በሀረሪ ክልል ህገወጥነትና ስርአት አልበኝነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ያሉ ሃይሎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ አሳሰበ።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሀረሪ ክልል ህገወጥነትና ስርአት አልበኝነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ያሉ ሃይሎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ አሳሰበ።

ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የገለፀው ሊጉ በክልሉ የተጀመረው የለውጥ ስራ በሚፈለገው ፍጥነት ለማራመድ የህግ የበላይነት አለመከበር አዳጋች አድርጎታል ብሏል ባወጣው መግለጫ።

በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ችግር የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም የመኖር ክልላዊ እሴቶችን የሚፃረር ተግባር መሆኑን አመልክቷል።

የህዝቡ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ህልም እውን የሚሆነው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ እንደሆነ ነው መግለጫው ያመለከተው።

ሊጉ በመግለጫው በክልሉ ህገ ወጥነትና ስርአት አልበኝነት በይዘቱና መጠኑ እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቁሟል።

በተለይም ካለፈው አመት ወዲህ የከተማ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸውና ከይዞታቸው በጉልበት የማፈናቀል፣ አርሶ አደሮች ከማሳቸውና ከይዞታቸው ማፈናቀል፣ ህገወጥ የመንግስትና የህዝብ መሬት ወረራ እና ህገወጥ ግንባታና ንግድ እየተስፋፉ ነው ብሏል።

እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ይዞታዎችን በሃይል የመውረር፣ የደቦ ፍትህ፣ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ ፣ በሰላም የመኖርና የመስራት መብቶች መገደብ የዜጎችን ድህንነትንና የክልሉን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑት መሆኑን ጠቅሷል።

በተለይም ሰሞኑን በክልሉ በጥቂት ህገ ወጦችና ስርዓት አልበኞች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ንብረት የማውደም እና የመንግስት ሃላፊ መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ ጥቃት የመፈፀም እጅግ አሳዛኝ ተግባር መፈፀሙን ነው መግለጫው ያመለከተው።

በመሆኑም ህግን በሁሉም ላይ እኩል ተፈፃሚ በማድረግና ህግን ተላልፈው የሚገኙ አካላትን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት እንዲከበርና እንዲረጋገጥ የማድረግ ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

የህግ የበላይነት በማስፈን የህዝብና የክልሉን ፀጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡ ከሀብሊ ጎን በመቆም በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግ የማይተካ ሚናውን እንዲጫወት ጥሪ አቅርቧል።

ፋና

Share.

About Author

Leave A Reply