በቅርቡ የፀደቀውን የስደተኞች አዋጅ በመቃወም በአዲስ አበባና በጋምቤላ የተቃውሞ ሠልፍ ሊደረግ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በሦስት ተቃውሞና በአንድ ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ፣ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎችን ጥቅም የሚነካና የህልውና ሥጋት ነው ያሉ የክልሉ ነዋሪዎች ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የተቃውሞ ሠልፍ እንደሚወጡ ታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል የተባለው የተቃውሞ ሠልፍ በተመሳሳይ ሰዓት በጋምቤላ ክልልም እንደሚካሄድ የተናገሩት፣ የሠልፉ አስተባባሪ አቶ ፔን ኡጁሉ ናቸው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው አዋጁ የክልሉ ነዋሪዎች ያልተወያዩበት መሆኑን፣ በክልሉም ሆነ በአዲስ አበባ ለጠሩት የተቃውሞ ሠልፍም ፈቃድ ማግኘታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች 300 ሺሕ ብቻ እንደሆኑና በክልሉ በሚገኙ ሰባት መጠለያ ካምፖች ግን ከ400 ሺሕ በላይ ስደተኞች እንደሚኖሩ የተናገሩት አቶ ፔን፣ በቅርቡ የፀደቀው አዋጅ የክልሉን ነዋሪዎች ጥቅም የሚያስነካ ነው ብለዋል፡፡ ከክልሉ ነዋሪዎች የላቀ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ከተደረገ፣ ሌላ የደኅንነት ሥጋት እንደሚያስከትልም አስምረውበታል፡፡

አቶ ፔን በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ ነዋሪዎችና በስደተኞች መካከል ተፈጥረዋል ያሉዋቸውን ግጭቶችን በማስታወስ፣ አዋጁ ለጋምቤላ ነዋሪዎች የህልውና ሥጋት እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በቅርብ ጊዜያት ብቻ 100 ሰዎች የሞቱብን በስደተኞችና በነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ፔን እንደሚሉት፣ አዋጁን በተመለከተ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የክልሉ ነዋሪዎች ጋርም ውይይት አለመደረጉ ተቀባይነት የለውም፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም ላይ 21.3 ሚሊዮን ሕዝቦች አገራቸውን ለቀው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያም ከ26 አገሮች የመጡ ከ930,000 የሚበልጡ ስደተኞች እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ከጎረቤት አገሮች ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች ጋምቤላን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 27 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በመስከረም 2016 በኒውዮርክ ከተማ በተደረገው የመሪዎች ስብሰባ የስደተኞችን አያያዝ ለማሻሻል ኢትዮጵያ ቃል መግባቷ የሚታወስ ነው፡፡ የገባችውም ቃል አንድ ስደተኛ በኢትዮጵያ እስከሚኖርበት ጊዜ ድረስ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት በኢኮኖሚና በማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚኖረውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በግብርና፣ በንግድና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ መሥራት፣ በተመቻቹ የሥራ ዕድሎች መሰማራት፣ የመማር መብት ማግኘትና የመሳሰሉትን ጥቅሞች ለማጋራት በስብሰባው ቃል ገብታለች፡፡

በአፍሪካ በጣም ተራማጅ ሲባል የተሞካሸው አዋጁ በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚኖሩ ስደተኞች የመማር፣ የመሥራት፣ የመደራጀት፣ የመዘዋወር፣ ንብረት የማፍራት ብሎም የማስተላለፍ፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የማግኘት መብት ጭምር የያዘ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከለላ ያገኙና ጥያቄ ያቀረቡ ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢ ከማኅበረሰቡ ጋር ተዋህደው የአገሪቱ የሊዝና የፋይናንስ አሠራር መሠረት በማድረግ በልማት እንዲሰማሩ የሚያስችለው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ፣ ከነዋሪዎቹ ቁጥር የላቀ ስደተኞች ለሚኖሩበት የጋምቤላ ክልል ግን አደጋ እንደሆነ አቶ ፔን ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ቢቀር የአዋጁ ተፈጻሚነት በተወሰኑ ክልሎች ላይ ጫና እንዳይፈጥርና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በተቃውሞ ሠልፉ የሚያሰሟቸውን መፈክሮችም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በክልሉ የሕዝቦችን መብት ማወቅና መቀበል በጋራም ለመሥራትና ለመኖር የሚያስችል፣ በሌላው ኪሳራ ማትረፍ የሌለበት ነፃና ግልጽነት የነገሠበት ሥርዓት እንዲሰፍን እንታገላለን፣ የጋምቤላ ሕዝብ በስመ አንድነት ከእንግዲህ ጭቆና አይቀበልም፣ የጋምቤላ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት እንዲከበር በፅኑ እንታገላለን፣ ሰሙ ወዳጅነት ወርቁ ግን የጥቂቶችን ጥቅም ያገናዘበ ብልጣ ብልጥ የሆነ አንድነት የጋምቤላ ሕዝብ በጭራሽ አይቀበልም፣ የጋምቤላ ወጣቶችን ነፃነት በማፈን የክልሉ ሀብት ዝርፊያንና የመብት ረገጣን በጋምቤላ ክልል ውስጥ እንደ ከዚህ በፊት እንዲፈጸም አንፈቅድም፣ እ.ኤ.አ. መስከረም 20 ቀን በኒዮውርክ ከተማ 71ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ጫናና ሥቃይ በውስን ክልሎች ትከሻ እንዳይወድቅ በሚጠይቀው መሠረት በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞች በሁሉም ክልል በእኩል እንዲሠራጩ አጥብቀን እንጠይቃለን፣ ኢትዮጵያ የስደትና ፍልሰት መነሻ፣ መሸጋገሪያና መዳረሻ አገር መሆኗን ታሳቢ በማድረግ ይኼንኑ ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ መሠረት ልማቶችን በማሳደግና በማስፋፋት ለዜጎችና ለስደተኞች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገው ሥራ የጋምቤላን ሕዝብ ጥቅምና ህልውና መስዋዕት በማድረግ እንዳይፈጸም አጥብቀን እንቃወማለን፤›› የሚሉ መፈክሮችም መዘጋጀታቸውን አቶ ፔን ለሪፖርተር የላኩት ዶክመንት ያስረዳል፡፡ ~ ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply