በምርጫ ይካሄድ ወይስ ይራዘም ክርክር ላይ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አቋም

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የምርጫ ሂደት የሚወሰነው በቀነ-ገደብ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ዝግጅትም ጭምር ነው። ስለዚህ ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው። (1) የግዜና (2) የዝግጅት ጉዳዮች ናቸው።

(1) ዴሞክራስያዊ ምርጫ በተያዘለት ቀን መካሄድ አለበት (መራዘም የለበትም)።
(2) ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ መሆን አለበት (በቂ ዝግጅት ይጠይቃል)።

ለዴሞክራሲ ግንባታ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ቅድመ-ሁኔታ ነው። ለዚህም በቂ ዝግጅት መደረግ አለበት።

ከምርጫ ዝግጅቶች

(1) ምርጫ ሰላም ይፈልጋል። ህዝብ መረጋጋት አለበት። መረጋጋት ከሌለ ፓርቲዎች ህዝብን ማደራጀት አይችሉም። ፕሮግራሞቻቸውን ለህዝብ ማቅረብ አይችሉም፤ ደህንነቱ ላልተረጋገጠ ህዝብ ፖለቲካ መስበክም ተገቢ አይደለም። ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ላልተረጋጋ ህዝብ ማቅረብ አይችሉም። ምርጫ ለማካሄድ መረጋጋት ቅድመ-ሁኔታ ነው።

ህዝብ ከቀዩ መፈናቀል የለበትም። ከቀዩ ከተፈናቀለ ከምርጫ ጣብያው ተፈናቀለ ማለት ነው። የት ሆኖ ይመርጣል? የት ሆኖስ ይመዘገባል? የተፈናቀለ ህዝብ ሚያስፈልገው ምርጫ ሳይሆን መልሶ መቋቋም ነው። ህዝብ ንብረቱ ከተዘረፈና ከወደመ ምርጫ ምን ያደርግለታል?

(2) ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ጠንካራና ገለልተኛ መንግስታዊ ተቋማት (ለፓርቲዎች ሳያዳሉ የህዝብን ፍላጎት የሚፈፅሙ) ያስፈልጋሉ። ገለልተኛ ደሕንነት፣ ፖሊስ፣ ፍርድቤት፣ ምርጫ ቦርድ ወዘተ ተገንብተዋል? በጠቅላይ ፍርድቤት ፕረዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊና በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጥንካሬና ገለልተኛነት አልጠራጠርም። ግን በዚሁ አጭር ግዜ ውስጥ የፍርድቤትና የምርጫ ቦርድ ሙሉ መዋቅር ገለልተኛና ጠንካራ ማድረግ ይችላሉን? ግዜ አያስፈልጋቸውም ወይ?

ባጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት ቀን መደረግ ያለበት ቢሆንም ምርጫ ለይስሙላ ቀነ-ገደብ ለመሙላት ተብሎ የሚከወን ሳይሆን የዝግጅት ቅድመ-ሁኔታ የሚጠይቅ ወሳኝ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ነው። ስለዚህ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ከጉዳይ “ቀን” ወጥተን የዝግጅት ቅድመ ሁኔታን መፈተሽ ይኖርብናል።

እናም በዓረና አቋም መሰረት ምርጫው በተያዘለት ቀን ቢካሄድ ችግር የለብንም። ዝግጁ ነን። ግን አንድ ቅድመ-ሁኔታ እናቀርባለን።

መንግስት ሕግን አክብሮ ማስከበር አለበት። ሰላምና መረጋጋት ይስፈን። መፈናቀል፣ ንብረት መውደምና የንፁሃን ግድያ ይቁም። ተቋማትን ይገንባ! ከምርጫ በፊት የህዝብ ደሕንነት ጉዳይ ይቅደም። ከዛ ፖለቲካ ይከተላል።

መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን የምርጫ ዝግጅት ቅድመ ሁኔታዎች አማልቻለሁ፤ ምርጫውን ማካሄድ እችላለሁ ካለና ማረጋገጫ ከሰጠ ምርጫው በተያዘለት ቀን ቢደረግ ደስተኞች ነን። ካልሆነ ግን መረጋጋት ባልሰፈነበት፣ መራጮች በተፈናቀሉበት፣ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መዋቅሩን እስከ ወረዳ ድረስ ባልዘረጋበት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል ቢራዘም አንቃወምም።

ምርጫ ፖለቲካ ነው። ከፖለቲካ የህዝብ ደሕንነት ይቀድማል። መጀመርያ ሚፈለገው የህዝብ ህልውና ነው። ህዝብ ከሌለ ምርጫ የለም፤ መራጭ ህዝብ ነዋ! ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሰላማዊ መሆን አለበት። ሰላም ከሌለ እውነተኛ ምርጫ የለም። እናም መጀመርያ የህዝብ ሰላም ይስፈን፤ ፖለቲካ ይደርሳል!

ስለዚህ የምርጫ መካሄድ ጉዳይ በዝግጅት ቅድመ-ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል!

ሰላም ለኢትዮጵያ!

 

Share.

About Author

Leave A Reply