በርካቶች የተገደሉበትና 100 ሺሕ የሚጠጉ የተፈናቀሉበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ግጭት አልረገበም

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና 100 ሺሕ የሚጠጉ መፈናቀል ምክንያት የሆነው፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በአጎራባች ወረዳዎች የተከሰተው ግጭት አሁንም አለመርገቡ ተገለጸ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ እንዲያረጋጉ ከገቡት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የመከላከያ ኃይል እንዲገባ ጠይቋል፡፡

የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ጃለታ፣ ጥያቄው ለፌዴራል መንግሥት መቅረቡን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

መስከረም 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አራት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሺ ዞን አመራሮች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመገደላቸው ሳቢያ ግጭቱ ተቀስቅሷል፡፡

በተጠቀሰው ቀን የምዕራብ ወለጋ፣ የካማሺና የመተከል ዞኖች አመራሮች በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመውን የሰላም መደፍረስና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እየፈጠሩት ያለውን ችግር ለመፍታት በማሰብ ለውይይት ተቀምጠው እንደነበር፣ አመራሮቹም በጋራ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የካማሺ ዞን አመራሮች በአሶሳ የተደረገውን ስብሰባ ጨርሰው ሲመለሱ፣ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልዩ ስሙ መቀቢላ በተባለ ሥፍራ በታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡

በግድያው ወቅት ጥቃቱን የፈጸሙት የታጠቁ ኃይሎች አመራሮቹ የነበሩባቸውን ሁለት ተሽከርካሪዎችም አቃጥለዋል፡፡

ከዚህም ግድያ በመቀጠል በአካባቢው ውጥረት መንገሡን፣ እንዲሁም በሰዎችና በንብረት ላይ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ሪፖርተር ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ካሉ አጎራባች ወረዳዎች ዜጎች ተፈናቅለው ወደ መሀል በሚገኙ፣ የኦሮሚያ አካባቢዎች መሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር፣ ‹‹እስካሁን ወደ 85 ሺሕ ዜጎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለዋል፣ በተጨማሪም ወደ 30 የሚጠጉ ዜጎች ተገድለዋል፤›› ብለዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ደግሞ እንዲሁ የክልሉ ተወላጆች ከኦሮሚያ ክልል መፈናቀላቸውን አቶ ዘለዓለም አስረድተዋል፡፡

አቶ ዘለዓለም ከዚህ ቀደም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥር የነበሩና በአስተዳደር ወሰን ማካለል ወደ ኦሮሚያ ክልል በተወሰዱ ወረዳዎችና አጎራባች ከሚኖሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተወላጆች 20 ሺሕ የሚጠጉ ተፈናቅለው፣ በክልሉ የተለያዩ ሥፍራዎች መሥፈራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ አኃዝም ጫካ የገቡትን አይጨምርም ብለዋል፡፡

‹‹ከሰው ሕይወት መጥፋት ጋር በተያያዘም ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ ሎሚጣ ቀበሌ በተባለ ሥፍራ 28 የቤንሻንጉል ተወላጆች ተገድለዋል፤›› ያሉት አቶ ዘለዓለም፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም ካማሺ ዞን ውስጥ 16 የሚሆኑ የኦሮሚያና የሌላ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውን አምነዋል፡፡

‹‹የኦነግ ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ‹እኔ ነኝ የኦነግ ትክክለኛ ተወካይ› የሚል የታጠቀ ኃይል ችግሩ በተፈጠረባቸው አጎራባች አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የተናገሩት ኃላፊው፣ ‹‹በአካባቢው ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለመነጠል ሲሠራ ቆይቷል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተለይም በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ይህ ኃይል ችግር ሲፈጥር እንደቆየና የሁለቱም ክልሎች አመራሮች ችግሩን ለመፍታት እንቅስቃሴ ለመጀመር በተስማሙበት ወቅት፣ ይህ የፀጥታ ችግር መፈጠሩን አቶ ዘለዓለም አስታውሰዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ሪፖርተር ያነጋገራቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች፣ እርሻቸውን ጥለው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

በካማሺ ዞን 11 ዓመታት በእርሻ ተሰማርተው የነበሩትና አሁን ተፈናቅለው በሀሩ ሊሙ የሚገኙ አንድ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ ሁለት ሠራተኞቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንና ንብረታቸው መዘረፉን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የዜጎችን መፈናቀል ተከትሎ በምዕራብ ወለጋ ለሚገኙት ተፈናቃዮች ዕርዳታ እየተደረገ እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት ነገሪ (ዶ/ር)፣ በቀጣይም ተጨማሪ ዕገዛዎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በተቃራኒው ከኦሮሚያ ክልልና ከአጎራባች ወረዳዎች ተፈናቅለው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለፈለሱት ከ20 ሺሕ በላይ ዜጎች፣ ምንም ዓይነት ዕርዳታና ዕገዛ ማድረግ እንዳልተቻለ አቶ ዘለዓለም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በዋናነት በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መንገዶችን እየዘጉ ስላስቸገሩ፣ ሌላው ቢቀር መድኃኒቶችን ማድረስ እንዳልተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

‹‹ተፈናቃዮቹ በተለይም ሕፃናትና ሴቶች ለሦስትና ለአራት ቀናት ምግብ ሳያገኙ በየጫካው ይገኛሉ፤›› ሲሉ የችግሩን መጠን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኦነግ ስም እንደሚንቀሳቀሱና ከጥቃቱም ጀርባ አሉበት ስለተባሉት ኃይሎች የተጠየቁት የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ፣ ድርጅታቸውም ሆነ ሠራዊቱ ከጥቃቱ ጀርባ እንደሌለበት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥቃቱን የፈጸሙት በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ፣ የኦነግን ሰንደቅ ዓላማ የያዙና ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ቶሌራ አክለዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply