በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አካባቢ ግጭት ተቀሰቀሰ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አካባቢ ግጭት መከሰቱ ተነገረ።

የግጭቱ መንስኤ ረዥም ጊዜ የቆየና በዘላቂነት ለመፍታት ሂደት ላይ የነበረ የወሰን አለመግባባት ነው ተብሏል፡፡
በግጭቱ ሰዎች ሞተዋል ከመባሉ ውጭ ስለደረሰው የጉዳት መጠን የተገለጸ ነገር የለም።

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚዋሰን ነው።

ግጭቱ ያጋጠመው በምንጃራ ሸንኮራ ወረዳ አሞራቢት ቀበሌ ከሚዋሰኑት ፈንታሌና ቦሰት ወረዳዎች አዋሳኝ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

ችግሩ የቆየ የወሰን ጥያቄ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት በሁለቱ ክልሎች ባለሙያዎች ተቋቁመው በ2010 ዓ.ም አጥንተው የጨረሱት ውሳኔ ያላገኘ በመሆኑ ግጭቱ እንደገና አገርሽቷል፡፡

በተለይም ቦርጨታ ከሚባለው የቦሰት ቀበሌ አካባቢ ችግሩ መከሰቱ ታውቋል፡፡

ለዛሬ አዳር ደግሞ ኪሊ አርባ (ጋርዳ) በሚባለው የምንጃር ሸንኮራ አካባቢ የእንስሳት መኖና የእንስሳት መጠለያ መቃጠሉንና ውጥረት መንገሡን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡

በሰሞኑ ግጭትም የሰው ሕይወት ማለፉና የአካል ጉዳት መድረሱ ነው የተነገረው፡፡ምን ያህል ሰው እንደሞተ ግን የአካባቢው ባለስልጣናት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ደግሞ ለግጭቱ ሰበብ የሆነው የእንስሳት መኖ መቃጠል ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ እንደተናገሩት ችግሩን ለመፍታት ሁለቱ ዞኖች ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። እንደ አቶ እምቢአለ መረጃ የግጦሽ መሬት እና የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ ነበር።

ከትናንት ጀምሮ ለተቀሰቀሰው ግጭት ሰበብ የሆነው የተሰበሰበ የእንስሳት መኖ በእሳት እንዲቃጠል በመደረጉ ነው። ለመፍትሔውም ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ከምሥራቅ ሸዋ ዞን የስራ ኃላፊዎች ጋር እየመከሩ መሆናቸውንም መምሪያ ኃላፊው ለአማራ መገናኛ በዙሃን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎሳ ፀጋዬም ችግሩ ረዥም ጊዜ የቆዬና በዘላቂነት ለመፍታት በሁለቱ ክልሎች እየተሠራበት ያለ መሆኑን ገልፀው ለሰሞኑ ችግር መባባስም ሰበቦች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጎሳ እንዳሉትም በሁለቱ ዞኖች አዋሳኞች አካባቢ ባለ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሰበብ በከሰል ማክሰልና እንስሳት መሰራረቅ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ ትናንት እና ዛሬ ያለውን ውጥረት ለማብረድም የፀጥታ ኃይል በአካባቢው መሰማራቱ ታውቋል፡፡

ኢሳት

Share.

About Author

Leave A Reply