በህገወጥ መንገድ ተይዘው የተገኙ 500 ቤቶች በዕጣ ሊከፋፈሉ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ባደረገው ጥናት፣ በሕገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 500 ቤቶችን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች በዕጣ ሊያከፋፍል ነው፡፡

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ሰናይት ዳምጤ እንደተናገሩት፣ ከከተማ እስከ ወረዳ በተዘረጋ ጥናትና ክትትል እስካሁን 500 የጋራ መኖሪያ ክፍት ቤቶች፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዙና ውል የሌላው ቤቶች ተገኝተዋል፡፡

ቢሮው ባለፉት ወራት በሕገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን፣ የኮንዶሚኒየም መኖሪያና ንግድ ቤቶችን ኦዲት ማድረጉንም የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የቀበሌ ቤት ሆነው የፈረሱ፣ የጠፉ፣ የኪራይ ተመን የሌላቸው፣ ኪራይ የማይከፈልባቸው፣ ውል የሌላቸው፣ ከሕጋዊ ይዞታ ጋር የተቀላቀሉ፣ ተቀጥለው የተሠሩ፣ ተሸንሽነው የተከራዩ፣ ከግለሰብ ይዞታ ጋር ተቀላቅለው ተመላሽ የተደረጉና መረጃና ባለቤት የሌላቸው ቤቶች እንዳሉ ጥቆማ ስለደረሳቸው፣ በሦስት ከፍለው እየሠሩ መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡

ሥራውን ከራሳቸው ቢሮ በመጀመር መረጃ የማጣራት ሥራ ማከናወናቸውንና በርካታ የቀበሌና የኮንዶሚኒየም ቤት መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም ሥራውን ወደ ክፍላተ ከተሞች በማውረድ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን፣ ለዚህም ኅብረተሰቡ በየክፍላተ ከተሞቹ ለዚሁ ሥራ በተከፈቱ ቢሮዎች ጥቆማ እንዲሰጥ ኃላፊዋ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ጠፍተዋል የተባሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ያልተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ 550 መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት እነዚህና የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍጥነት ተገንብተው ለተመዝጋቢዎች እንደሚተላለፉ አስታውቀው፣ ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን ያለማቋረጥ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ሪፓርተር ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply