በሕገወጥ ንግድ ምክንያት የቤንዚን እጥረት ተከስቷል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተደጋጋሚ እየታየ ያለው የነዳጅ እጥረት በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተደጋጋሚ የነዳጅ እጥረት (በተለይ ቤንዚን) እያጋጠመ ነው፡፡ ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ከነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እየተቀዳ በየመንደሩ ስለሚሸጥ ነው ሲሉ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

ሕገወጥ የነዳጅ ግብይቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ በተለይ ካለፈው ወር ወዲህ እጥረቱ መባባሱን አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት በቂ የሆነ ነዳጅ በማስመጣት በአግባቡ እየቀረበ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ ይሁን እንጂ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የነዳጅ ሽያጭ አሁን እየታየ ላለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከማደያዎች ውጪ በተለይ ቤንዚን በኪዮስኮች ጭምር እየተሸጠ መሆኑን፣ ይህንን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለ ጥረት የላላ መሆኑ ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል፡፡

ከተለያዩ ነዳጅ ማደያዎች በሌሊት በበርሜል ቤንዚን በየመንደሩ በትርፍ እየተቸረቸረ መሆኑን በግልጽ ማረጋገጥ መቻሉን የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ በቅርቡ በበርካታ በርሜሎች ከተለያዩ ማደያዎች የተጫነ ቤንዚን ለመያዝ መቻሉ ሕገወጥ ንግዱ እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

በአንፃሩ በሕገወጥ ድርጊታቸው የተያዙ ሕገወጦች ላይ አስተማሪ ዕርምጃዎች አለመወሰዱ አሁንም ችግሩ እንዲቀጥል ሊያደርግ ስለሚችል፣ በተለይ በቤንዚን አቅርቦትና ሥርጭት ላይ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች በተወሰነ የዋጋ ልዩነት ከየመንደሩ ቤንዚን የመግዛትና የመጠቀም ሁኔታ መስፋፋትም የችግሩ ሌላ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችና ባጃጆች በየጉራንጉሩ ገብተው በሕገወጥ መንገድ ከነዳጅ ማደያዎች የሚወጣውን ነዳጅ መግዛት ስለሚችሉ፣ በአሁኑ ጊዜ የቤንዚን እጥረት እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ ነዳጅ የማመላለሱ ሥራ ቀልጣፋ ሆኖ አለመገኘት መሆኑንም አቶ ታደሰ አስታውሰዋል፡፡

(ሪፖርተር)

Share.

About Author

Leave A Reply