“በባድመ ጉዳይ ሐቀኛና ሁለቱንም የሚጠቅም ውሳኔ ያስፈልጋል” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግዮን፡- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዴት አዩት?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ውሳኔው በሁለት የሚከፈል ነው:: ምናልባት መጠነኛ ዕውቀት ያለኝ በባድመ ጉዳይ ነው:: ባድመን በተመለከተ መንግሥት አስረክባለሁ የሚል ቃል ገብቷል የሚል ነገር ሰምቻለሁ:: እኔ ውጪ ነበርኩ፤ በአካል አልሰማሁትም:: ግን እንደዚህ ዓይነት ነገር ተብሎ ከሆነ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተስማምተው ያቋቋሙት የድንበር ኮሚሽን፣ በማካለል ደረጃ ባድመን ወደ ኤርትራ አጥፎታል:: መጀመሪያውኑ ባድመ በኢጣልያና በኢትዮጵያ በተደረገው ውል መሠረት ባድመ ወደኤርትራ ይታጠፋል:: አሁንም በድንበር ኮሚሽኑ መሠረት ባድመ ወደኤርትራ ይታጠፋል:: በወረቀት ደረጃ የተሰመረው መስመር ባድመን ወደኤርትራ ያጥፋታል:: መስመር ከማስመር በተጨማሪ ዲማርኬሽን፣ ማለትም በቦታው ተገኝቶ ችካል መትከል ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያና ኤርትራ የተስማሙት መጀመሪያ በወረቀት ይሰመራል፤ ከዚያ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ችካል ይተክላሉ ይላል:: በወረቀት ደረጃ የተሰመረው ተከናውኗል:: የቀረው ችካል መትከሉ ነው፤ እስካሁን ድረስ ችካሉ አልተተከለም:: ችካል ይተከል ሲባል የድንበር ኮሚሽኑ ጓዙን ጠቅልሎ ወጣ:: ይህም የሆነው አቶ ኢሳይያስ የሠላም አስከባሪ ኮሚቴው፣ ኮሚቴውን ከአካባቢው ሲያስወጣ የድንበር ኮሚሽኑ ዳኞችም ከዚያ ተነሥተው ወጡ:: በዚህ ምክንያት ችካል አልተተከለም:: አሁን እንግዲህ ኢህአዴግ ሲያስረክብ የግድ ሁለቱም ሀገራት ተገናኝተው መደራደር ይኖርባቸዋል:: የወረቀቱ መስመር የሚያሳየው ወረቀት ብቻ ነው እንጂ ያለውን እውነታ በደንብ አያሳይም:: ለምሳሌ፡- መስመሩ ት/ቤትን፣ መካነ መቃብርን፣ የሃይማኖት ተቋማትንና ሌሎችን ለሁለት ይከፍላል:: ናይጄሪያና ካሜሩን የወሰን ውዝግብ በነበራቸው ጊዜ፣ እኔ በተባበሩት መንግሥታት ተቀጥሬ በሕግ አማካሪነት እዚያ እሠራ ነበር:: በወረቀት መስመሩን ስናሰምር የነበረውን ሁኔታ ባናውቅም ወደ ቦታው ተገኝተን ችካል በምናስተክልበት ጊዜ፣ መስመሩ አንድን ቤት ለሁለት ይከፍላል:: በዚያን ጊዜ ናይጄሪያና ካሜሩን ተስማምተው ቤቱ ወደካሜሩን ይታጠፋል:: በምትኩ ደግሞ ናይጄሪያ ሌላ ነገር ይተካላታል ተብሎ በስምምነት ያንን ቤት ወደካሜሩን አጠፉት:: አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ችካል በሚተከልበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ብዙ ጉራማይሌ ነገሮች ስለሚኖሩ ሁለቱ ወገኖች ተገናኝተው መደራደርና መስማማት ይኖርባቸዋል::

ግዮን፡- የኤርትራ መንግሥት ይህን ውሳኔ ይቀበላል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ባድመን ላስረክብ ሲል ምንድነው የሚያስረክበው? የትኛውን ነው? በወረቀት ላይ የሰፈረውን ብቻ ነው? ደግሞ በችካል ቢያስረክብስ ትምህርት ቤት፣ መቃብርና ቤተ ክርስቲያን ለሁለት እየከፈለ ነው? በዚህ ዓይነት እንዴት አድርጎ ይሆናል? የግድ መስማማትን ይጠይቃል:: ባድመ የኤርትራ መሆኑ የሚያከራክር ባይሆንም ሐቀኛ የሆነ፣ የተመጣጠነ፣ ለሁለቱም ጠቃሚ የሆነ ሁኔታ ሊሆን የሚችለው ተነጋግረው መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ሲያስተካክሉ ነው::

ግዮን፡- ከሕግ አንፃር ሲታይ ህዝብ ሳይወስን፣ ፓርላማ መቅረብ እያለበት በአንድ ድንገተኛ ውሳኔ እንዲሀ ዓይነት ነገር ማምጣት ተገቢ ነው? የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ በወሰነው የሚሆን ነገር ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እርግጥ ለፓርላማ በማቅረብ ማፀደቅ ነበረባቸው:: ይሄ ጉዳይ እኮ እጅግ ከባድ ጉዳይ ነው:: በህዝበ ውሳኔ (በሪፈረንደም) ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያን አንዲት ጋት መሬት ፓርላማ እንኳን ሊሰጥ አይችልም::

ግዮን፡- ይህ ፍላጎትና ውሳኔ የመጣው ከማን ይመስልዎታል? ከህወሓት ወይስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ? ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይህን ማወቁ አስቸጋሪ ነው:: ይሄ ነገር በህወሓት ጊዜ የተነሣ ነገር አልነበረም:: አሁን የተነሣው ዶ/ር ዓቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ስለሆነ፣ ምናልባት በእርሳቸው አነሳሽነት የተጀመረ ነገር ሊሆን ይችላል:: በእውነት እንቅስቃሴው የሚደገፍ ነው፤ የኢትዮጵያ መብት በተለይ የባህር በር መብቷ እስከተጠበቀ ድረስ በኤርትራና በአትዮጵያ መካከል ሰላም መስፈን አለበት:: በእውነት ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ ሀገር፣ ሁለት ህዝብ ናቸው:: መከፋፈል የሌለባቸው ሁለት ሀገሮች ቢኖሩ ኤርትራና ኢትዮጵያ ነበሩ:: አሁንም ቢሆን ምናልባት በሂደት ወደበለጠ መቀራረብ፣ ወደኮንፌደሬሽን ሊሄድ ይችል ይሆናል:: የኤርትራ መለየት በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው:: ከአፍንጫቸው በላይ አርቀው ማሰብ የማይችሉ መሪዎች ያደረጉት ነገር ነው እንጂ በህዝቡ ፍላጎት የተደረገ ነገር አይደለም::

ግዮን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር በቅድሚያ ሰላማዊ ግንኙነት ሳይፈጥር ፀብ ላይ ባሉበት ሁኔታ በጥድፊያ ውሳኔ ላይ መድረሱ ምንን ያመለክታል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይህ ውሳኔ ሁለቱን ወንድማማች ሀገራት በሚጠቅም መልኩ ከተፈታ ወደሰላም ያመራል:: ከዚያ በኋላ የሰላም ስምምነት ያደርጋሉ:: ግን መጀመሪያ የሁለቱም መብት በሚከበርበት ሁኔታ ጉዳዮች መጠናቀቅ አለባቸው:: በተለይ የባድመ ሁኔታ በጣም የህዝቡን ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ነው:: በባድመ ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወገኖቻችን አልቀዋል:: የመሬቱ ጠቃሚነት አይደለም ባድመን ብዙ ዋጋ ያሰጠው፤ ብዙ የኤርትራና የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም ፈሷል::

ግዮን፡- ከዓመታት በፊት የአልጀርሱ ስምምነት ለኤርትራ ከፀደቀ በኋላ፣ “ውሳኔው ሳይፈፀምልኝ ስለቆየሁ እኔ ተጎድቻለሁ፤ እንደዚህ ዓይነት ካሣዎች ይገቡኛል” የሚል ቅድመ ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት አያቀርብም? የኢትዮጵያ መንግሥትስ ከመወሰኑ በፊት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ማቅረብ አልነበረበትም?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ውስጡን ምን እንደተባባሉ አላውቅም፤ ግን በአልጀርስ ስምምነት ብዙ ያልተፈፀሙ ውሳኔዎች አሉ:: ለምሳሌ፡ – ከድንበር ኮሚሽን በተጨማሪ የካሣ ኮሚሽን የሚባል ነበር:: ይህ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ 10 ሚልዮን ዶላር ተጨማሪ ፈርዶላታል:: ይህ ገንዘብ አልተከፈለም፤ ወደፊትም የሚከፈል አይመስለኝም:: ብዙ ያልተፈፀሙ ነገሮች አሉ:: በመሠረቱ ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም፤ ነገሩን በሰላም ለመቋጨት እንቅፋት ነው የሚሆነው::

ግዮን፡- ሌላው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የወሰነው፣ የህዝብ መሠረተ ልማት ተቋማትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥ ተዘጋጅቷል፤ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከዚህ በፊትም ሲባል እንደነበረው አይ. ኤም. ኤፍ እና የዓለም ባንክም በተለይ ቴሌኮምን ወደግል መዞር አለበት ብለው ብዙ ይወተውቱ ነበር:: እውነትም በቂ ምክንያት ያላቸው ይመስለኛል:: ምክንያቱም ቴሌኮም በቴክኖሎጂው ከዘመኑ ጋር ብዙም አልተራመደም:: በየጊዜው ኮኔክሽን በየቦታው የለም ይባላል:: ተወዳዳሪ ስለሌለበት ክፍያው በጣም ውድ ነው:: ኬንያ ውስጥ ተመሳሳይ ወደ20 አማራጭ ቴሌኮምዩኒኬሽኖች አሉ:: የኛ ግን ሞኖፖሊ ነው:: ሞኖፖሊ ብዙውን ጊዜ እድገትን ያቀጭጫል:: በዚህ ምክንያት ኢትዮ ቴሌኮም ከዘመኑ ጋር አላደገም:: ስለሌሎቹ ዘርፎች ባለው ኢኮኖሚስት ስላልሆንኩ ልለፋቸው:: ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ 75 ዓመቱ ነው፤ ከተቋቋመ:: የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ተሸክሞ ዓለምን ይዞራል:: የውጭ ሀገር ባለድርሻ በዚህ ውስጥ መግባቱን እኔ አልደግፈውም:: ኢትዮጵያውያን ውጪ ሀገር ሆነን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደመናውን ሰንጥቆ በሰው ሀገር ማረፊያ ላይ ሲሮጥ ሲታይ የሆነ ስሜት ይቀሰቅሳል:: አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሚያለቅሱም አሉ:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ መታየት የለበትም፤ ሀገርን የሚወክል ድርጅት ነውና:: ከኢኮኖሚው በላይ የሀገር ማንነት ተወካይ መሆኑና የሚፈጥረው የኩራት ስሜት ከግንዛቤ መግባት ያለበት ይመስለኛል::

ግዮን፡- እነዚህ ትልልቅ ውሳኔዎች በጠቅላይ ሚነስትሩ በቀጣይ የመሪነት ጊዜያቸው ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ይኖራል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- በዶክተር ዓቢይ ጠቅላይ ሚነስትርነት ህዝቡ ተስፋን ሰንቋል:: ብዙ ለጆሮ የሚጥሙ ነገሮች ተሰምተዋል:: እንግዲህ በሥራ ላይ ለመዋል ጊዜ ቢጠይቅም፣ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ በመሪዎች ያላየናቸውንና ያልሰማናቸውን ጥሩ ጥሩ ቃላት እየተናገሩ ነው:: በተግባር ይውሉ እንደሆነ እንጠብቃለን፣ እናያለን:: በእኔ ጊዜ በመሪዎች እንደዚህ የረካንበት ጊዜ አልነበረም፤ ግን ገና ብዙ ይቀራል::

ግዮን፡- እናመሰግናለን::

Share.

About Author

Leave A Reply