ እውነታዎች ናቸው::

እንዲህ ያለውን ምርጫ ታሪክ በማድረግ ነፃ ምርጫ ማካሄድ የምርጫ ቦርዱ አጣዳፊ ሥራ ሊሆን ቢገባውም የቦርድ አወቃቀሩ እስካልተለወጠና በተለይም መሠረታዊ የአቅም ግንባታ አፈፃፀም ለውጥ (ትራንስፎርሜሽን) እስካላመጣ ድረስ ምርጫ ማድረግ የሚመከር አይሆንም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በግልጽ በሚታይ አድልዎ በሃገሪቱ የሚንሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጥፋት ሲፈጽምና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሥልጣንን ተቆናጦ እንዲጨፍር እገዛ ሲያደርግ የኖረ ተቋም ነው።

ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያፈገፍጉ ምክንያት የሆናቸው አንድም የምርጫ ቦርድ ግልጽ አድልዎ መሆኑን ይናገራሉ። ኢህአዴግ በ1997 ዓ.ም አሸናፊነቱን ሲያውጅ ሕዝብ ገና ለምርጫ ተሰልፎ ነበር። በብዙ ጣቢያዎች ቆጠራው አልተጠናቀቀም ነበር። ምርጫ ቦርድ ግን ይህንን አልተቃወመም። እንደውም አጸናው። በዚህ ሳቢያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ቦርድ ላይ የነበረውን የገለልተኛ ተቋምነት እምነት አነሳ። በዚህ ስሌት ይህ ምርጫ ቦርድ ከምርጫው በፊት ራሱን እስካልለወጠ ድረስ አሁንም ከኖረበት ኢህአዴጋዊ አድልዎ አስተሳሰብ ተላቅቆ ፍትሃዊ ዳኛ ይሆናል ብሎ ማለት ያስቸግራል።

በመጀመሪያ ራሱን በድጋሚ ፈትሾ አወቃቀሩን አስተካክሎ እና ለፖለቲካው ፉክከር ምህዳር መፍጠር በሚችልበት መንገድ ተዘጋጅቶ በፍጹም ገለልተኛ ስሜት እና ዓላማ ለመሥራት ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሰራሮች በአዲስ በመተካት የሚካሄደው ምርጫ ፍትሃዊ እና ግልጽ እንዲሆን ከሌሎች የዳበረ ዴሞክራሲ ካላቸው ሃገራት ልምድ ጭምር ቀስሞ በአዲስ መልክ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ መዘጋጀት አለበት።

የአሁኑ የምርጫ ፉክከር እንዳለፈው ጊዜ በቀላል ቡድኖች መካከል የሚካሄድ አይሆንም።ግንቦት ሰባትን ፣ ትዴህን ፣ ኦነግን እና ኦብነግን የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኢህአዴግ ጋር ፉክከር የሚያደርጉበት መድረክ ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ የብዙዎች ዐይንና ፍላጎት የሚያርፍበት በመሆኑ ጥቂት ስህተት እንደቀደመው በፓርቲና በመንግሥት መካከል በሚደረግ ጭቅጭቅ የሚያበቃ ሳይሆን በፓርቲና በፓርቲ መካከል ጭምር ግጭት ሊያስነሳ ሕዝብንም ወደጥፋት ሊመራ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ከምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዝ ጀምሮ እስከ ቅድመ ዝግጅት እስከታዛቢ እና እስከ አስመራጭ አባላት ድረስ ከዚያም ድህረ ምርጫ ድምጽ ቆጠራ እና ውጤት ማሳወቅ ድረስ በከፍተኛ ገለልተኝነት እና ጥንቃቄ መስራት ሊያስፈልግ ይችላል። በመሆኑም አሁን ካለው አደረጃጀት እና በሕዝብ ዘንድ

ካለው አናሳ አመኔታ አንጻር ሲታይ ምርጫ ቦርድ ከምርጫው በፊት ራሱን መለወጡ የግድ ይሆናል። ፍርድ ቤቶች የአንድ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ዋነኛ መገለጫ የሆነው የሕግ የበላይነት /rule of law/ ነው። ይህን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችሉት ደግሞ ፍርድ ቤቶች ናቸው። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት አሪስቶትል የተባለው የግሪክ ፈላስፋ ስለ ሕግ የበላይነት ሲናገር ‹‹የሕግ የበላይነት ከማንኛውም ሰው የበላይነት የተሻለ ነው››! “The rule of law is better than that of any individual”. ብሎ ነበር::

ከአርስቶትል በኋላ የመጡት ምዕራባዊያን የሕግ ተመራማሪዎችም ይህንንም ሃሳብ ይበልጥ በማጠናከር ‹‹ንጉሥ ራሱም ቢሆን በሰዎች የበላይነት ስር መሆን አይገባውም፤ ከአምላክና ከሕግ በታች እንጂ:: ምክንያቱም ንጉሡን ንጉሥ ያደረገው ሕጉ ነውና›› “The king himself ought not to be subject to man, but subject to God and the law, because the law makes him King”. በማለት የሕግ የበላይነትን አጽንተውታል:: የዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብም አሪስቶትል ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ከሰነዘረው ሀሳብ የተለየ አይደለም:: ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም “በሕግ ፊት እኩል ነው” የሚባለው የሕግ የበላይነት ከማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት አለበለዚያም ፓርቲ የሚበልጥ ጉዳይ ስለሆነ ነው::

በሰለጠነው ዓለም ተቀባይነት ያገኘው የሕግ የበላይነት ጽንሰ ሀሳብ መሠረቱ የግሪክ ዴሞክራሲ አባቶች የሚባሉት ፈላስፋዎች ያፈለቁት ሀሳብ ነው:: በዴሞክራሲ አግባብ መንግሥት ማለት የሕዝብ ውክልና ያለው ተቋም ማለት ሲሆን የሕግ የበላይነትን በሚገባ ማስፈጸም ካልቻለ ግን ይህ መንግሥት የሕዝብ መንግሥት ሳይሆን የተወሰኑ መደቦች የመንግሥትነት ሳይሆን የመደብ እና የቡድን ሚና ሲጫወት ነው የኖረው። የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥባቸው ፍርድ ቤቶችም በተቃራኒው መንግሥት ከሕግ በላይ መሆኑን ሲያውጁለት ቆይተዋል። ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ የዴሞክራሲን ጽንሰ ሃሳብ በተግባር ለመተርጎም በተለይ ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ ገዢው ፓርቲ የሚፈጥራቸውን በደሎች ለማከም የሠሩት ሥራ አናሳነት ለጊዜው ቀርቶ ምርጫን በሚያህል ግዙፍ ጉዳይ ፓርቲና ሕዝብ በድምፅ መጭበርበር ሲራኮቱና ሰው ሲጎዳ ጭምር ለቀረበላቸው ክስ ተገቢ ፍትህ አልሰጡም።

(በቅርቡ በኬኒያ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፍርድ ቤት የተጫወተውን ሚና ልብ ይሏል።) ፍርድ ቤቶች አንድ ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ፣ መብቱን ተጠቅሞ በገለጸው ሃሳብ እና ኢህአዴግን በመቃወሙ ብቻ ተከስሶ ሲታሰርና ሲንገላታ ፍትህ ሰጥተው ያንን ዜጋ ነጻነቱን አላረጋገጡለትም። የፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ተቋምነት በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ ሳቢያም የካንጋሮ ፍርድ ቤት ተብለው ቅጽል ስም እስኪወጣላቸው ድረስ የሕዝብ አገልጋይነታቸው ተረስቶ ኖሯል። በተለይም በማናቸውም ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ አለመስማማት በሚከሰት ጊዜ ፈጥነው ገለልተኛ አቋም በመያዝ ጉዳዩን መርምሮ ፍርድ መስጠት ላይ ያለባቸው ድክመት ላለፉት 27 ዓመታት ሲወራለት የኖረ ነው። በግልጽ አድልዎ በመፈጸም የዜጎቸን በሕግ ፊት እኩልነት ማረጋገጥ ባለመቻላቸው አገሪቱን የአምባገነን አስተዳደር ምሳሌም አድርገዋታል። በማንኛውም የመንግሥት ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መንግስት ብቻ እንዲረታ እና ዜጎች እምባቸውን ረጭተው እንዲመለሱ ያደርጉም ስለነበር ምሬት እና እሮሮ የማያጣቸው ተቋማት ሆነው ኖረዋል።

ስለሆነም በየትኛውም መንገድ ቢሆን ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ የፍርድ ቤቶች ለህሊና እና ለሕግ ብቻ አዳሪነታቸው አንዲሁም ፍጹም ገለልተኛ ተቋምነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል። መንግሥት ተከስሶ የሚፈረድበት፣ እንደሌሎች አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ጥፋት ካጠፋ ከቢሮው ተወስዶ እስር ቤት የሚገባበት ዓይነት አካሄድ ከፍርድ ቤቶች የሚጠበቅ የስራቸው አነድ አካል ነው። በዚህ መጠን ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ባይቻል እንኳንም መጪው ምርጫ ፍጹማዊ ዴሞክራሲ እና ሕግ ብቻ የሚገዛው መሆኑን ከዚህ ያፈነገጠ በሙሉ በሕግ እንደሚዳኝ ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ካልተዋቀረ ምርጫ አኪያሂዶ ቅሬታችንን ዳኙ ማለት ዳግም ወደንትርክ መግባት ይሆናል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተመሳሳይ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሲገፈፉ አስቀድሞ መንግሥትን በመውቀስ እና ፍርድ ቤቶች ተገቢ ሥራቸውን እንዲሠሩ በማድረግ የመብት ጥሰትን ለማስወገድ መሥራት የሚገባው ተቋም ነው። ላለፉት 27 ዓመታት ይህን ሲያደርግ ግን አልታየም።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ መነሻ በማድረግ በክልሉ የተካሄደውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በይፋ መግለጫ በግልጽ ያቀረበበት መንገድ እጅግ የሚበረታታ ነው። መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ከማቅረብ ጀምሮ ጉዳዩን እስከመከታተልና ለመገናኛ ብዙሃን እስከ ማሳወቅ ያደረገው ጥረት የተቋሙን ትክክለኛ ሥራ የሚያስመሰክር ነው። ባለፉት ዘመናት ግን በተለይ በ1997 ዓ.ም መንግሥት ሕዝቡ ድምጼ ተጭበረበረ ብሎ ያነሳውን አመጽ ተከትሎ ኢህአዴግ በወሰደው የኃይል እርምጃ በግፍ ስለ ገደላቸው ዜጎች ድምጽ አላሰማም። የሕዝቡ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ብሎ ሪፖርት አላወጣም። ጭራሽም አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎችም ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች ማጣጣል እና የኢህአዴግ ገበና ሸፋኝ ከመሆን የዘለለ ለሕዝብ ጠብ ያለ ሥራ አልሠራም። ይህ ዛሬ መቆሙን በሥራው እያሳየን ነው።

ስለሆነም ከምርጫው በፊት ራሱን በዚህ መጠን አዋቅሮ የሕዝቡን ሰብዓዊ መብት መጠበቅና እንዳይጣስ መከላከል በሚችልበት ዝግጅት ላይ መገኘት ይኖርበታል። እምባ ጠባቂ ተቋም ይህ ተቋም በተመሳሳይ የሕዝብን የመበደል እና የመገፋት ዘመን ማብቃት ማወጅ አለበት በየትኛውም መንገድ ከሕዝብ ወግኖ እንዲቆም ፣ በደል እንዲሰረዝ ፣ በዳይ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እንዲቀጡ እና ፍትህ እንዲገኝ መሥራት አለበት። ፋይል ይዘው አስርተ ዓመታት ሙሉ ፍርድ ቤት የሚመላለሱ ደሃ ኢትዮጵያውያንን እምባ በማበስ በደላቸው እና ጥቃታቸው እንዲቆም ማድረግ ይገባዋል። ይህ ተቋም በዚህ መልኩ ካልተደራጀ ምርጫ ቢካሄድም በምርጫው በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች እንባ አባሽ ሆኖ የሚቆም አይኖርም። ስለሆነም እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሁሉ እንባ ጠባቂ ተቋምም በተመሳሳይ ራሱን በሚገባ ማደራጀትና አሁን የተፈጠረውን የዴሞክራሲ ምህዳር መሠረት አድርጎ የዜጎቹን ጥቅም ማስከበር በሚችልበት መጠን መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ፕሬስ ፕሬስ ሁሉንም ብልሹ አሠራር ነቅሶ የሚያስተካክል ዐራተኛው መንግሥት ነው።ምርጫም ያለፕሬስ ተሳትፎ አይሞከረም።

1984 ዓ.ም ላይ ለፕሬስ ነጻነት ማበብ ተፈጥሮ የነበረው መልካም ዕድል ባለፉት ሃያ ዓመታት በሰበብ አስባቡ እየተሸራረፈና እየባከነ በመቀጠሉ እነሆ በአሁኑ ጊዜ አገራችን በፕሬስ ነጻነትና በዴሞክራሲ አድማስ መስፋት ሳይሆን የመናገር ነጻነትን በመገደብና ጋዜጠኞችን በማሳደድ ከሚታወቁት አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች::

 

ሶስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆነው ቶማስ ጄፈርሰን ነጻነት በተነሳ ቁጥር የሚጠቀስለት አንድ ዝነኛ አባባል አለው:: “እውነትን ለማግኘት የሚረዳው ብቸኛውና ብልሀተኛው ፖሊሲ የሀሳቦችንና የመረጃውን ገበያ ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት መተው ነው:: ጋዜጣ ከማይኖርበት መንግሥትና መንግሥት ከማይኖርበት ጋዜጣ የመምረጥ ሥልጣን የእኔ ቢሆን ኖሮ መንግሥት የማይኖርበት ጋዜጣ ለመምረጥ ለደቂቃ እንኳን አላመነታም ነበር::” ብሏል። በኢትዮጵያ ባለፈው ዘመን በሪፖርት እንደሚቀርበው በሃገሪቱ የፕሬስ ነጻነት ለይምሰል እንጂ ከልብ የተፈቀደ ጉዳይ አለመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው ጫና እና በመንግሥት መዋቅር ሥር ብቻ እንዲጠቃለሉ የሚወጡ ሕጎች በራሳቸው አሳሪ መሆናቸውን አሳይተዋል። ገዢው ፓርቲ የግሉ ራዲዮና ዜና ተቋም እያለው ሌሎች አካላት በዚህ ዘርፍ ላይ እንዳይሳተፉ እገዳ ጥሎም ኖሯል። መንግሥት የፈለገውን ያህል የኅትመት ውጤት እያሰራጨ የግል አሳታሚዎች ከአንድ የፕሬስ ውጤት በላይ እንዳይኖራቸው አግዷል። በጋዜጠኝነት ሥራቸው በዘገቡት ዘገባ ምክንያት በአሸባሪነት ሕግ ከስሶ እስር ቤት ያስገባቸው ጋዜጠኞች ብዙ ናቸው። በዜጎቹ ላይ ስለላ ያካሂዳል።

በተለያዩ መንገዶች የፕሬሱን ህልውና የሚያዳክሙ እርምጃዎች ይወስዳል። በዚህም የሃገሪቱ የፕሬስ እንቅስቃሴ አለ ከሚባልበት የለም ወደሚባልበት ደረጃ አድርሶታል። አሁን ይሄ በቅቷል። ፕሬሱ ማበብ አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እንዳሉትም ፕሬሱ ተጠናክሮ “ዐራተኛ መንግሥትነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ” ምርጫው አንገብጋቢ ጉዳይ አይሆንም። በአጠቃላይ ዶን ትሬሲ “አብዛኞቹ መንግሥታትና ሃገራት ሲፈጠሩ ባላባታዊ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ይዘው ነው። በዚህ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የዚሁ “ሕዝብን ጌታ ሆኖ የመግዛት” ተፈጥሮ ቅሪት አለበት። ይህ ከሥርዓቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት ጊዜ ይፈልጋል” እንዳለው ነውና እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት በአግባቡ እስኪደራጁና እስኪጠናከሩ እንዲሁም እንደ አዲስ ለመሥራት ራሳቸውን እስኪያነቃቁ ድረስ ካልተጠበቀ ምርጫውን ማጣደፍ ሕዝብ የሚፈልገውን እና የሚመኘውን ውጤታማ የዴሞክራሲ ሥርዓት መፍጠር ያስችላል ተብሎ አይገመትም።

(መላኩ ብርሀኑ)

Share.

About Author

Leave A Reply