በሸካ ዞን ባለው አለመረጋጋት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለወራት ሥራ እንደፈቱ ተነገረ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +
በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በምትገኘው ሸካ ዞን የተለያዩ ግጭቶች መሰማት ከጀመሩ ጥቂት ወራቶችን አስቆጠሩ።
ይህም አለመረጋጋት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎችን የትምህርት ጉዳይ አስተጓጉሏል።
የዚህ ችግር መንስኤ በነዚህ ጥቂት ወራት የተከሰተ ሳይሆን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ የሸኮ ሕዝብ ራሳችን በራሳችን እናስተዳድር የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱ እንደሆነ በሥራ ምክንያት ነዋሪነቱን አዲስ አበባ ያደረገውና የአካባዊው ተወላጅ ኮስትር ሙልዬ ይናገራል።
የያደገበትን አካባቢ ‘ትንሿ ኢትዮጵያ’ ሲል የሚጠራው ኮስትር የሸካ ዞን የብዙ ህዘቦች መናኸሪያም እንደሆነች ይናገራል።
በተለይም ከጥቂት ጊዜ ወራት በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከማል የአካባቢውን ሕዝብ ሊያናግሩ ከመጡ ወዲህ ደግሞ ነገሮች መባባሳቸውን የከተማዋ ሰላም ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መንገሻ አዲስ ይናገራሉ።
የሸካ ዞን የመዠንገር፣ ሸካ እና ሸኮ ብሔሮች የሚኖሩበት ሲሆን፤ ከአፈ ጉባዔዋ ጋር በነበረው ውይይት ላይ የተሳተፉት ሰዎች እኛን የማይወክሉ ናቸው በሚል መንስዔ ችግሩ እንደተባባሰ ኮስትር ለቢቢሲ ገልጿል።
«አፈ ጉባዔዋ ውይይት ላይ ሳሉ፤ ከአዳራሹ ውጭ ያሉ ወጣቶች ተቃውሞ በማሰማታቸው ወጥተው አነጋግረዋቸዋል። ቢሆንም ጉዳዩ ሊፈታ ስላልቻለ የአካባቢው ሕዝብ ተቃውሞውን በሥራ ማቆም አድማ እየገለፀ ነው፤ ትምህርት ቤቶችም ዝግ ናቸው» ብሏል ኮስትር።
በቴፒ ከተማ እና የኪ በተሰኘችው ወረዳ ከሆስፒታል በቀር ሌሎች የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሥራ ላይ እንዳልሆኑ ከነዋሪዎችና ከቴፒ ከተማ ፀጥታና ፍትህ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ተሥፋዬ አለም ሰምተናል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ጉዳዩን ለክልልም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት እንዳቀረቡና ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸውም ምሬታቸውን አሰምተዋል።
ከተማዋ ባለመረጋጋቷና የንግድም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመቆማቸው ምክንያት ልጆቻቸውን አዲስ አበባ ድረስ ልከው እያስተማሩ ያሉ ነዋሪዎች እንዳሉ ኮስትር ያስረዳል።
«እንግዲህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ አሁንም ተቸግሮ ነው ያለው፤ የቴፒ ዩኒቨርሲቲም ተማሪዎችን ያልጠራበት ምክንያት ይህ ነው።» ይላል
የአካባቢው ሕዝብ ትኩረት እንዲሰጠው ነው እንቅስቃሴዎችን ወደማቆም የተገባው ሲል ኮስትር ሁኔታውን ያስረዳል፤ «ቢያንስ የፌዴራል ቢሮ ዝግ ሲሆን ለምን ሆነ ብሎ የሚመጣ አካል ይኖራል በሚል” እንደሆነ የሚናገረው ኮስትር «አዲሱ የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስም ጉዳዩን ያውቁታል፤ ሶስት ወር ገደማ ሆነው። ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘንም።» ብሏል።
ጥያቄው ምንድነው?
የደቡብ ክልል መንግሥት የዞን እና ክልል እንሁን ጥያቄዎችን በመመለስ እና በመመርመር የተጠመደ ይመስላል።
«የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በደንብ ያውቀዋል፤ በቅርቡ ዞኖችን እንደ አዲስ ሲያዋቅር እንኳ የእኛን አካባቢ ጥያቄ ችላ ብሎታል» በማለት ኮስትር ቅሬታውን ያሰማል።
የሸካ ዞን በዋናነት የሶስት ብሔር ተወላጆች ይኖሩበታል፤ ሸካ፣ ሸኮ እና መዠንገር።
ከእነዚህ ብሔሮች መሃል የሸካ የበላይነት ስላለ እኛ ራሳችን በራሳችን እንደ ዞን ማስተዳደር እንድንችል ይሁን ዋነኛው ጥያቄ እንደሆነ ኮስትር እና አቶ መንገሻ ያስረዳሉ።
ትላንት ረፋዱ ላይ በቴፒ ከተማ አለመረጋጋት ነበር የሚሉት አቶ መንገሻ፤ ጥያቄያቸው ከራስን ማስተዳደር ወደ መሠረተ ልማት ጥያቄ ወርዷል።
ጥያቄያቸውንም ለክልል ምክር ቤት እንዲሁም ለፌዴሬሽን እንዳቀረቡ ገልፀዋል።
“በጣም በርካታ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ጩኸቱን አሰምቷል። አሁንም ቢሮዎች አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም። በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኮ እና የመዠንገር ተወላጆች ዛሬ ወደ ከተማ ወጥተው አወያዩን፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥያቄያችንን የመሠረተ ልማት ነው ማለቱ ተገቢ አይደለም ብለው ወጥተዋል።» ብለዋል
የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ዋና አማካሪ የሆኑት አኔሳ መልኮ ሁኔታውን አጥንተን ምላሽ እንሰጣለን ብንልም የሚሰማን ማግኘት አልቻልንም ይላሉ።
«ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር የሚሉ አሉ። እኛ ይህ ትክክል ነው ብለን ዛሬውን ምላሽ መስጠት አንችልም። በጥናት ወደፊት ይታያል ተብሎ ተነግሯቸዋል። ዛሬውኑ ይደረገልን፤ ዛሬውኑ ይጠና የሚሉ አሉ” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል
አቶ አኔሳ የአቶ ሚሊዮን አስተዳደር ሁኔታውን በማረጋጋት ሥራ ላይ መጠመዱን ይናገራሉ።
«አመራሩ የማረጋጋት ሥራ ላይ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ነገር እንዳይኖር ነው የምንሰጋው። ዋናው ሰላምና መረጋጋት ነው።»
ለአለመረጋጋቱ ዋናው መንስዔ የሕዝቡ ጥያቄ አለመመለስ ሆኖ ሳለ ጥያቄው መፍትሄ ሳይበጅለት ሰላም ማምጣት አይከብድም ወይ የሚል ጥያቄ ለአማካሪው ሰንዝረንላቸው ነበር።
«ጥናት ይካሄዳል ብያለሁ እኮ፤ አጥኚ ቡድኑም በሰላም መንቀሳቀስ መቻል አለበት። መደማመጥ ከሌለ፤ እኔ ያልኩት ብቻ ይሰማ የሚል ባለበት እንዴት መሥራት ይቻላል?» በማለት ጥያቄ ያነሳሉ
የደቡብ ክልል የገጠር ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ አክሊሉ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማነጋገር ትላንት በሥፍራው ቢገኙም ሰዎች እየመረጡ እንጂ ሁላችንንም አላነገሩንም ሲሉ ነዋሪዎቹ ይወቅሳሉ።
ኃላፊውን ለማግኘት ቢቢሲ በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሊነሳ አልቻለም።
በአካባቢው የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ፀጥታ ለማስከበር እየጣሩ እንደሆነና፤ አከባቢው አሁንም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማይስተዋልበት ኮስትር ይናገራል ።

Share.

About Author

Leave A Reply