በሉሲ ጉዞ ከአሜሪካ የተገኘው 60 ሚሊዮን ዶላር የት እንደገባ አልታወቀም ተባለ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለዓለም ለማሳወቅ በሚል ከስምንት ዓመታት በፊት ሉሲ ወደ አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች እንድትጓዝ ተደርጎ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ በወቅቱ ተገልፆ የነበረ ሲሆን ይህ ገንዘብ የት እንደገባ አለመታወቁ ተሰማ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ላይ የመስሪያ ቤታቸውንና የተጠሪ ተቋማትን የ2011 ዓ.ም የ9 ወራት የስራ ሪፖርት ያቀረቡት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው አንድ የምክር ቤት አባል ከሉሲ የአሜሪካ ጉዞ ጋር ተያይዞ ሉሲ በተገኘችበት ሀዳር በተባለው ስፍራ ላይ የሰው ዘር መገኛ ብሔራዊ ሙዚየም ለመገንባት በመንግስት ታቅዶ የነበረ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አይነት ግንባታም ሆነ ስለ ሙዚየሙ የታወቀ ነገር የለም ለምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት በሰጡት ምላሽ የሉሲ ሙዚየም በአፋር ክልል ሀዳር በተባለው ስፍራ ለመገንባት እቅድ ተይዞ የነበረው እሳቸው ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመምጣታቸው ከዓመታት በፊት እንደሆነ ጠቅሰው ለሙዚየሙ ግንባታ የሚሆነው ገንዘብ ከሉሲ የአሜሪካ ጉዞ በተገኘው ገንዘብ ለመስራት ታቅዶ እንደነበርና ሆኖም ያ የተባለው ገንዘብ በማን እጅ እንዳለና መጠኑንም በተመለከተ እንደማይታወቅ ጠቁመው ሁኔታውን በማጣራት ስራ ላይ ነን ብለዋል

መተኪያ የሌላቸው እንደ ሉሲ አይነት የዓለም ቅርሶችን ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳሰስ የሚከለክለውን የዩኔስኮ ህግን በመጣስ ሉሲ ወደ አሜሪካ እንድትጓዝ የተደረገው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ የነበረ ሲሆን የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ታምራት ሀይሉ

Share.

About Author

Leave A Reply